ምስጋና

ጀግናው ወንድሜ!

ዛሬ ደግሞ እስቲ ምስጋና ራስህን፣ ቤትህን፣ ሚስትህንና ልጆችህን በመምራቱ ኺደት
ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንይ።

ምናልባት ምስጋና በደንብ “እናውቃቸዋለን” ከምንላቸው መልካም የኾኑ ሥነምግባራዊና መንፈሳዊ ልምምዶች አንዱ ነው። ይኼም ደግሞ በብዙዎቻችን ዘንድ በአንድ ወቅት ላይ ስለተደረገልን መልካም ነገር የሚሰማንን ጥሩ ስሜት የምንገልጽበት ይበልጡንም ቅጽበታዊ ምላሽ ነው።

ነገር ግን ምስጋና በአንተ ሕይወት ውስጥ ስለተሰከሰተ መልካም ነገር በማመስገን ብቻ አይወሰንም። የእነዚህን መልካም ነገሮች በከፊልም ይኹን በሙሉ አስገኚያቸው ከአንተ ውጪ በኾነው አካል መኾኑን ተረድተህ ዘወትር የምትለማመደው እንጂ። በዚህም ምክንያት ምስጋና የሕይወትህ ሥርዓትህ አንድ አካል ይኾናል።

ብዙ ጊዜ ምስጋናን የስሜቶቻችን መግለጫ ነው የምናደርገው። ይኽም ማለት የምናመሰግንበት ጥሩ ስሜት ሲሰማን ብቻ እናመሰግናለን ያ ጥሩ ስሜት ሳይኖረን ሲቀር ግን አናመሰግንም።

አኹን እኔ እያጫወትኩህ ያለሁት ምስጋና ግን የስሜት መግለጫ ሳይኾን ድርጊት እንጂ። ምስጋና ድርጊት ሲኾን ደግሞ አስበህበት፣ አምነህበት ያመንከውንም በስሜት ሕዋሶችህ ሲሠራጭ የምታደርገው ነው።

ልብ አድርግ! ይኽ አስበህና አምነህ በስሜት ሕዋሶችህም ተሠራጭቶ የምታመሰግነውን ምስጋና በአንደበትህ ባትገልጸው እንኳ በመላ ሰውነትህና በሕይወትህ ይታያል።
እንዲህ አስበህና አቅደህ ማመስገንህ በሕይወትህ ያለውን ውጣ ውረድ፣ መከራውንና ችግሩን መካድ አይደለም። ነገር ግን በሕይወት ጥጋ ጥግ ያሉትን ብዙውን ጊዜም ከማናስተውላቸው በጎነቶች፣ ደስታዎች፣ ተፈጥሮአዊ እውነታዎችና ጸጋዎች(ስጦታዎች) ለማትረፍ እንጂ።

እንደ አባወራ በጠዋት ከምትነሳባቸው ምክንያቶች አንዱ ለምስጋና መኾን አለበት። በተኛህበት እንዳትቀር የፈቀድከው አንተ ሳትኾን አንተን በዐላማ የፈጠረና ለዐይኑ እንቅልፍ የሌለበት ፈጣሪ ነው።

ውድ ወንድሜ! ቀንህን በምስጋና ጀምር። እንደው ፊት እንደመታጠብና እዳሪም እንደመውጣት (እንደመጸዳዳት) በልማድ በደመነፍስህ አታድርገው። አስበህበት የዛሬን ሌሊት ማለፍህን አስምረህበት የምታመሰግንበትን ቃላት መርጠህለት ለምስጋናም የሚኾን ምግባር ሠርተህ እንጂ።

ይኽን የምስጋና ሕይወት ስትለማመድ የራስህን ሕይወትና የቤተሰብህን በተረጋጋ መልኩ መምራት ያስችልሃል። እነርሱም ይኼን ካንተ ይማራሉ። አንተ በብዙ መከራ ውስጥ እያለፍክ፣ ሀገርህ በብዙ ችግር ውስጥ እያለች፣ ቤተሰብህም ብዙ ፈተና ተጋርጦበት ሳለ አንተ ዘወትር ለአኮቴት(ምስጋና) ከአምላክ ፊት ስትቀርብ ያያሉና ፈለግህን ይከተላሉ።

የምስጋና ቅብብሎሽ

ምስጋና ከሰው ወደሰው የሚተላለፍ ነው። አንተ አመስጋኝ ስትኾን ሚስትህም አመስጋኝ ትኾናለች፤ ልጆችህም እንዲሁ። አንተ ስታማርር ሚስትህም ኾነች ልጆችህም እንዲሁ መኾናቸው አይቀርም።

አንተ ፈጣሪ የሰጠህን ስጦታ አነሰ በዛ ሳትል አመስግነህ በዚህም ስጦታህ ብትጠቀምበት ሚስትህም አንተ የሰጠሃትን ስጦታ አመሰግና ተቀብላ ትጠቀምበታለች፤ ልጆችህም እንዲሁ።

ሚስትህ እንድታዝንልህ አስበህ ዕለት ዕለት ስለገጠመህ ፈተና፣ ችግር፣ የሰላም ማጣት፣ የፍትህ መጓደል ማታ ስትገናኙ አታቅርብላት። ለጊዜው ብታጽናናህ እንጂ እርሷም ያንተኑ ጠባይ አንጸባርቃ አንተ በምትሰጣት( የአደባባይ ድካምህ፣ በእልፍኝ ስርዓትህ፣ የመኝታ ቤት ወሲብ) ታማርርሃለች። ልጆችህም እርሷን እያዩ መከተላቸው እርግጥ ነው።

የምስጋና ጥቅሙ ከተመስጋኙ ይልቅ ይበልጡኑ ለአንተ ለአመስጋኙ ነው። ዛሬ በተግባር አንተ ቤት ምስጋናን ያልተለማመዱት ልጆች ነገ አድገው ትልቅ ከኾኑ በኋላ በጨበጧቸው ትልልቅ ስጦታዎች ፣ ትዳሮች፣ ልጆች፣ አያመሰግኑም። ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው/በኑሮኣቸው ሳይቸግራቸው ከደስታ የራቁ ይኾናሉ።

የትኞቹም ቤተ እምነቶች ስለምስጋና በመርህ ደረጃ ቢያስተምሩም ተግባራዊና ተጨባጭ የኾነውን የምስጋና ሕይወት አፈጻጸሙንም የምናየው ግን በቤተሰብ ውስጥ በወላጅም ላይ ነው።

ስለዚህም
፩ ሲጀመር ማመስገንን ከሕይወትህ ሥርዓት ውስጥ አካት(ልመናንና ምስጋናን ለይ)
፪ ለሚስትነት የምትመርጣት ሴት አመስጋኝ እርሱንም ከእናቷ የተማረች መኾኑን አስረግጥ። “እናቷን አይተህ ልጅቷን አግባ” እንዲሉ
፫ የምስጋና ሕይወትህ ይማሩበት ይከተሉትም ዘንድ በሚስትህ በልጆችህ ፊት ግልጥ፣ የታወቀና የተረዳ ይኹን።

እንዳናመሰግን ምን ያግደናል…ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *