ለምስኪን ሕግ ሲወጣ ለዱርዬ ግን ያለውም ይፈርሳል

ሳተናው!

ቆየት ካሉት ጦማሮቼ ላይ ሴት ልጅ ምን ዓለማዊም ኾነ መንፈሳዊ እውቀትን ብትሸምት፣ ገንዘብም ብታደርግና “እኖረዋለሁ” ብትልም ቅሉ፤ ይበልጡን ስሜቷን እንደምትከተል ጽፌያለሁ። እርሷ ለአንድ ክስተት አመክንዮንውን፣ ገሃድ የወጣውን ሐቅ ብታውቀው እንኳ በዚያ ቅጽበት የተሰማት ስሜት የተረዳችውን አመክንዮ፣ ያካበተችውን ዓለማዊም ኾነ መንፈሳዊ ልምምድ ይረታባታል።

አንዲት ወደብ ዳር የታሠረችን መርከብ ብታይ ለአፍታ በቆመች ብትመስል እንኳ ስትናወጥ ውላ ስትናወጥ ታድራለች። ኾኖም ግን በወፍራም ገመድ ከወደቡ ጋር ታስራለችና መናወጧ ለክፉ የሚሰጥ አይደለም።

ለሴት ልጅ ስሜቷ ማዕበል ነው፦ መቼ እንደሚነሳ፣ በምን እንደሚነሳ፣ ወዴት እንደሚነሳ፣ ለምን እንደሚነሳ፣ ለምን ያክል ጊዜ እንደሚቆይ እና መቼ እንደሚያርፍ፣ በምንስ እንደሚያርፍ አታውቀውም። በእነዚህ የስሜት ማዕበሎች ወቅትም መርከቧ እንደታሠረችበት ወፍራም ገመድ ያለ ራሱን የገዛ ወደብ ሊኾናት የሚችል አባወራ ወንድ ትሻለች።

አልያ ግን ከእርሷ የባሰና በእርሷ ላይ ይቅርና በስሜቶቹ፣ በብልቶቹ ላይ እንኳ ስልጣን ከሌለው (እነርሱን መግዛት ያልቻለ) ወንድ ጋር ስትኖር በግራ መጋባት ዓለም ውስጥ ትባክናለች። እነዚህ የበዙ የውስጥ ጥያቄዎቿ እረፍት ስለሚነሷትም በተደጋጋሚ “አዋቂ” የመፈለግ፣ የመሄድ ነገርም ይስተዋልባታል።

ከሚስትህ ጋር ተጣብቀህ ፍሬያማ ትዳር ትሻ ከኾነ እነዚህን ሁሉ ማወቅ ግን ያንተ ግዴታ ይኾናል። እነዚህን ካላወቅህ ከእርሷ ጋር ለመኖር የሚያዳግትህና ያንተንም አለማወቅ በእርሷ “አዋኪነት” አሳበህ እርሷንም ኾነ ሴቶችን ሁሉ ስትከስ የምትኖር ሰነፍ ትኾናለህ።

ሳተናው!
ይኼንን የሴት ልጅ ጠባይ እንዳትረዳ የሚጋርዱህ ታዲያ ከዘመን “ስልጣኔ” ጋር በ”እኩልነት” ስም የመጡ በዘፈን፣ በኪነጥበብ፣ እና በሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን ውጤቶች የምታገኛቸው ናቸው።

አንተ ይኼንን መገንዘብ ሲከብድህ፣ አልያም መገንዘብ ሳትፈልግ ስትቀር ነው እንግዲህ ራስን በመግዛቱ ከእርሷ በታች የኾንክና ለስሜቷ ወደብ የማትኾናት መኾንህን ስታውቅ አንተን መያዣ መጨበጫ ሕግ የምታወጣልህ።

ስለዚህም ራስህን መግዛት ከዚህም የተነሳ ቤትህንም በሥነ-ስርዓት እና ሥነ-ምግባር መምራት ያንተ የተፈጥሮ ግዴታህ ኃላፊነትህም ኾኖ ሳለ የተገላቢጦሽ እንዴት ልትኖር እንዳለህ እርሷ ስርዓትን ታበጅልሃለች።

ምንም እንኳ እኔ የምወዳት እህቴን እንዲህ አድርጊ ብዬ ባልመክራትም ለእርሷ ይኼን መንገድ መምረጥ ግን ዋነኛው የመንገዱ ጠራጊ አንተው ራስህ እንደኾንክ ልነግርህ እወዳለሁ። ልብ አድርግ! ሚስትህ ምን መንፈሳዊ ትምሕርትንም ኾነ ተፈጥሮኣዊ ሳይንስ ብትማርና ከዚህም የተነሳ ትዳርን መምራት ያለበት ወንዱ እንደኾነ ብታውቅም እንኳ ስሜቷን የማትረታ፣ የማታሳርፍም ስትኾንባት ከእርሷ የባሰ ስሜተ ስስ እንዳገባች ስታውቅ ስርዓትን ታበጅልሃለች።

በተቃራኒው ደግሞ እርሷ የትኛውንም ትምሕርት(መንፈሳዊም ኾነ ዓለማዊ) ብትማር ስሜቷን መግራት፣ መግዛትና ማሳረፍ ለሚችል ወንድ (ለምን ዱርዬ አይኾንም) ምድራዊውን(ሰው የሠራውን) አይደለም ሰማያዊውን(ከፈጣሪ የተሰጠንንም) ሕግ ከማፍረስ ወደ ኋላ አትልም።

ልብ አድርግ ግን ካንተ የሚያርቃት ወደ እርሱም የሚስባት ማዕበል ለኾነው ስሜቷ እረፍት መኾኑ እንጂ ዱርዬነቱን በቁሙ ወዳለት አይደለም፤ ከእርሱ ጋር መኖርም እንደማትችልም ልቧ ያውቀዋል።

ይኼን የእኔ ሚስት አታደርገውም ከእኔ በላይ አምናታለሁ( እነዚህ የምስኪንና የአልጫ መፈክር ናቸው) ማለቱን ተወውና ግዴታህን ተወጣ። ራስህን መግዛትና መምራት ተለማመድ ከዚያም ሚስትህን፣ ልጆችህን፣ ቤተክርስቲያንን እና ሀገርንም ጭምር እንጂ።

ግዴታህን መወጣት የተገባህ አንተ ወደብ ልትኾናት ሲገባ የስሜቷ ማዕበል በተናወጠ ቁጥር አንተም አብረህ የምትባክን ከኾነ በዚህ ውስጥ ለሚፈጠረውን ጥፋት በእርሷ ስንፍና እና በፈጣሪ ፈቃድ ላይ አታሳብ።

ሳተናው!
ልብ አድርግ ይኼን ጽሑፍ ሴትን ልጅ ትረዳበት ዘንድ የኃላፊነትህን ታላቅነት፣ ለምንስ እንደኾነ ትረዳው ዘንድ ጻፍኩልህ።

በማን መቃን ሥር ትኖራላችሁ?…. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *