ለወንዶቻችን አልጫ መኾን የመገናኛ ብዙኃን ሚና

ሳተናው!

የመገናኛ ብዙኃኖቻችን ተፈጥሮኣዊውን፣ ባሕላዊዉን፣ ታሪካዊውን የአባቶቻችንን ጀግንነት ቁንጽል በኾኑ ዘገባዎች ከማሰታወስ ባለፈ የዘመኑ ወጣት እንዴት ቢችል ልቆ ባይችል ግን በእነርሱ ልክ ወንድ ኾኖ መኖር እንደሚችል አያሳዩትም።

ይልቁንም ሀገርንና ዳር ድንበርን ያስጠበቀ፣ ኃይማኖትንና ባሕልን ያቆየ፣ ሕዝቧን ከባርነት ቋንቋዎቿንም ከመጥፋት የታደገውን የወንዶቿን ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ አትንኩኝ ባይነት ጊዜው ያለፈበት ነውጠኝነት ተደርጎ ሲኮነንና ሲወገዝ ይሰማል። ተማሩ በሚባሉት ልሂቃኖቻችን ጭምር ይኽን ወኔ ‘አምባገነንነት፣ ኋላቀርነት’ ብለው ሲፈረጁ መስማት እየተለመደ ነው።

እንደነዚያ ቀደምት አባቶች በአካል ብቃት ታጥቆ፣ በአእምሮኣዊ ብስለት ልቆና በመንፈሳዊነትም መጥቆ በመገኘት ቆራጥና ለዓላማ ጽኑ ኾኖ መኖር “ግትር” የሚያሰኝ ኾኗል። በተጨማሪም በቤት ሚስትንና ልጆችን በስነስርዓትና በስነምግባር መምራት/ማሳደግ “ኋላቀር” ያሰኛል። ስለሀገር፣ ስለወገንና ስለማንነት ተቆርቁሮ መሟገትማ የሚያስከስስ፣ የሚያሳስር አንዳንዴም የሚያስገድል ይኾናል።

ከዚህም የተነሳ ትውልድ እንደ እንሰሳ የሚበላና የሚጠጣ፣ የሚዋሰብም ያለ ዓላማና እቅድም በዋልፈሰስ በነዱት የሚፈስ ሲኾን ይታያል፤ ይኽ ደግሞ ላልተረዳው ዘመናዊ ባርነት የሚያዘጋጀው ከፈጣሪውም የሚያርቀው ስልታዊ የኾነ የአመንዝራዋ ዓለም ሴራ ነው።

ዐለም መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅማ የእግዚኣብሄርን ሕዝብ በተለይም ቤተሰቡን እንዲመራና እንዲጠብቅ፣ ትውልዱን በስነስርዓትና በስነምግባር እንዲያንጽ ኃላፊነት የተጣለበትን ወንድ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከታዋለች።

1ኛ የማንነት ቀውስ (ከእውቀት ማነስ የተነሳ የትውልድ መጥፋት)
2ኛ የስሜትና የመንፈሳዊ ሕይወት ቀውስ (ከተመናመነ መንፈሳዊነት የመጣ የስነምግባር ዝቅጠት)
3ኛ የአካል ብቃት ቀውስ (በስፖርት በሥራ ያልዳበረ ጡንቻ፣ መወፈር አልያም መኮሰስ )

1ኛ የማንነት ቀውስ

ወንዶች ልጆቻችን(አባት ነኝና እንዲህ አልኩ) በአኹኑ ጊዜ የማንነት ቀውስ ውስጥ ናቸው። “እንዴት?” ብትሉ በየመገናኛ ብዙኃኑ ወንዶች ለትዳራቸው፣ ለቤተሰባቸው፣ ለማሕበረሰባቸውና ለሀገራቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ከሴቶች ያልተለየ ተደርጎ ይቀርባልና ነው።

ይኽ በተለያዩ መርሃግብሮች የሚቀርበው ወንዶችን ከሴቶች ለይቶ ያለማየትና በአንድ (አንድ ናቸው በሚል) የመፈረጅ ሥራ ወንዶችን ለጾታዊ ማንነት ጥያቄና ግራ መጋባት ዳርጓቸዋል።

አስረጅ፦ “ወንዶች(አባቶች) እንደእናት የእርሷን ሥራ ካልሠሩ ልጆች ማሳደግ ምን እንደኾነ አያውቁም” ተብሎ በመገናኛ ብዙኃኖቻችን ልጅ ማዘል “ዘመናዊ አባትነት” እየተባለ ይቀርባል ያሸልማልም።
በዚህም ልጅ ማዘልን፣ ይኽንንም እንደ ጀብዱ ማውራት፣ ፎቶም ተነስቶ መለጠፍ የእናቶችን ጭንቀት፣ ድካም የ”መጋራት፣ የማገዝና የመረዳት” ተደርጎ ይወሰዳል።

“ወንድ ልጅ እንደሴቷ ከሴቷም ባልተለየ ሚና መገኘት አለበት” ማለት ወንዱ ላይ የጾታዊ ማንነት ቀውስ መፍጠር ነው። አንድ ወንድ(አባት) ልጆቹን ፈጣሪ እንደሰጠው ሚናና ኃላፊነት ቢያሳድግ ተገቢ ኾኖ ሳለ እንደእናት ካላሳደገ ሲባል ግን ተፈጥሮኣዊ ባሕሪውን የሚሞግት የሚያስትም ነው።

ይኽ ሳያነስ ደግሞ ወንዶች በተለይም አባቶች በተለያዩ “ኪነጥበባዊ” ውጤቶች ላይ በቤታቸው(በቤተሰባቸው) “ቀልደኛ፣ ፌዘኛ፣ ተረበኛ፣” ተደርገው ይቀረጻሉ። አልያም የቤተሰባቸው አባላት የሚያፌዝባቸው ከስልጣኔ የራቁ፣ ለዘመኑ ንግግርም ኾነ ጥበብ ባዕድ ተደርገው “የማዝናናት” ገጸ-ባሕርይ ይላበሳሉ።

የእነዚህ ድምር ውጤት ከኩምክና(ቀልድ) ውጪ የረባ ቁምነገርና ሚና የሌለው መጣ ቀረም ኖረ ሞተም ልዩነት የማያመጣ ማንነት ለዚህ ጾታ እንዲኖረው ያደርገዋል።

እስቲ የቤቱን ቅጥ የሚያሲዝ የስነስርዓትና ስነምግባር ልክ የኾነ ደረጃውንም የሚያስቀምጥ ይኼንንም ከሚስቱና ከልጆቹ የሚጠብቅ እርሱንም ካጣባቸው ደግሞ የሚሚክር የሚቀጣም አባት በመገናኛ ብዙኃኑ ሲቀርብ ታዝባችኋል? ይልቁንስ እንደዚህ ዐይነቱ አባት “አካባጅ፣ ስልጣኔ ያልገባው፣ ዘመናዊነት ያልደረሰበት፣ የድሮ ስርዓት ናፋቂ አምባገነን” ይባላል እንጂ።

ማስታወሻ፦ ሳተናው! በቤትህ ውስጥ አንተና ሚስትህ እንደአፈጣጠራችሁ ኹሉ ሚናችሁም ኾነ ኃላፊነታችሁ ፍጹም ለየቅል ነው።

2 የመንፈሳዊ ሕይወትና የስሜት ቀውስ(ጉስቁልና)

ሰው በሕይወቱ ምክንያታዊ(logical) ብቻ ሳይኾን ስሜታዊ(emotional) ጭምር ነው። ይኹን እንጂ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ስሜታዊ(ለውሳኔና ለምርጫ ከአመክንዮ ይልቅ ስሜታቸውን የሚያደምጡና እርሱንም የሚያምኑ) ናቸው ።

ይኽ በእንዲህ እያለ ግን የመገናኛ ብዙኃን አኹን አኹን ወንዱን ቆሞ ከማመዛዘን ይልቅ ለስሜቱ ያደላ ቆዳ ስስ፣ ውሳኔም የሚፈራ አልጫ፣ ስነልቦናዊም ኾነ አካላዊ አቋም የሌለው ልፍስፍስ፣ አፈቀርኩ ብሎም የሚያላዝን ምስኪን እያደረጉት ያቀርባሉ። ይኽንንም “በኪነጥበብ” ውጤቶቻቸው(sitcom drama, stand-up comedy ዘፈኖቻቸው)እና በዜናዎቻቸው ይፈጽሙታል።

በመንፈሳዊ ሕይወቱም ቢኾን ራሱን የሚያይበትን፣ ፈጣሪውን የሚረዳበትንና ስለመጪውም ዐዲስ ሕይወት በመመርመርና ፈጣሪው በፈጠረውና በሚጠብቀውም ልክ በምግባርና በስርዓት ከመኖር ይልቅ ስጋዊ ስሜቶቹን ብቻ እየተከተለ የሚነጉድ ኾኗል። በዚህ ረገድም እነኚው መገናኛ ብዙኃን የስነምግባርና የኑሮ ስርዓት መመሪያ ከሰጠው ፈጣሪ ውጪ አብላጫ ድምፅና ጭብጨባ ላለው ኃሳብ እያደሉ ትውልዱ ማወቅና መኖር ያለበትን ሳይኾን መስማት የሚፈልገውንና የእነርሱንም ጥቅም የጠበቀውን በማቅረብ ከድጡ ወደማጡ ይገፉታል።

መንግስትም ቢኾን የትውልዱን ስነልቦና የሚሰልቡ pornographic ይዘት ያላቸውን መረጃዎች ከሕትመትም ኾነ ከስርጭት(የኢንተርኔቱን ጨምሮ)ከማጥፋትና ትውልዱን ከሞራል ዝቅጠት ከመታደግ ይልቅ ነጻ ሚዲያውን ተጠቅመው የእርሱን ስርዓት የወቀሱትን ማሳደድና ማገድ ላይ ሲጠመድ ይስተዋላል።

ከዚህም የተነሳ በመንፈሳዊ ልምምዶቹ በቅዱሳት መጽሓፍት ንባባት፣ በአጿማት፣ በጸሎታት (በምስጋና) በቀላሉ ከሚያገኛቸውና ሕይወቱን በሐሴት ከሚሞሉ ኃብታት ትውልዱ ይርቃል።

3ኛ የአካል ብቃት ቀውስ

ከኑሮ ዘይቤ ለውጥ ጋር ተያይዞ ወንዶቻችን በተፈጥሮ ከተቸርነው አቋም በጣም በወረደ የአካል ብቃት ላይ ይገኛሉ። ወንድ ልጅ በተፈጥሮው ከሴቷ ይልቅ ከደረቱ ሰፋ ከወደ ቂጡ ጠበብ የተደረገበት እርሷም ከዳሌዋ ሰፋ ከደረቷ ጠበብ የተደረገችበት ምክንያት አለው።

ውሎኣችን(ሥራችን)ይኽንን ተፈጥሮኣዊ ቅርጽና ከእርሱም ጋር ያሉትን ጡንቻዎች የማያዳብርልን ቢኾን እንኳ ኾን ብለን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልንሠራ ይገባናል። ዛሬ ዛሬ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የምናያቸው ወንዶች እንደሴቶቹ ቁንጅናቸውን የሚጠብቁ የወንድ ተክለሰውነት የማይታይባቸው ናቸው። አልያም አባት ለመባል ቦርጫቸው የተለጠጠ ቆፍጣናነትና ንቁነት የጎደላቸውን እናያለን።

በመገናኛ ብዙኃኑ የሚተላለፉትም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጭፈራ አይሏቸው ዳንኪራ ለወንዱ ጡንቻ ምንም ፋይዳ የሌላቸው ለታይታ የኾኑ በስፖርት ተሳበው የጭፈራ አምሮታቸውን ለሚወጡት ቢኾን እንጂ ወንዱን ፈረጣማና ጠንካራ ማድረግ አይቻላቸውም።

ማጠቃልያ ፡ ወንዶቻችንን ለማልፈስፈስ የመገናኛ ብዙሃን ተጽዕኖ ትልቁን ሚና ይጫወታል። ክተሳሳቱ መረጃዎች ጀምሮ በ”ኪነ ጥበብ” ስም ሆን ተብለው እስከሚቀርቡ ውሸቶች ድረስ አሉታዊና ኢተፈጥሮኣዊ ይዘታቸው የጎላ ነው።

መፍትሔው፡ አጠቃቀምህን በጣም መቀነስ ነው። አካልህን በስፖርት አዳብር መጽሓፍትን በማንበብ የእውቀት አድማስህን አስፋ መንፈሳዊ ተመስጦዎችን(meditations) እና ልምምዶችን ገንዘብ በማድርግ የሞራል ልዕልናህን ጠብቅ።

ከዚህ በታች ያስቀመጥኩልህ ተፈጥሮኣዊ የአባትነት፣ የባልነት፣ የወንድነትና የመሪነት አርኣያ አጥተው ያደጉ በሀገራቸው ካለው የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ሥርም የወደቁ ወንዶችን ፎቶ ነው።

ሳተናው! ልብ አድርግ ዛሬ ራስህን (በአካል ብቃት፣ በአእምሮ እውቀትና በመንፈሳዊ ልቀት) የምታንጸው ለራስህ ብቻ ሳይኾን ነገ ለሚወለደው ልጅህም ብቃት ኃላፊነት ከሚሰማው አባትነትህ ጤናማና ተፈጥሮውን የጠበቀ ዘረ መል(DNA) ለማውረስም እንጂ፤ ምንም እንኳ ምርጫውና ውሳኔው ያንተ ቢኾንም።

ዓላማ መስቀል ቆራጥነት ጽናት ታታሪነት ካሰቡት መድረስ ድንቅ መስራት መለያቸው የነበሩትን አባቶችህን አስብና ይህን ጠባያቸውን ለመውረስ ትጋ ፈለጋቸውን ተከተል ልማድህም አድርግው። ይህን ለማድረግ ከሶፋ ላይ መነሳት ቴሌቪዥንሀን ማጥፋት ስልክህን/ፌስቡክህን ማስቀመጥ ሰበባሰበቦችህን መተው … ግድ ይልሃል።

መልመጃ 1 የነገ የአንድ ቀን የአካል ብቃት ግብ
ዓላማ በአስራ ሁለት ሰዓት ውስጥ 1000 push-up መስራት(ከዚህ በፊት ያልሞከርኩት) መቼ እኹድ ግንቦት 04 2011 ዓ.ም. ቆራጥነት አደርገዋልሁ እችለዋለሁ

ሳተናው!.… … ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *