እንኳን ደኅና መጡ

እንኳን በደኅና መጣህ

በአባወራ ድረ ገጽ አባትነትንባልነትንወንድነትን እና ራስነትን(መሪነትን) እንወያይበታለን።

አባት ብለን ለልጆቹ ጥላ ከለላ፣ የሚያስፈልጋቸውን አቅራቢ ይኽም ተፈጥሮኣዊ ግዴታው መኾኑን የሚረዳ፤

ከልጆቹ ደግሞ ስነስርዓትን፣ስነምግባርን በፈንታው የሚፈልግ የሚጠብቅ

ልጆቹን መክሮ፣ ገስጾ፣ ቀጥቶ የሚያሳድግ

ባል ብለን ሚስቱን የሚያሟላ እርሷም የምታሟላው፤ በወንድነቱም የወደደችውና ያገባችው መኾኑን ተረድቶ የወንድነት ሚናውን በባልነቱ የሚወጣ፤

በተለይም ለመኝታቤት ደስታዋ የሚታትር  ይኼ ደስታዋም ደስታው፣ እርካታዋም እርካታው የኾነ።

ወንድ ብለን ጀግና፣ ደፋር፣ ቆራጥ፣ አስቦ የሚናገር የሚያደርግም ለተናገረው ላደረገውም ነገር “እኔ ነኝ” ብሎ ኃላፊነት የሚይወስድ፤

በየወንዙ (ደጋግሞ)የማይምል ቃሉን የሚጠብቅ፣ የፈጣሪውን የአባቶቹን፣ የወገኖቹን አደራ ለመጠበቅ በሕይወቱ የሚወራረድ፤

ከሚስቱ፣ ከልጆቹ፣ ከሀገሩ፣ በፊት የሚሰዋ።

ራስ መሪ፣ የመሪነትን ስልጣን ከፈጣሪው የተቀበለ፣ ቤቱን ቤተሰቡን ሚስቱን ልጆቹን የሚመራ፤

ራሱን የገዛ በስነስርዓቱም ኾነ በስነምግባሩ ለሚስቱ፣ ለልጆቹ አርአያ የሚኾን
ከፈጣሪ በተቀበለው አደራና ኃላፊነትም መሠረት ሚስቱን ልጆቹን በስርዓት የሚቀርጽ በስነምግባር የሚያንጽ፣ የሚመክር የሚገስጽ የሚቀጣም

ይኼን ሰው እኔ አባወራ እለዋለሁ።

ጽሑፎቹ የእኔን የሕይወት ተሞክሮና አስተውሎት መነሻ ተደርገው የተጻፉ እንጂ በምንም ዓይነት መልኩ የሐኪም ወይም የባለሙያን ምክር ለመተካት የተሰናዱ አይደሉም።

ስለዚህም የስነልቦናም ኾነ የስነአእምሮ እንዲሁም በአፍኣ ያለው አካል መቃወስ ሲገጥምህ መጀመሪያ ባለሙያ ማማከርህን እርግጠኛ ኹን። ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ የምጠቁምህም ኾነ የማቀብልህ መረጃዎች አካላዊ ስነልቦናዊ(መንፈሳዊ) እና አእምሮአዊ ዝግጁነት ይሻሉና።

ጽሑፎቼ ውስጥ በብዛትና በድግግሞሽ ስለ ስነስርዓትና ስነምግባር ታነባለህና እነርሱን መስማት ካልፈለግህ ስለጋጠወጥነት ስለስንፍና በግልጽ ስናገር ቅር የሚያሰኝህ ከኾነ ይኽ ገጽ ላንተ አይኾንም።

እንዲሁም በማሕበረሰባችን ውስጥ “ነውር” ተብሎ ስለሚቆጠረው ወሲብ ለትዳር፣ ለትውልድም በወል፣ ላንተም ኾነ ለሚስትህ በግል ያለውን ጥቅም፣ እውነታውን  በግልጽ ስጽፍ ምቾት  ከነሳህ ይኽ ያንተ ቦታ አይደለም።

ከዚኽ ውጪ ግን ወንድነታችንን ስለራሳችን ልዕልና ስለሚስቶቻችንም ደስታ ስለሀገር ተረካቢ ትውልድ፣ ማሳደግ ፈልገህ ከመጣህ መልካም አደረግህ።

በሕይወት ካለፍኩበት፣ ከመጽሐፍት ከተማርኩት፣ በታላላቆቼም ከተመከርኩት የምታተርፈው ሳይኖር አይቀርምና እንኳን ደኅና መጣህ ስልህ ከልብ በኾነ ወንድማዊ ሰላምታ ነው።

በድጋሚ እንኳን በደኅና መጣህ