ምስኪን-ባሎች ፈቃድን መፈለጋቸውና መጨረሻቸውን ማክፋቱ

አንተ ምስኪን ሆነህ ለምትሠራው ሥራ ሁሉ ፈቃድንም ሆነ አድናቆትን ከሚስትህ የምትሻ ከሆነ፦
1ኛ በራስ መተማመንህ ደካማ ነው ወይም ይሆናል ማለት ነው። ይህም ሥራህን በራስህ እውቀትና ችሎታ የመገምገምና የመመዘን ደረጃውንም የመወሰን ችግር እንዳለብህ ያሳያል።
2ኛ ለሚስትህ ባንተ እና በእርሷ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያልተገባ ሥልጣን ትሰጣታለህ
3ኛ ከፍተኛ የሆነ ቁጣን እና ንዴትን ውስጥህ ታከማቻለህ
እስኪ ቀስ እያልን እነዚህን እንያቸው
1ኛ በራስመተማመንን በተመለከተ
አንተ የምትሠራውን ሥራ አውቀህና ተገብቶህ ሥራ እንጂ ከሚስትህ ትክክለኛነትን ሽተህ ወይም ገና ለገና ደስ ያሰኛታል ብለህ መሆን የለበትም። ይህ ድርጊት አንተ በራስህ እውቀት እና ግንዛቤ ላይ የመጽናትህ ማሳያነው። ይህም ጽናት ላንተ ብቻ ሳይሆን ለሚስትህም ጭምር እንጂ ነው። ያንተ በራስ የመተማመንህ ድጋፍነት ወዳንተ የሚስባት አንተንም የሚሠራውን የሚያውቅ ተወዳጅ ወንዳወንድ ያደርግሃል። ልብ አድርግ አንተ ሥራን የምትሠራው እንዲህ ለመባል አይደለም። አንተ እንደዚህ ስለሆንክ እንጂ።
2ኛ ለሚስትህ ባንተ እና በእርሷ መካከል ያልተገባ ሥልጣን ትሰጣለህ፦ ለድርጊቶችህ ትክክለኛነት የእርሷን ይሁንታ የምትሻ ከሆነ በውስጣዊነት ሥልጣንን እየሰጠሃት ነው። በእያንዳንዱ ውሳኔህም ሆነ ድርጊትህ ላይ ታዲያ እንዴት “እኔ ሳልመከር ተወሰነ ወይም ተደረገ ” የሚል ስህተት ላይ ትወድቃለች። በዚህም ምክንያት ሁልጊዜ የእርሷን አስተያየት የምትጠብቅ ፊቷንም የምታይ ሲከፋት የሚከፋህ፣ ስትደሰት የምትደሰት፣ ሲታኮርፍ የሚጨንቅሀ ስታለቅስ የምትረበሽ ትሆናለህ። ይህ ደግሞ ለሌላ ለከፋ ስህተት ይዳርግሃል እርሱም የእርሷን ስሜት ማዕከል ያደረገ ሕይወት መኖር። ታዲያ ውሳኔህም ሆነ ድርጊትህ በዕውቀት እና በአመክንዮ የተደገፈ ከመሆን ይልቅ የእርሷን ተለዋዋጭ ስሜት ያማከለ ይሆንና ስሜቷን ማዕከል ያደረግክላት ሚስትህ እንኳ በውጤቱ በፍጹም ደስተኛ አትሆንም።አንተ እርሷን ደስ ለማሰኘት ስትጥር እርሷ ግን ሳይመስላት፣ አንተም የበለጠ ስትጥር እርሷም የበለጠ ሳይመስላት ብዙ ዘመን ይሆናል(ይህ ዋነኛ የምስኪኖች መለያ ጠባይ ነው)። ይህ ሥልጣን ውሎ አድሮ ያንተን ድርጊት ከእልፍኝ እስከ መኝታ ቤት የሚያነሳ እና የሚጥል ይሆንና ያንተን በራስህ ዕውቀት ላይ የመደገፍ ተፈጥሮህን ይሸረሽራል፤ ይህንንም ዕውቀት የመኮትኮትና የማሳደግ ፍላጎትህም ይቀንሳል። ከዚህ በኋላማ አንተ ለወቀሳ እና ለክስ ተላልፈህ የተሰጠህ ሁሌም የምትማረርብህ ሆነህ ታርፋለህ።
3ኛ ከፍተኛ ቁጣንና ንዴትን ታከማቻለህ በዚህም ቢያንስ ደም ግፊትና የልብ ውጋት(stroke) ይወዳጁሃል በተለይ የወንድ በሽታ መሆናቸው ሳትዘነጋ።
ምስኪን-ባል(ወንድ) ምንም እንኳ ሴቶቹ የሚወዱት እርሱም የሚወዳቸው(በአፍ፣ ላይ ላዩን) ቢሆንም እንደርሱ ድካምና ፍላጎት አድናቆትና ፈቃድ ፈላጊነት ውጤታማ ስለማይሆን ከፍተኛ ቁጣንና ንዴትን በውስጡ ያጠራቅማል። ለዚህም ነው በምስኪንነታቸው ተወዳጅ ናቸው የሚባሉ ባሎችን ጠጋ ብላችሁ ስለትዳራቸው ስትጠይቁ “አይ….ይይ ሴቶች” ብለው ከብዙዎቹ ተከድኖ ይብሰል መልስ የምታገኙት። ይሁንና እኛ ሰዎች ይህን ራሳችንን ሆነን ልንቀርፈው ይቻለን የነበረው ካቅማችን በላይ እስኪሆን እንጠብቅና ለፈጣሪያችን እንተወዋለን። የፈጣሪ መልስ ደግሞ እኛ ባሰብነው እና ባቀድነው ሳይሆን በራሱ የጊዜ ሰሌዳ እርሱ እንደፈቀደ ይፈጸማልና የዘገየ ሲመስለን የሚከተሉትን ሁለት እና ሁለት ብቻ መተንፈሻ መንገዶች እንጠቀማለን። እነርሱም አንደኛው ተአምራዊ የሆነው መለኮታዊው ኃይል አንድ ቀን ሁሉንም ይለውጣል ብሎ አንገትን ደፍቶ እስከ መጨረሻው መቀጠል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያ ሲጠራቀም ፣ እንደገሞራ እሳት ውስጡ ሲማሰል የቆየውን ብሶት ፍጹም እርሱነቱ እስኪያጠራጥር ድረስ አንድቀን ገንፍሎ ይወጣና አይጣል ያሰኛል። እርሷም ይሄን ተሸክሜአለሁ ስትል ለሽማግሌም ሆነ ለፍትህ አካላት ታቀርባለች በዚህም ተቀባይነት አግኝታ እርሱ ይኮነናል።

እነዚህ ሁለቱም የመተንፈሻ መንገዶች ጤናማ ትዳርንም ሆነ ደስተኛ ቤተሰብን ለማትረፍ የማይመከሩና ፈጽሞም ስህተት የሆኑ ናቸው።በአንደኛው መፍትሔ ባል ወንድነቱ ተገፎ ለልጆቹ ፈሪ እና የፈሪ አርአያን ይዞ በቤታቸው ለሚፈጠር ችግር ሁሉ ተጠያቂ ተደርጎ ለልጆች ይታያል። የቤቱ ታታሪ የቤቱ ምሶሶ እናት ብቻ እንደሆነች ተደርጎ ይነገራል ዛሬ ብዙዎቻችን የአባትን ውለታ እረስተን በዕውቀት አልቦ ጩኸት እናት እናት ብቻ የሚያሰኘን አባዜ ከዚህ የመነጨ ነው።እውነት እንነጋገር ከተባለ ዛሬ ዛሬ እኮ ባል እንደ አውራ ንብ እየተቆጠረ በመንፈስም ሆነ ጭርሱን በአካል ከቤት እየወጣ መሆኑን እየታዘብን ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ደግሞ ያ ምስኪን-ባል በወቅቱ የተሠጠውን ሥልጣን በአግባቡ ተጠቅሞ ንዴቱን ባለማብረዱ ወደ ሁለተኛው እና ወደ ማይቀረው መፍትሄ ወስዶት ከቤት የመውጣቱ ነገር በፍትህ አካላት ውሳኔ ይጸናል። ከዛም ለልጆች እናት ብቻ ጨዋ፣ አሳቢ፣ ተቆርቋሪ፣ አፍቃሪ አባትማ ምስኪን ምንም መወሰን የማይችል ሁሉን እሺ ባይ ሸክምን ኃላፊነትን ሁሉ ለእናት የሰጠ ግድየለሽ አልያም ጬኸታም ሚስቱ ላይ የሚያንባርቅ ተማቺ የመኖሩ ትርጉም ግልጽ ያልሆነ ይሆንና ልጆች ደርሰው ለእናት ተቆርቁረው አባታቸውን ወይ እነርሱ አልያም በሕግ አካላት የሚያስወጡበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።……………………ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *