ምስኪን-ወንዶች አድናቆቶን (በተለይ) ከሴቶች ይፈልጋሉ

ይሄን ርዕስ ላብራራው ሳስብ ምን ያክል ብዙ ወንዶች በዚህ ጥላ ሥር እንደሚያርፉ አስበውና የምገልጽበት ቃላቶች ያጥሩኛል አንድም ገጼ ይጠበኛል። ለምን? ይህን አድናቆት፣ፈቃድ፣ማረጋገጫ ጠያቂነት በተገላቢጦሽ ሴቷ ከወንዱ የምትሻው ነበርና። አንተ እንግዲህ የቱ ጋር እንዳለህ ራስህን ፈትሽ።
ምስኪን-ወንድ በእያንዳንዱ የድርጊቱ ፍጻሜ ላይ የሚስቱን ወይም የሴቷን ማረጋገጫ መስማት ይፈልጋል። እርሷን ወይም ብዙ ሴቶችን የማረከበት ከሆነ “ትክክል ነኝ፣ሚስቴ ትወደኛለች፣ ሴቶች ይወዱኛል” ብሎ ያስባል።እኔ ግን እልሃለሁ ላንተ ማረጋገጫህ ፈጣሪ የሰጠህ ሕሊናህ፣በእርሱም ላይ ያለህ እምነት፣ በተለይም በአንተ በእጁ ሥራ (በራስህ ተፈጥሮ) ላይ ባለህ ተጨባጭ እውቀት እንጂ ሌላው ካንተ ይራቅ።ይህች ዕውቀትህ ስትጸናም ነው እውነተኛ አፍቃሪህን የምታገኘው። ከሰዎችማ ማረጋገጫ ስትሻ መቼም ራስህን ሳትሆን ለራስህም ሆነ ለሚስትህ ሳትበጅ ታልፋለህ።ሰዎች በራስ መተማመንህን እንዲሰጡህ አታድርግ ሚስትህም ብትሆን። እንደውም አንተ በራስህ ስትተማመን ሚስትህ ባንተ ላይ የመደገፍ ፍላጎቷ ይጨምራል፣ ይህ ደግሞ አንተን ለእርሷ ብቻ እንድትሰጥ ይጋብዝሃል(በፍቅር) እርሷንም ይማርክልሃል።
የእርሷ ባንተ ጽናትና እምነት ላይ መደገፍም ነው አንተን እንድትወዳት እና እንድትንከባከባት የሚያደርግህ። በሌላ አገላለጽ ደግሞ፦ ይህ ነው ወይም ነበር ሴትን ልጅ ወንዱ እንዲወድበትና እንዲንከባከብበት በውስጡ የተቀመረለት የፍቅር ጥበብ። ዛሬ ዛሬ ግን ሴቷ ይህን በወንዱ ላይ ያላት እምነትና ድጋፍ እንደ ክፉ ጋኔን እየተቆጠረ “በጭራሽ የወንድ ጥገኛ አትሁኚ” “የወንድ እጅ አትዪ” እየተባለ ይመከራል። አዎ ይህንን ሴቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ወንዶቹም ይሉታል፤ ምናልባትም “እየሠራች አታግዘኝም” ብለውም ይነጫነጫሉ። ይህን ስንል ግን ሳናስበው ምን እንዳተረፍን ታውቃላችሁን? ለራሱ ቆሞ የሚያቆማት ፣ በእምነቱ ጸንቶ የሚያጸናት፣ ቃሉን ጠብቆ የሚታመንላት፣ በውሳኔው ጸንቶ ወደብ የሚሆናት የእርሱን ድጋፍ መሻቷን የሚወድላትን ወንድ ሳይሆን የራሱ መልክ(መገለጫ) የሌለው ተለዋዋጭ(በራሱ የማይቆም)፣ በእምነቱ የማይጸና (ያመነበት ዓላማ የሌለው)፣ ቃሉ የረከሰበት ላያት ሁሉ የፍቅር መኃላ የሚምል፣ ውሳኔውን አቋሙን ለአንዷም እንኳ ቢሆን በተደጋጋሚ የሚለዋውጥ፣ ድጋፍ መፈለጓን ወዶ ሠርቶ በመደገፍ ፍቅራቸውን ከማጠንከር ይልቅ “ራስሽን ቻይ ከእኔ ላይ ውረጅ” የሚል ወንድ አተረፍን። ታዲያ ሴቶች ራሳችሁን ቻሉ ወንድ ላይ ጥገኛ አትሁኑ ሲባሉ ይህንንም ሲሆኑ ወንዱ በተፈጥሮው ሊሞላው የሚፈልገውን ክፍተት ያጣል ሁሏም “ራሷን የቻለች፣ የወንድ እጅ የማታይ ፣ጠንካራ ሴት” ትሆንና አንዷን ካንዷ፣ ይህችን ከዛች፣ የመጣችውን ከሄደችው የሚለየው በመልክ ብቻ ይሆናል። ይህ ነው እንግዲህ የዘመናችን በሽታ ወንዱም ሴቱም የታመመበት። ሴቷ ራሷን በመቻል ሩጫ ላይ ስለውበቷ ተጨንቃ ስትኖር ወንዱ ደግሞ በወንድነቱ ደጋፊነቱ አለኝታነቱ ይቀርና መልክ ቀላዋጭ ሆኖ፣ ሲመርጥ ሲያማርጥ፣ ሲቀምስ ሲቀማምስ ፣በዝሙት ተወርሶ ፣ውድቀቱን ከስኬት ቆጥሮ፣ ድካሙን የድል ዒላማ አድርጎ፣ ውርደቱን በ”ክብር” ዜማ አቆለጳጵሶ እያቀነቀነ ከድጥ ወደ ማጥ ይጓዛል።
ብዙ ምስኪን-ወንዶችም በሴት መከበባቸውን የመወደዳቸው ምስክር፣ ሴት(ሚስት) ለማግኘታቸው ዋስትና አድርገው ይወስዱታል። አንዳንዶችም ደግሞ ከተለያዩ ሴቶች ጋር በፍቅርም ሆነ ባልጋ መውደቃቸው ወንድነታቸውን የሚያረጋግጥላቸው በራስ መተማመንን የሚጨምርላቸው አድርገው ይስሉታል። ይህ ግን ትልቅ ስህተት ነው። ላንተ ወንድነት፣ ላንተ በራስ መተማመን፣ ላንተ አፍቃሪነት፣ ላንተ ጤናማ እና ተፈጥሮአዊ ወሲበኛነት…በአጠቃላይ ላንተ አባወራነት ማረጋገጫ እና ምስክርነት የሚያጨበጭቡ ሴቶች ወይም የሚሰው የሴት ገላዎች መኖር የለባቸውም(ምንም እንኳ በፍላጎታቸው ቢሆንም)።
እናስ?

ተፈጥሮህን እወቅ ተረዳ!! ለማንነትህም ሆነ ድርጊትህ ፈቃድ ወይም ማረጋገጫን ከውጭ አትሻ!!!!!
አንተ ወንድ የምትሆነው
1ኛ ተፈጥሮህ ስለሆነ ነው(የሠራ አካልህ)
2ኛ ማንነትህን በመቀበልህ እና በዛም ማንነት ስትኖርም ነው።(አልያ ሚስት መሆን አማረኝ ማለትህ ወይም ለወንድነትህም ማረጋገጫን መሻትህ አይቀርም)።
ምስኪን-ወንድ(ባል) ሚስቱን ከመማረክ ይልቅ እርሱ በወደደ ከፍቅረኛው ምስክርነት ማረጋገጫን ይሻል።ማን ይሙት አሁን አንተ ከወደድክ ካንተ በላይ ለመውደድህ ምስክር ያሻኻል? ታዲያ በፈቃድህ የወደድከውን ከመጠየቅ ከእና ከመውሰድ ውጪ መነፋረቅህ “የፍቅርህ ብርታቱ” ነው ያስብላል? ለምንስ እርሷን “መስክሪ እስቲ ባንቺ ላንቺ አይደለም እንዴ” እያልክ ታስጨንቃታለህ።ይህ በምስኪኖች የመጀመሪያ የፍቅራቸው ጥንስስ ጀምሮ እስከ ትዳር ሕይወታቸው በአሳዛኝ ሁኔታ ይታያል። ወደኃታል? አዎ! አግብተኃታል?አዎ! የሚጠበቅብህን አውቀህ ተፈጥሮህን እና ተፈጥሮዋን ተረድተህ አድርግላት እንጂ ዘመን አመጣሽ ስልጣኔ ተብዬ ፈቃድ (ማረጋገጫ) ከአፏ ወይም ገጽ ለገጽ እርማት ከአንደበቷ ስትከጅል አልጫ ትሆንባታለህ። ካላገባኃትና ካልፈለገችህ ደግሞ ውሳኔዋን አክብረህ ክብርህን ጠብቀህ ተለይ እንጂ አታላዝን።…..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *