ምስኪን-ወንድ ግጭትን ይሸሻል

ምስኪን-ወንድ ወይም ምስኪን-ባል ከላይ በተራ ቁጥር አንድ ካስቀመጥነው(በሁሉ ልወደድ ባይነቱ) የተነሳ ከማንም ጋር ላለመጋጨት የሚያሳየው ፀባይ በተለይ ከሚስቱ ጋር ባለው ሕይወት በብዙ እጥፍ ጎልቶ ይታያል። እስቲ በቤተሰቦቻችሁ፣በዘመዶቻቹህ ያሉ በሁሉ ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ለምስኪንነታቸው አይደለም ሰዉ ሳር ቅጠሉ የሚመሰክርላቸውን ሰዎች በጥሞና አስተውሉ። እነዚህ ምስኪን-ባሎች ሌሎች ባሎች ለሚስቶቻቸው፣ ለሚስቶቻቸው ቤተሰቦች፣ ለሚስቶቻቸው ወዳጆች ብቻ ምን አለፋችሁ በሚስቶቻቸው በኩል ለሚያውቋቸው ሁሉ የማያደርጉትን ቸርነት ወይም መልካምነት ያሳያሉ ያደርጋሉም። ለምን? ብላችሁ ስትጠይቁ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለት አንኳር መልሶችን ታገኛላችሁ፤በሁሉ ልወደድ ባይነታቸውንና ግጭትን መሸሻቸውን። ይህ ድርጊታቸው ግን የፈሩትን ከመድረስ አያግደውም፤ እንዲያውም በመጠንም በዓይነትም ጎልቶ ይፈጸማል እንጂ ።እርሱም ይህ ነው ተብሎ የማይገለጽ በሚስቶቻቸው የሚደርስባቸው ንቀት (አለመወደድ)እና ግጭት ናቸው።

ምስኪን-ባል አንድም የቤቴን ጸጥታ፣ ሰላም እና ፍቅር አላደፈርስም እንዳውም ያጠራልኛል ብሎ ፤አንድም በቅጥ የለሹ የእኩልነት ስብከት ተሰብኮ ሚስቱን አይቋቋምም ወይም አይጋፈጥም። ስለዚህም ደግሞ የማይፈልገውን ነገር “ችግር የለውም”፣ ሊፈጽመው የሚወደውን(የሚፈልገውን)ደግሞ “ግድ የለም ይደርሳል” እያለ ይጓዛል። ይሄ ሰው ግን ሰው አይደለም እንዴ? ታዲያ እርሱ በሰውነት ተፈጥሮው ፣ስጋ በባሕሪው የያዘውን በተለይም ደግሞ መሻትን ገንዘብ አድርጎ ፍላጎት አልባ ሆኖ መታየቱን ምን ይሉታል? “ውደዳት፣ ተንከባከባት፣ እዘንላት” ማለት ስለፍላጎቶችህ እና ስሜቶችህ ዋሻት(ደብቃት) ማለትነውን? ምንም እንኳ የመዋሸቱ ዓላማው እርሷን ለማስደሰት ወይም ላለማሳዘን ቢሆንም ፤ እርሱም ላይሳካ።ደግሞስ ስለፍላጎቶቹ ግልጽ ካልሆነ ሚስቱስ እንዴት ብላ ደስ ልታሰኘው ትችላለች?
በተጨማሪም ፍላጎቶቹን ደብቋልና ማንም አይረዳውም በተለይም ሚስቱ። እርሱ ለሚስቱ የሚነግራት እርሷን የሚያስደስታትን ወይንም ቅር የማያሰኛትን ብቻ ነው። ከተከፋችበት ከተነጫነጨችበት ቶሎ በይቅርታም ይሁን በማባበያ ይመልሳታል። ጣፈጠም መረረም እኔ እንዲህ ነኝ ፍላጎቶቼም እነኚህ እነኚህ ናቸው ብሎ ቁርጥ ባለ ቋንቋ ተናግሮ ከጠቀሳቸው ፍላጎቶቹ ጎን በመቆም የሚመጣውንም መጋፈጥ አይችልም። እስቲ ራሳችሁን ታዘቡ “ይሄን እንዲህ እንዲህ ላድርገው?” ስትባሉ ምን ትመልሳላችሁ? የፈቀዳችሁትን “አዎን እንዲህ እንዲህ ይሁን” ያልፈቀዳችሁትን ደግሞ “አይሆንም አይደረግም” ብላችሁ ፍርጥም ትላላችሁ? ወይንስ “ጣጣ የለውም፣ችግር የለውም” ነው መልሳችሁ። ጣጣማ አለው ልጄ ችግርማ አለው እያልኩህ ነው። በጭራሽ “ችግር የለውም” የሚለውን መልስ አትጠቀም። በትዳር ሕይወትህም ሆነ በሌላ ማሕበራዊ ሕይወትህ እንዲሆን ለፈቀድከው ነገር(ጉዳይ) እርሱኑ ጠቅሰህ ይሁን ይፈጸም በል። አልያ ግን ተቃውሞህን ሾላ በድፍኑ ሳይሆን በግልጽ ቋንቋ አልፈልግም፣ አልወድም፣ አይሆንም እና የመሳሰሉትን ተጠቅመህ አሳውቅ ግብረ-መልሱንም እንደ አመጣጡ አስተናግድ።

እውነትን ይዘህ በጭራሽ አትፍራ!!! እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር ሲባል አልሰማህም። እውነት አርነት ታወጣሃለችና አንተን፣ ያንተን ፍላጎቶች እና ስሜቶች በአግባቡ ልትገልጻቸውና ልታስተናግዳቸው ይገባሃል።ይህን በማድረግህም ራስህን፣እውነቱን፣ ተናገርክ እንጂ አልዋሸህም። የሚወድህም ሰው በተለይም ሚስትህ ልትወደው የሚገባት በእውነት የሆንከውንና የፈለከውን እንጂ በውሸት የተቀባውን እርሷን ደስ የሚያሰኘውን መሆን የለበትም። በሌላ ቋንቋ ውሸትህ ከሚመቻት ይልቅ እውነትህ ይጎርብጣት።ያን ጊዜ ከእውነትህ ጋር ራሷን ለማስማማት ትጥራለችና ካልተመቻትም ትመክሩበታላችሁና የተገለጹትም ጠባዮችህ የእውነት ሲሆኑ ምክራችሁ ውጤታማ እና ጽኑ ይሆናል።
****ልብ አድርግ አጉል “ፍቅር ፍቅር ብለህ፣ ሚስቴን ደስ ይበላት ብለህ ፣አልያም አትከፋብኝ” ብለህ ራስህን፣ ፍላጎትህን መደበቅህ በሚስትህና ባንተ መካከል ያለውን የየራሳችሁን ግንዛቤ ከማዛባት ውጪ አንተ እንደምታስበው ያንተን ፍላጎት ሰውቶ ትዳራችሁን በጭራሽ አያጸናውም።******

ዛሬ ዛሬ ላይ የአብዛኛውን ወንድ ምስኪንነት በፍቅረኛው ለሚቀርብለት የፍላጎትም ሆነ የመብት ጥያቄ በተደጋጋሚ በሚመልሰው “ጣጣ የለውም የኔ ፍቅር፣ችግር የለውም የኔ ማር” መልስ ማወቅ ይቻላል። ጓደኝነታቸው ሲጀመር ገና ሊገናኙ የሚቃጠሩበትን ቀን፣ ቦታ እና ሰዓት እንኳ እንዲህ ይሁን ብሎ መቁረጥ አይችልም። አይ እንዲህ ይሁን ስትለው “ችግር የለውም፣ ችግር የለውም፣ችግር የለውም” የሚለውን የምስኪን ቋንቋ ሀ ብሎ ይጀምራል ከዛማ ምኑ ተወርቶ ያልቃል። “ችግር የለውም” የምትለው ቃል ግን ጉድና ጅራቷን የኋላ የኋላ ታመጣቸዋለች፤ የመከራንም ጽዋ ትግተዋለች። አንተስ አሁንም በምስኪንነትህ ጸንተሃል ወይስ ራስህን ወደ አባወራ ከፍ እያደረግህ ነው?….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *