ሚስትህ ጥበቃ ትሻለችን?

ሳተናው!

ለወንድ ልጅ በመሠረተው ትዳር ሚስቱ ለኑሮ የሚያስፈልጋትን (አስቤዛ) ማቅረብ፣ ከማንኛውም አደጋ መጠበቅ እና ትውልድን ተክተው ያልፉ ዘንድ ዘርን መስጠት ተፈጥሮኣዊ ግዴታው ነው።

ከእነዚህ ሦስቱ ኃላፊነቶቹ ታዲያ በተለይ የመጀመሪያው (ለቤቱ የሚያስፈልገውን አስቤዛ ማቅረብ) ሴቶች ከቤት ውጪ ሠርተው ገንዘብም አግኝተው በሚገቡበት በዚህ ዘመን እርሷም የምትጋራው ኾኗል።

ሦስተኛው፦ ዘርን መስጠቱ ምንም የማያሻማ የእርሱና የእርሱ ግዴታ ሲኾን፤ ሁለተኛው፦ እርሷን መጠበቅ ግን ትንሽ ግር ሳያሰኝ አይቀርም። የዛሬው ጦማር በዚህ በሁለተኛው ላይ ያጠነጥናል።

ወንድ ልጅ ሴትን ወይም ባል ሚስቱን ይጠብቃታል ሲባል “ከምን ከምን ይጠብቃታል?” የሚለው ጥያቄ ወደ አእምሮህ ቢመጣ ተገቢ ነው። ብዙ ወንዶችን ይኼን ጥያቄ ብትጠይቋቸው የአብዛኞቹ መልስ “ከዱሩዬ፣ ከሌባ፣ ከአውሬ፣ …ወዘተርፈ” ይኾናል።

እኔ ግን ዛሬ ልነግርህ የፈለግኩት ከዚህ የተለየ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋትም ጭምር እንጂ እርሱም ሚስትህ በውሳኔዋ ራሷን፣ ቤቷን እና ልጆቿን እንዳትጎዳ ልትጠብቃት እንዲገባ ነው።

ሳተናው!
“ዘመናዊ” ትምሕርት ስትማርና “ሰልጥኛለሁ” ብለህ ስታስብ ግን ይኼንን ጥበቃ “ጭቆና” ብለህ መተርጎም ትጀምራለህ። ይኹን እንጂ ሚስትህ ምን የተማረች(ማስትሬት፣ዶክትሬት ቢኖራት)፣ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የደረሰች(ኢታማዦር ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር) ፣ አልያም እድሜዋም ኾነ ገንዘቧ ከፍ ብሎ ብታገኘው እንኳ በትዳርህ ውስጥ ግን እርሷ ከምትወስናቸው ውሳኔዎች የተነሳ እንዳትጎዳ ልትጠብቃት ይገባል።

ይኹን እንጂ ምስኪን በስልጣኔ ተደልሎ፣ በእኩልነት ተታሎ፣ በ”ፍቅርም” ልቡ ጠፍቶ፣ የሚያስከትለውንም መዘዝ ፈርቶ ይኽንን መታደግ “መታደግ” ብሎ አይቆጥረውም። ሴታውሉ ደግሞ የሚተኛቸው ሴቶች ከቁጥር እንዳይጎሉበት ይፈልጋልና ለሴቶቹ የተቆረቆረ መስሎ ይኽንን ትድግና “ሴቶችንና ኃሳባቸውን መናቅ ነው” እያለ በከፍተኛ ሁኔታ ይተቻል።

ስለ ሴት ልጅ ባሕርይ ስንወያይ ግን ስሜታዊ እንደኾነች፣ ይኽም ስሜት ሞገድ ኾኖ (በቀን፣ በሳምንት..) ውስጥ በተደጋጋሚ ውሳኔዎቿ እንደሚለዋወጡ እንረዳለን። ነገር ግን ለዚህ በምርጫዎችና በውሳኔዎች መካከልም ለሚዋዥቀው ሞገድ ስሜቷ ወደብ የሚኾን እንዲሁም በዚህ ሞገድ ውስጥ ትዳሩን በጥበብ የሚመራ አባወራን ትሻለች።

ወንድምዓለም! ይኼንን ጥበቃ ቀድመን ከዘረዘርናቸውና ከመሰሎቻቸው ጥበቃዎች ለየት የሚያደርገው አንድ ዋነኛ ነጥብ አለ ። እርሱም፦ በቀደሙት ጥበቃዎችህ አንተ የተጋረጠባትን አደጋ ፊት ለፊት ስትጋፈጥ እርሷ ደግሞ ከደፈረች ከጎንህ ከፈራች ግን ከኋላህ ስትኾን በዚህኛው ግን ከሚጎዳት ውሳኔ ጎን በመቆም አንተን ፊትለፊት ትጋፈጥሃለች።

ቢኾንም ግን ስሜቶቿ ሳይረብሹህ፣ ማዕበሉም ሳያሰምጥህ ውሳኔዎቿን ገምግም። መንፈሳዊም ኾነ ዓለማዊ እውቀት አላት ብለህ ለብቻዋ አትተዋት። ምን “የተማረች ነች”ም ብትል አንድ ጊዜ-የሰጠው መናፍስት ጠሪ አልያም የኃይማኖት አጭበርባሪ ያታልላታልና(አዋቂ፣ ነቢይም ነን ባዮች ስንት ዶ/ሮችን አስከተሉ?)፤ ምን “ብልህና አስተዋይ ነች” ብትል እባብን የመሠለ “ለስላሳ” ነገር ግን መሠሪ ዓላማዋን ያስታታልና(ሴታውል ይተኛታልና) ነው።

ሳተናው!
ለሚስትህ ከምታደርጋቸው ጥበቃዎች ሁሉ ይኼ መጨረሻ ላይ የጠቀስኩልህ ቁርጥ ውሳኔን፣ ጽኑ ልምምድን እና ትልቅ መስዋዕትነትንም ካንተ ይፈልጋል። ብዙዎቻችን ወንዶች ሚስቶቻችንን ከሚጎዳቸው ነገር ለመጠበቅ እንሞክራለን አልፈን ተርፈንም ያንጓጠጣቸውን፣ የሰደባቸውን፣ የመታቸውን፣ ያስፈራራቸውን ለመበቀል እንጋበዛለን።

ይኹን እንጂ የሚስቶቻችንን ውሳኔዎች መዝነን ቀሎ ስናገኘው ሊጎዳቸው እንደሚችል፣ በዚህም እነርሱ ብቻ ሳይኾኑ ትዳሩ፣ ትውልዱና ሀገርም ተበዳይ እንደሚኾኑ አስረድተን ስንታደጋቸው አንታይም። ይኽንን የሚስትህን የትዳርህን የቤተሰብህን ጥበቃ መንግስት፣ ፍርድ ቤት አልያም ፖሊስ ቢያፈርሱልህ እንጂ “ይሠሩልኛል” ብለህ አትጠብቅ።

ነገር ግን ላንተ አካልህ ናትና ጥበቃህ(ትድግናህ) በግዘፍ ከሚታየውና ከሚዳሰሰው በተጨማሪ ከማይታየውና ረቂቅ ከኾነው ጎጂ ኃሳቧም ጭምር ሊኾን ይገባሃል። ይኽን የምታደርገው ግን ካለእርሷ መኖር የማትችል ደካማ ስለኾንክ ሳይኾን ትዳርህን በዓላማ የምትመራ መድረሻ ርዕይም ያለክ አ..ባ..ወ..ራ ስለኾንክ እንጂ!

…. ይቆየን!

ቴሌግራም
https://t.me/abawera

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *