ለድካምህ ሰበብ ሳታበዛ ኃላፊነቱን ውሰድ

 

ወደ አባወራነት የምታደርገው ጉዞ ዛሬ ቢጀምር እንጂ አንተ በሕይወት እስካለህ ድረስ ማብቂያ የለውም። ለሚስትህ ለልጆችህ ለትውልድ ለሀገርህ ኃላፊነት ተሰምቶህ ከሰበበኛነትም ርቀህ ለውጥን ስትሻ ከራስህ ትጀምራለህ።

ሀገርህ እስክትለወጥ፣ መንፈሳዊ አገልግሎቶች እስኪጠሩ (ከሚሰማባቸው ሕጸጽ) ፣ ልጆችህ ራሳቸውን እስኪችሉ፣ ትዳርህ እንደምትፈልገው እስኪኾን፣ ያንተም ገቢ እስኪሻሻል መጠበቅ የለብህም። በተሰጠህና ባለህ በምትችለው ኹሉ ራስህን አሻሽል።

ጀግናው ወንድሜ
ወደ አባወራነት የምታደርገው ጉዞ በተለይም በዚህ ባለህበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እንደመገኘትህ ከባድ ነው። በዚህ ባለንበት ጊዜ ተፈጥሮአዊውና ባሕላዊው ወንድነት በራሱ እብደት (የአእምሮ መቃወስ)፣ አምባገነንነት፣ ዱርዬነት፣ ራስወዳድነት፣ በሚሉ አሉታዊ ቃላት ይጠቃል።

ከዚህም የተነሳ ትውልዱ(ወንዱ ትውልድ) የወንድነት ጠባይ ትቶ በሴትና በወንድ መካከል መሐል ሰፋሪ መኾንን መርጧል።

አንተ ግን ወንድሜ ተፈጥሮህን ተረዳ እርሱንም ኮትኩተህ ተንከባክበህ አበልጽገው። የተፈጠርክበትን ምክንያት ተረድተህ ለተፈጠርክበት ዓላማ፣ በተፈጠርክበት ልክ እንዲሁም በተሰጠህ ጸጋ በልዕልና መኖሮ የምትችለው ተፈጥሮህን ስታውቅ፣ ስትንከባከብና ስታበለጽግ ነው።

በጉዞህ ሰበበኛነትን ጥለህ ኃላፊነትን አንጠንጥል። ይህ ማለት ባጭሩ ምስኪንነትህን ጣልና በወኔ ተነስ። ምስኪን በምንም መስፈርት አባወራ አይኾንምና።

ምስኪን ሰበበኛ ነው፦ አንድም በቃላት አሽሞንሙኖ፣ በሰውነቱ ተቅለስልሶ በድምጹ ተሰላችቶ(አሳዝኖ) የማድረጉ ፍላጎት እንዳለው፣ እንደሚወድ፣ ቢኾንም ደስ እንደሚለው ነገር ግን ማድረግ ያልቻለበትን ምክንያት ዘርዝሮ አይጨርሰውም።

አንድም ምስኪን ሰበበኛ ነው፦ “እኔው ራሴ በገዛ ፈቃዴና ስልጣኔ አደረግኩት” ቢል ሰዎች ይጠሉኛል፣ ወዳጆቼ ይሸሹኛል፣ ጥላዬ ይከዳኛል ውቃቢ ይርቀኛል ሲል ይፈራልና ነው።

ጀግናው ወንድሜ
አንተ ግን “ሰው እንዳይከፋብኝ” ብለህ ብዙ የግዴታ ውሎች ውስጥ አትግባ። የገባኸውንም ቃል ሰበብ ፍለጋ ግራ ቀኙን ሳታማትር ፈጽም። ማድረጉን ካልቻልክም በአጭር ቃል፣ በተረዳ አንደበት፣ አስረግጠህ “ይቅርታ አልቻልኩም” በል። በዚህ ሰዎች አንተን ቃል ማስገባት በውልም ማሠር ከባድ፤ ነገር ግን ቃል ገብተህ በውል ታስረህ ብትገኝ ፈጻሚነትህ የማያጠራጥር እምነትም የሚጣልብህ ቁምነገረኛ ያደርጉሃል።

ለራስህ ስንፍና ኃላፊነት ስትወስድ ራስህን ለመለወጥ የሚያስፈልግህን ቅድመ ዝግጅት ጨረስክ ማለት ነው። ነገር ግን ዛሬም ስንፍናዎችህን በተራቀቁና በቃላት በተከሸኑ ሰበብ አስባቦች የምታሰማምራቸው ከኾነ የምን ትዳር፣ ሚስት፣ ልጆች መምራት ነው ራስህን ማስተዳደር ያልቻልክ ብኩን መኾንህ እኮ ነው!

ቀላል ምሳሌ ልስጥህ ዛሬም በቀጠሮ ሰዓት መገኘት ተስኖህ ሰበብ የምትደረድር ከኾነ፣ ራስህን በሥስቱ መሰኮች(በአእምሮ፣ በአካል ብቃት፣ በመንፈሳዊ ሕይወት) ማሻሻሉን ትተህ ሰበቦችን የምታሰልፍ ከኾነ፣ ዛሬም ከሱስ ለመውጣት(የFB፣ የTV፣ …) ለምክኒያቶችህ ኁልቁ መሣፍርት ሲታጣ …. ምናለፋህ ሰበብ ይቅርብህ።

ለዚህ ደግሞ መፍትሔው አንድና አንድ ነው። እርሱም ውጤቱ ምንም ይኹን ምን ለንግግርህ “እኔ አልኩ”፣ ለሥራህም “እኔ ሠራሁ” በማለት ኃላፊነቱን መውሰድ። ኃላፊነት የምትወስድ ለሥራህም ተጠያቂነትን የማትፈራ ሲኾን አስበህና አቅደህ በጥንቃቄ ትናገራለህ ታደርጋለህም።

ይኽ ደግሞ ከሚስትህ ጋር ለሚኖርህ ግንኙነት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ካወቅህበት ትዳራችሁን ወደ ደስታ ከፍታ ማምጠቅ የሚችል አዎንታዊ ሚና ካላወቅህበት ደግሞ የትዳሩን ድክመትና ውርደት ኹሉ የምትሸከምበት አሉታዊ ሚና ይኖረዋል። “እንዴት?” ነው ያልከኝ አየህ ሚስትህ..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...