ምስኪን ወንድ ፈሪ ነው!

ሳተናው!


አዎ! ምስኪን ወንድ ፈሪ ነው! ምስኪንን በተፈጠረበት ልክ፣ ለተፈጠረለት ዓላማ እና ውስጡ ላመነበት ነገር እንዳይኖር የሚያደርገው ፍርሃት ነው።

ይኼንን አብዛኞቹ ምስኪኖች ለመቀበል ይከብዳቸዋል፣ ማመን ይቸግራቸዋል፣ ይክዳሉም፤ ደፋር ነን ብለው ያስባሉና። እኔ ግን በራሴው እግር ሄጄበታለሁና እንደ መልካም ስፍራም ተመላልሼበታለሁና አውቀዋለሁ።

ምስኪን ማለት ፈሪ ነው!
ፈሪ ስንል ሰውየውን ፍርሃት ስንል ስሜቱን ይጠቅሳል። ምን ማለት ነው?

፩ኛው በበጎ ጎኑ፦ የሰው ልጅ ፈጣሪውን የሚፈራበት ስሜት አግባብ ሲኾን
፪ኛው ግን፦
      👉 የጉብዝና ኃይል የሌለው፣ የድፍረቱ ኃይል የዛለ፣ድፍረት የሌለው፣ ቡቡ፣ ፈርጣጭ
(ከሳቴ ብርሃን ሰላማ መዝገበ ቃላት)

      👉 ወኔ ቢስነት፣ ድፍረሽ የለሽ (ዘርጋው)
      👉 ቡቡ፣ ስጉ (ዐለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ)

ከላይ የጠቀስኳቸው የመዝገበ ቃላት ፍቺዎች በያዝነው ዐውደ-ንባብ ውስጥ የጋራ ትርጓሜ ይዘን እንድንሄድ ፈልጌ ነው።

ፍርሃት የጠቀስናቸውን ትርጓሜዎች ከያዘ ወደ  እኛ ጉዳይ ስንመጣ ታዲያ ምስኪን ለምን ይፈራል? ብለን እንጠይቅ። ምስኪን ወንድ አንድን ነገር አጥብቆ ይፈራል እርሱም፦

“የሰውን ጥላቻ” ነው።

ይኽ የሰውን ጥላቻ መፍራቱ ደግሞ ከምን ይመነጫል ቢሉ “ሰውን ማስደሰት፦ ደስታን ይሰጠኛል፣ በሰው ዘንድ ቅቡል ያደርገኛል፣ ያስወድደኛል፣ ያስከብረኛልም” ከሚለው የውድቀት መርሑ ይመነጫል።

ይኼንንም መርሕ ከአስተዳደጉ(ከቤተሰብ፣ ከትምሕርት ቤት…..)፣ ከመገናኛ ብዙኃን እና ከራሱም የተሳሳተ አረዳድ አግኝቶ በልቡ ያትመዋል። ከዚያም በኑሮው ኺደት ኹሉ ሰውን ለማስደሰት ይሞክራል፣ ይጥራል። 

ማንም ሰው በእርሱ ላይ ቅያሜ፣ ጥላቻ እንዳይዝበት፤ ስሙም በክፉ እንዳይነሳበት ማድረግ የሌለበትን ኹሉ ሲያደርግ ማድረግ የፈለገውንና የተገባውን ግን ይተዋል። ይኼንንም የሰውነት ልኩ የመንፈሳዊነትም ጥጉ ያደርገዋል።

ከዚህ የውድቀት መርሑ የተነሳ አንድን ነገር ለማድረግ ገና ሲያስበው ወደ አእምሮው የሚመጣው “ይኼ ነገር እኔን ይጠቅመኛል ወይ” ሳይኾን “ሰው ምን ይለኛል? ይቀየሙኛልስ ወይ?” ነው።

ምስኪን ወንድ ፈሪ ነው! “ምን ያስፈራዋል?” ብትሉ የሰውን ቅያሜ ይፈራል።

ምስኪን አንድን ድርጊት እንደፈጣሪው ትዕዛዝ፣ እንደ ልቡም ፈቃድ(መሻት) እና እንደነገሩም ተገቢነት(ትክክለኛነት) ከመፈጸም ይልቅ የሰው ፊት ያያል። በዙሪያው ያሉ ሰዎች ፊት ከከፋበት ይተወዋል። ሲተወው ግን ፍርሃት ነው አይለውም ፍቅር እንጂ።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ምስኪን “አፍቃሬ ሰብዕ(ሰው ወዳጅ)፣ መልካም አሳቢ፣ ሰውን ማስቀየም የማይፈልግ” እና የመሳሰሉት እየተባለ ይሞካሻል። እርሱም በ”ትክክለኛ መንገድ” ላይ ስለመኾኑ ማረጋገጫ ያደርገዋል።

እውነታው ግን “ብጠላስ” ብሎ ያመነበትን፣ የወደደውንና የተገባውንም ነገር ከማድረግ ልቡ የፈራ፣ የባባ፣ የሠጋ ሲኾን በስተመጨረሻም ድፍረቱን አጥቶ ወኔውም ርቆት በፍቅር ስም ራሱን የሸወደ ፈሪ ይኾናል።

የምስኪን የፍርሃቱ ጥግ 

በተለይ በጾታዊ ግንኙነት(በፍቅር ሕይወቱ) በምስኪኑ ላይ ታላቅ ፍርሃት ይታያል። እርሷ እንዳትጠላው ሲል ያመነበትን፣ የሚፈልገውንና የተገባውን ነገር ጥሎ ከእርሷ ጋር ይስማማል። ውጤቱ ምንም ይኹን ምን ብቻ ከእርሷ ጋር መጋጨት እርሷን ማስቀየም አይፈልግምና ይስማማል። ይኼ ደግሞ ለፍርሃት እንጂ ለፍቅር ጠባዩ እንዳልኾነ ለመረዳት የፍልስፍና ትምሕርት መውሰድ አይጠይቅም።

ምስኪን እንደ ቤተሰብ መሪነቱ አንዲት ውሳኔ ራሱን ችሎ አይወስንም “ለምን?” ብላችሁ ብትጠይቁት ምን ይመልሳል?…… “በፍቅር አምናለሁ”

ጣፈጠህም መረረህም ምስኪን ከኾንክ ፈሪ ነህ። እርሱ ደግሞ በኑሮህ ውጣ ውረድ፣ በማሕበራዊ ግንኙነትህ፣ በፍቅር ሕይወትህም ፈቀቅ እንዳትል እንዳታድግም አስሮ የሚይዝህ ጠላትህ ነው። 

መፍትሔው

ፍርሃት ስጋ ለባሽ ኹሉ ምን ደፋርና ጀግና ቢባል የሚሰማው ስሜት ቢኾንም(ስጋት ለስጋ ለባሽ ኹሉ ጠባዩ እንደኾነ) ስሜቱ የሚነዳው ለእርሱም የተገዛ አለመኾን ግን ጀግንነት ነው።

አባወራ ስትኾን ያሰብከውንና ያመንክበትን ስትናገርና ስታደርግ ለሚመጣው ነገር “እኔ ነኝ” ብለህ ኃላፊነት በመውሰድ ተገብቶህ ታደርጋለህ እንጂ የሰው ፊት በማየት አይደለም። ልታደርገው ስትል የሰው ፊትና ካሜራ አትይ ጭብጨባና ውዳሴም አትጠብቅ ማድረግ ስላለብህ፣ ስላመንክበትና ስለፈለግከውም  ይኹን እንጂ።…. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *