ሁሉን አትብላ!

ሳተናው!

ምግብ የሚሠሩ ነጋዴዎች ደንበኞቻቸውን ነገ እና ከነገወዲያም ተመልሰው እንዲመጡ የሚያደርጋቸውን የምግብ ዓይነት ያዘጋጃሉ። ይኹን እንጂ ነጋዴዎች የገበያ ወረት ጠባቂዎች ናቸውና ካንተ ገንዘብ ከማትረፍ ያለፈ ብዙ ርቀው በመሄድ ምግባቸው በወደፊት ጤናህ ላይ ስለሚፈጥረው ጉዳት አያሳስባቸውም።

ለዚህም በማስረጃነት የምሰጥህ በዓለም ላይ ተሰራጭተው የሚገኙትና በሺህ የሚቆጠሩ ቅርንጫፍ ያላቸው የ”ደራሽ-ምግብ”(fast food) ምግብ ቤቶችን አስተውል። እነዚህ ምግብ ቤቶች “የሚጣፍጥ ነገር መሥራት” ብቻ ብለው እንዳይመስልህ ምግብ የሚያዘጋጁት፤ ይልቁንስ የሰውን ልጅ ፍላጎትና ዝንባሌ የሚያጠኑ፣ ጠባዩንና ልማዱን የሚከታተሉ የሥነ-ልቦና እና ሥነ-አእምሮ ተመራማሪዎች እንዲሁም የኮምፒውተር ሶፍትዌሮችን በመጠቀም አመጋገቡንም በማጥናት በማጥመድም እንጂ። በዚህም መሠረት እነርሱ የሚያቀርቡልህ ምግብ ስታየውና ስታሸተው የሚማርክህ ስትበላው ደግሞ ድገመው ድገመው የሚያሰኝህ ይኾናል።

ይኹን እንጂ እንደዚህ ተወስውሰህ ይጠቅምህ ዘንድ ገዝተህ የምትበላው ምግብ በጤናህ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።

ወንድም ዓለም!
ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከማሕበራዊ ሚዲያዎች እና ከትምሕርት ተቋማትም ጭምር በእውቀትና በመረጃ መልክ ተቀብለህ ወደ አእምሮህ ብሎም ወደ ልብህ የምታስገባቸው ጽንሰ-ሀሳቦች ላይ ትልቅ ጥንቃቄ አድርግ።

ዓለም ውሸትን አጣፍጣና አፍጥና ወደ ጆሮህ ማድረስ ትችልበታለች። መገናኛ ብዙኃኑን፣ የማሕበራዊ ትስስር ገጹን እና ትምሕርት ቤቶችን እስኪ ታዘባቸው። ትውልዱ ኑሮውን የሚያሻሽልበትን፣ ራሱን የሚገዛበትን እና ሀገሩን የሚያሳድግበትን መረጃ ከማቀበል ይልቅ ዘርን ከዘር፣ ጎሳን ከጎሳ፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ወንድን ከሴት፣ ባልን ከሚስት፣ ወላጆችን ከልጆች የሚከፋፍል ዜና ከሽነውና አጣፍጠው ሲያቀርቡ ትሰማለህ፣ ታያለህ፤ ትወድላቸዋለህ ታጋራዋለህም።

ይኽም ኾኖ ደግሞ ዕለት፣ ዕለት የጥፋትንና የሞትን ዜና እየነገሩህ ሰምተህ የማትጠግባቸው፣ ዐይተህ የማትሰለቻቸው አድርገውሃል።

ግን ለምን ወንድም ዓለም?
አብዛኞቻችን ስህተት ፈላጊ፣ ስናገኝም ፈራጆች፣ በዚህም ላይ እኛ የማንገኝበት ይመስል ተመጻዳቂዎች ነን። ከዚህም የተነሳ ልክ እንደ ደራሽ-ምግቡ(fast food) ለጊዜው አጓጉተው፣ ሰቅሰው ሲይዙህ ስትከታተላቸውም፣ እያደር ደግሞ ከሚያመዛዝነው አእምሮህ ይልቅ የምታምናቸው፣ ከፈጣሪህም እውነት ይልቅ የምትቀበላቸው ይኾናሉ።

ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ፦ ልክ እንደ ደራሽ-ምግቡ ሱስ እስኪኾንብህ ድረስ ትመገብና ጉዳት እንዳለው ቢገባህ እንኳ መተዉ ሲከብድህ፤ በዚህም እንድትጎዳ፤ የራስህን አመክንዮ ገፍተህ፣ የፈጣሪህን ቃል ሽረህ አምነህ የሰማሃቸው እነዚህ ተቋማትም የኋላ የኋላ የጥፋት ፈረስ መኾናቸውን ስትሰማ መመለስ ይቸግርሃል፦ ከኅሊናህ፣ ከፈጣሪህ ተጣልተሃልና ያስፈራሃል።

ይህ ታዲያ አንተ ላይ በግል፣ ትዳርህ ላይ፣ ቤተሰብህ፣ ትውልድና ሀገረህም ላይ ያለው አሉታዊ እንድምታ የትዬሌሌ ነው።

ሳተናው!
ያንን ደራሽ-ምግብ ስትበላ የሚሰማህን ስሜት እንደምትከተል አስቀድመው አውቀው እንዳጠመዱህ፣ ጤናህን እንዳሳጡህ ነገር ግን እነረሱ (ነጋዴዎቹ) እንደከበሩ፣ ይኽንንም ኾን ብለው አውቀው እንደሚያደርጉት፤ ቀድሜ በጠቀስኩልህ ተቋማትም በኩል የሚያልፉ መረጃዎች አንተ ስትሰማቸው ምን እንደሚሰማህ የሚያውቁት ጠባቂዎቻቸው አጣፍጠው ይሰጡሃል አንተም ግራቀኙን ሳታይ በግብታዊነት ለግብረ-መልስ ትቸኩላለህ በዚህም አንተ፣ ቤተሰብ፣ ትውልድ፣ ሀገር ይናጋሉ።

ሰሞኑን በማሕበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ስንቀባበላቸው የነበሩ፣ አሁንም ያሉ የፈጠራ ክስተቶች ይኽንኑ ያጠናክራሉ። የሚገርመኝ ደግሞ የመመርመር፣ የማጣራት እና ከወገኝተኝነት ነጻ የኾነ ዜና መሥራትን ተምረው እንደኛው መረጃውን ከዚሁ መንደር ለቅመው የሚዘግቡትን “ጋዜጠኞች” ሳይ የችግሩን ሰፋትና ጥልቀት አሳሳቢ መኾኑን ትገነዘባለህ።

ሳተናው!
እባክህን ስሜታዊ አትኹን! ስሜታዊ ስትኾን ማንም፣ ወደ የትም፣ መቼም፣ እንዴትም፣ ለምንም፣ ለማንም ይጠመዝዝሃል።

የምትኖርበትን ዓላማ አጥርተህ ለይ!

የቀን ውሎህን በርከክ ብለህ ከፈጣሪህ በተቀበልከው እንጂ ከፌስቡክ በምትቃርመው አጀንዳ አትወስን!
.
.
.
.

ስሜታዊ ወንድ የሚስቱን ፈተና ይወድቃል……. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *