ምስጋናና እጮኛህ

ጀግናው ወንድሜ!
ይኽ በተግባር የተፈተነ፣ በጥናት የበለጸገ፣ በንባብም የዳበረየሕይወት ትምሕርት ነው። ማንም ጨክኖ ይኽን አይነግርህም፤ ቢመርህም ግን እወድሃለሁና እንዲህ እልሃለሁ…..

ከዚህ በፊት በነበሩት ኹለት ጽሑፎች የምስጋናን ጥቅም፣ ያንተ አመስጋኝ መኾን በትዳርህ ውስጥ የሚያመጣውን እረፍት አይተናል።

ሲቀጥልም አመስጋኝ ሕይወት እንዳይኖረን እንቅፋት ጋሬጣም የሚኾኑብንን ጠቁሜሃለሁ።

እነዚህንና ሌሎችንም ጨምረህ በአባወራነት ጉዞህ አመስጋኝነትን ተለማምደህ ቤትህ በበረከት ይሞላ ዘንድ ለሌሎችም አርአያ ትኾን ዘንድ እመኛለሁ።

አኹን ደግሞ አንተ ምንም እንኳ ምስጋናን ተምረህ ተለማምደህም አመስጋኝ ብትኾን የምትመርጣት ሚስት መሠረታዊ የአመስጋኝነት ሥርዓት ከሌላት የምስጋናንም ችግኝንም እናቷ ካልዘራችባት ትዳርህ ፈታኝ እንደሚኾን አትጠራጠር።

ይኸውልህ ወንድሜ!

ነገሩ ኹልጊዜ እንደምነግርህ ነው። እርሱም ሴትህ ካደገችበት ቤት እናቷ አባቷን (ሚስት ባልን) ስታመሰግነው ካላየች ያንተ አርኣያነት በድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ነው። ምክንያቱም እርሷ ባደገችበት ቤት ለወንድ ልጅ በተለይም ለአባቷ ጉልበት፣ ድካም፣ ለድካሙም ፍሬ ምስጋና ሲመለስለት አላየችምና።

የሚገርመው ታዲያ እናቷ ያልዘራችበትን ምስጋና ላንተ ከየትም አምጥታ አትሰጥህም። ደክመህ፣ ቸኩለህ፣ ያለህን አሟጠህ ደስ አሰኛታለውም ብለህ ወደ ቤትህ ብትፋጠን እናቷ ለአባቷ ትሰጠው ከነበረው የንቀት መልስ የተለየ አታገኝም፤ የተዘራባት እርሱ ነዋ!

እውነት እልሃለሁ ወጥተህ ወርደህ፣ ሠርተህ ደክመህ ባገኘኸው ብትችል ጠቦት፣ አልያም ጎድን፣ አልያም አንድ ኪሎ የክትፎ ስጋ፣ አልያም ዳቦ፣ ወይም ጮርናቄ(ብስኩት) ይዘህ ስትገባ አንተን በፈገግታ፣ የሰጠሃትንም ተቀብላ፣ አብቃቅታ ቤተሰቡን መግባ የምታሳድርልህ ሴት እናቷ አባቷን በማመስገን አርአያ የኾነቻት ናት።

ነገር ግን በእናቷ የሚከሰስ፣ የሚማረር፣ አባት ያላት ሴት ልጅ አልፎ ተርፎም አባቷን ላንተ የምታማ ከኾነች ነግ በኔ ብለህ ስማት። አንተ ስታገባት የአባቷን የክስ ፋይል ወንዶች ኹሉ አንድ ናቸው ብላ ወዳንተ የምታዞር ናት።

ጠቦት መግዛት አይደለም ሰንጋ ብትጥል፣ ወርቅ መግዛት አይደለም ወርቅ ቤት ብትከፍትላት፣ ሶደረ ላንጋኖ አይደለም ዱባይ ብታዝናናት አታመሰግንህም። ካላመንከኝ ዱባይንም ገዝተህ ሞክራት ስላለው ነው ግዴታው ነው ብትልህ እንጂ።

ስለዚህም ወንድሜ ልብ አድርግ!
ይኽቺ አንተ የመረጥካት ሴት ኮትኩተህ የምታሳድገው አርአያም የምትኾነው የምስጋና ዘር ችግኝም በውስጧ መኖሩን አረጋግጥ።

የችግኙ አብቃይ ወላጆቿ ቢኾንም መራር ይኹን ጣፋጭ ዘር መርጣ የምትዘራባት ግን እናቷ ናት። ይኼንን ምርመራህን ውበቷ፣ ሰውነቷ፣ እድሜዋ፣ ትምሕርቷ፣ ሐብቷ አሳዛኝነቷ ሊጋርዱት አይገባም።

ብዙውን ጊዜ ምስኪንነታቸውን ገፈው ያልጣሉ ወንዶች፣ የራሳቸውን አባወራ ያለመኾን ስንፍና የሚደብቁ ወንዶች ከማማረር ውጪ የአመስጋኝነት ጠረኑ ሲያልፍም ያልነካካቸው ሴቶች ሥር በ”ፍቅር” ሰበብ ወድቀው ማየት የተለመደ ነው።

ጀግናው!
አንተ ግን ከዚህ ራቅ የመረጥካት ሴት በትንሽ በትልቁ አማራ፣ አልቅሳ፣ ተነጫንጫና አሳዝናህ አይደለም የምትወዳት። ይኽ የምስኪን ወንድ ጠባይ ነው።

አንተ ሴትን ለሚስትነት ከመምረጥህ በፊት ራስህን ከምስኪንነት አላቅ። ካልኾነ በትዳርህ ውስጥ በሚገጥምህ መከራ ሚስትህ ላይ ጣትህን የምትቀስር ሰበበኛ ኾነህ ታርፈዋለህ።

ሲቀጥልም ፊትህ የተቀመጠችው ሴት የምታወራልህን አሳዛኝ ትራጀዲ ወደ ጎን አድርግ። ቀጥተኛም ጥያቄ ጠይቅ እናቷ አባቷን እንደቤቱ ምሰሶ እንደቤተሰቡም መሠረት አድርጋ በሰጣት ኹሉ ስሙን ታመሰግናለች ወይ? ይኽች ልጅስ ምስጋናን ታውቃለች ወይ?…. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *