መሪነትህ ከዐላማህ ሲመነጭ ሚስትህ ትከተልሃለች

ዐላማህ የተፈጠርክበት ምክንያት፣ልታሳካው ያለህ ሕልም(ርዕይ) ነው እንጂ ሴት አይደለችም።
ያንተ የኑሮህ ዓላማ የተፈጠርክበት ወደ እዚህችም ምድር የመጣህበት ምክንያት ነው።ትዝ ይልሃል ጥንት ወደዚህ ምድር ስትመጣ፤ ይኼን፣ ይኼን፣ ሥራ(አብጃት፣ጠብቃት) መባልህን። አዎን ሥራ ከተባልክ በኋላ ነው አጋዥ የተሰጠህ።
ወንድሜ የመኖርህ ምክንያት የታዘዝከው ሥራ አልያም ሕልምህ እንጂ አጋዥህ አይደለችም።ይኽንን ተፈጥሮኣዊ እና መሠረታዊ እውነት አትዘንጋ። የመኖርህ፣ በምድር ላይ የመመላለስህ ምክንያት እርሱ ነው።ዛሬ ላይም በዚህች ምድር ስትኖር ያንተ ድርሻ ምን እንደሆነ የተፈጠርክበትን ምክንያት፣ ልታሳካው ያሰብከውን ሕልምም ምንጊዜም በኑሮህ ቅድሚያ ስጣቸው።

ይህ በተፈጥሮ አንተ ውስጥ የተተከለ ተልዕኮህ ነው። ለዚህም ነው ወንድ ልጅ ራስን በመቻል ጉዞ ታግሎ የሚያሸንፈውን፣ ደክሞ የሚያሳካውን፣ አካባቢውን የሚቀይረውን ሥራ የሚፈልገው። በዚህም ሥራ ከሌሎች ልቆ መገኘትን ጥንካሬና ጥረቱን እንዲሁም እውቀቱን ተጠቅሞ ነጥሮ መውጣትን ይሻልና ዘወትር ይሠራል። ለዚህም ነው ለዓላማው ስኬት ለሕልሙ እውን መኾን በሚያደርገው ሩጫ ውስጥ ባሉት መዝናኛዎችም ውድድርነት ያላቸውን እና ተቃራኒን በመርታት ድልን የሚያጎናጽፉትን የሚመርጠው።

ወንድሜ በዚህች ምድር ስትኖር የምትኖርለት ዓላማ ወደ እዚያ ዐላማ የሚወስድህንም አቅጣጫ ግልጽ አድርገህ አስቀምጥ። ይህን ስታደርግ ብቻ ሴት ልጅ ከስሜታዊ እና ጊዜያዊ ፍቅር ወጥታ አክብሮትን ትቸርሃለች። ልብ አድርግ! ወደድኩህ ከነፍኩልህ ከምትልህ ሴት ልጅ ይልቅ አንተንና ሕልምህን ወይም ዓላማህን የምታከብረዋ ትልቅ አጋዥህ ናት።

ሴት ልጅ የኑሮ ደህንነትን ካንተ ትፈልጋለች(ገንዘብ፣ ዝና፣ ስልጣን አይደለም)። እርሷ ምን ገንዘብ ቢኖራት፣ ምን የተማረች ብትሆን፣ ከወንድ የምታገኘውን የተረጋጋና ጥርት ብሎ የተቀየሰን ዓላማ አይተካላትም። ስለዚህ እርሷን መከተሉን ተወውና ወደ ዐላማህ ተዘርጋ።

አንተ የጠራ አካሄድ የተሰቀለም ዐላማ ሲኖርህ የሕይወትህ አካል መኾንን ትሻለች። እርሷን መውደድህ፣ አባወራነትህ፣ የልጆቿ አባት መኾንህ ሁሉ በዋናው ዓላማህ ሥር የሚገቡ ቁምነገሮችህ እንደኾኑ ታውቃለች። ይህ ሁሉ በአጋጣሚ ሳይኾን ዐቅደህ የገባህበት መኾኑን ስታውቅ ላንተ ያላት አክብሮት ይጨምራል።
ነገር ግን ወንድሜ! በጭራሽ! ደግሜ በጭራሽ! እልሃለሁ የተፈጠርክበትን ዐላማ የሕይወትህን ሕልም(ራዕይ) ለሴት ብለህ አትርሳ(አትተው)። ተፈጥሮህም አይደለምና አያሳርፍህም፤ በቤትህም እርሷ ለጊዜው ወደድኩህ ብትልህ በኋላ ግን ዐላማህን የሳትክ የምትሄድበትን የማታውቅ መኾንህን ስትረዳ ትንቅሃለች። በውጪም ለሃይማኖትህ፣ ለወገንህ፣ ለሃገርህ የማትበጅ ትኾናለህ።
ስንቶች ለሴት ፍቅር ብለው ከተፈጠሩለት ዐላማ፣ ከተሰጣቸው ኃላፊነት፣ ከልጅነት ሕልማቸውም ተሰደዱ ፣ አጋዥ ተብሎ የተሰጠቻቸውን ዐላማ አደረጉ፤ ምንኛ ስሑት ናቸው?

ወንድሜ ጥንካሬህን ከመሸርሸር፣ አቅጣጫህን ከማሳት፣ ዐላማህን(ሕልምህን) ከማስረሳት ውጪ ፋይዳ በሌላቸው ጉዳዮች ጊዜህን አታጥፋ። በስመ ኪነ-ጥበብ ወይም ስነ-ጥበብ ውጤቶች ወይም ተራ ጊዜያዊ ፍላጎቶች(ጨዋታዎች) ተደልለህ ከመንገድ እንዳትቀር።
አባቶቻችን ጥርት ያለ የኑሮ አቅጣጫ፣ ዐላማ እና ሕልምም ስለነበራቸው ነው፤ ሃይማኖታችንን፣ አንድነታችንን፣ሀገራችንን ያቆዩልን። ሚስቶቻቸውን የሚወዱ ለነገ ትውልድ የሚያስቡ የተሰጣቸው አደራና ሕልማቸው ግድ ብሏቸው እንጂ። ሚስቶቻቸውን መውደዳቸው ለዓላማቸው እንዲኖሩ ለሕልማቸው እንዲሞቱ አደረጋቸው እንጂ መንገድ አላሳታቸውም ሕልማቸውንም አላጨናገፈባቸውም።

ሴት ልጅ ተወዳጅ ናት፣ ተፈቃሪ ናት። አንተም ሴትን ልጅ(የምትወዳትን፣ ሚስትህን) ማስደሰት ደስታህ ይኹን። ሚስትህን በማስደሰት ከምታገኘው ደስታ ውጪ ራስወዳድነት የተጠናወተው ከእርሷ የምትወስደው ደስታ ካንተ ይራቅ። ይህም ሁሉ የ”አባቷን ልጅ” ስታገኝ አንተም አባወራ ስትኾን ይፈጸማል። …..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *