“ምቾት በሽታ ነው!”

ጀግናው ወንድሜ ብዙዎቻችንን በምጣኔ ሀብት፣ በአእምሮ ልቀት፣ በመንፈሳዊ ተመስጦ፣ በአካል ብቃት(በጤና) እነንዳናድግ ከሚያደርጉን ነሮች አንዱ ምቾት ነው።

ምቾት ሰውን በእንጭጩ እንዲቀር ከርሞም ጥጃ እንዲኾን ትልቅ አስተዋጽዖ አለው። ሰውነትህን፣ አእምሮህንና መንፈስህን(ነፍስህን) ምቾት ስትነሳቸው ይጎለብታሉ፣ ይመጥቃሉ፣ ይበለጽጋሉ(በጸጋ)።

ሰውነት

ሰውነትህ ሲመቸው ይሰባል፣ ውጣውረድ የለበትምና ከምትበላው ምግብ የሚፈልገውን ወስዶ ሌላውን ወደ ስብ ቀይሮ ያስቀምጠዋል።

ስብ ደግሞ በልብህ ዙሪያ ሲጠራቀም፣ የደም ሥሮችህንም ሲያጠብ፣ በጉበትህና በኩላሊትህም ዙሪያ ሲከማች በሽታን ይዞ ይመጣል። ይኼን ስልህ ግን በሰውነትህ ላይ የጎላ ውፍረት ሊታይም ኾነ ላይታይ ይችላል። በተለይም የሥራህ ጠባይ ከቀኑ ብዙውን ሰዓት ቁጭ አድርጎ የሚያውልህ ከኾነ እነዚህ መከሰታቸው አይቀርም።

ከዚህም የተነሳ ቶሎ ይደክምሃል፣ በትንሽ በትልቁ ቁና ቁና ትተነፍሳለህ፣ አተነፋፈስህም ጥልቀት የለሽ አጭር ይኾናል ምን አለፋህ ግን ጤና ያሳጣሃል። አልፎ ተርፎም በወሲባዊ እንቅስቃሴህ አሉታዊነቱ ይጎላል።

ሐኪም ጋር ብትሄድ “ኮሌስትሮል ይታየኛል” ይልሃል። “ከየትመጣ?” ብትለው “አትንቀሳቀስማ”፤ “መፍትሔ ስጠኝ” ብትለው “እስፖርት ሥራበት” ብሎ ይሸኝሃል።

በሌላ ቋንቋ ምቾትህ በሽታን ጠርቷልና ሰውነትህን በስፖርት ምቾት ንሳው፤ ሌሊት ቀስቅሰህ አንቀሳቅሰው(አስሩጠው) እስኪያልብህም፤ መኪናህን አቁምና ወይም ከታክሲ ውረድና በእግርህ ኺድ ማለት ነው።

አንተም ወንድሜ ምክር ሰሚ ነህና ደረጃ በደረጃ ሰውነትህን ታንቀሳቅሰዋለህ። ስብህንም ከማጥፋት አልፈህ ጡንቻን ታዳብራለህ። በውጤቱም ሰውነትህ ንቁ፣ ቀልጣፋ፣ ታዛዥና ጤናማም ይኾንልሃል።
ይኽን ንቃትና ጥንካሬ ደግሞ ካወቅህበት ለመንፈስህና ለአእመሮህ እንዲተርፍና በስኬቱም እነርሱን እንዲያስከትል ማድረግ ትችላለህ።

ይመቸኝ ብለህ ማታ ድራፍትህን ስትገለብጥ አልያም ሶፋ ላይ ተጠቅልለህ ፊልም ስትኮመኩም አምሽተህ ጠዋት አምስትና ስድስት ሰዓት ድረስ አትተኛ። ይልቅስ ማታ በጊዜ ተኝተህ ጠዋት ማልደህ በመነሳት ሰውነትህን በስፖርት ብታነቃቃው ፈርጀ ብዙ ትርፍ ታገኛለህ።

፩ኛ ሰውነትህን ከአላስፈላጊ ስብ ትታደገዋለህ
፪ኛ የተስተካከለ የሰውነት አቋም ይኖርሃል
፫ኛ ጥንካሬ፣ ጉልበትና ጡንቻም ይኖርሃል
፬ኛ ወንዳወንድነትህ ይጨምራል

አእምሮህ
ከሰውነትህ አካላዊ እንቅስቃሴ የመጣው መነቃቃት ለአእምሮህ ይተርፋልና እርሱም ንቁ ይኾንልሃል። ይኼን ጊዜም አእምሮህ ዐዲስ ነገር እንዲቀበል በጥናትና በምርምር ስታስጨንቀው የድካምህን ፍሬ እውቀትን ገንዘብ ያደርጋል።

የሚታይ የሚዳሰሰው ሰውነትህ ከእንቅስቃሴ በኋላ አላስፈላጊ ነገር እንዳስወገደ፣አቋሙም እንደተስተካከለ፣ ፈርጣማም እንደኾነ ወንዳወንድም እንዳደረገህ አስተውል። አእምሮህም ከንባብና ከምርምር በኋላ ለአላስፈላጊና አጥፊ እውቀቶች ቦታ አይሰጥም። እውቀቱም በእውነት እና በእምነት የተረጋገጠ ይኾናል።

ብርቱና ምስቅልቅል የኾኑ የሕይወትህን ምስጢሮች መፍታት የምትችልበት ጥበብም ይኖርሃል። በምርምርና በልምድ የዳበረ እውቀትን ገንዘብ አድርጓልና ባወቀው እውቀት ይጸናል በራስ መተማመኑም ይጨምራል።

መንፈስህ(ነፍስህ)

ወንድሜ መንፈስህን ማደስ፣ ኅሊናህን ማሳረፍ ነፍስህንስ ማስደሰት ትሻለህን? እንግዲያውስ እውነቱን እነግርሃለሁ በአሸሼ ገዳሜ እነዚህን አታገኝም። መንፈስ የኾነው አምላክ ነውና በአርአያውና በአምሳሉ የሠራህ፣ ትንሹን እርሱ(ኅሊናህን) የሰጠህ፣ ሕይወት የኾነች እስትንፋስ ነፍስንም እፍ ያለብህ እርሱን ወደመምሰል ስትመጣ ብቻ ትጠነክራለህ፣ ትበረታለህ ታርፋለህም።

ይኼን ለማድረግ ደግሞ ቀላሉ መንገድ “እኔን፣ ራስህን፣ ዓለምንም እወቅበት በስርዓትም ኑርበት ብሎ የሰጠህን የሕይወት ቃል መጽሐፍ(manual) ማንበብና እንዳነበብከውም መኖርን መለማመድ ነው።

አንተ ለማንበብና እንዳነበብከውም ለመኖር ቁርጥ ውሳኔና ፈቃድ ይኑርህ እንጂ ትማራለህ፣ ታድጋለህ፣ ትመጥቃለህ። አልያ ግን ምሬት ቀለብህ፣ ንጭንጭ ቋንቋህ፣ ፍርኃት ኃሳብህ፣ ተስፋመቁረጥ ውሳኔህ ጉስቁልናም ሕይወትህ ይኾናሉ።

ወንድሜ ፈተና ስትፈተን “ለምን?” እያልክ አትማረር። ከፈተናው የምታገኘውን እውቀት፣ የምታተርፈውንም ጸጋ፣ የሚጨመርልህንም ማዕረግ አስብ እንጂ።ነገር ግን ምሬትን ስታዘወትራት ራሷን እያባዛች ሕይወትህን ተስፋ ቢስ ኑሮህንም ጎስቋላ ማድረጓ እሙን ነው።

እንዲህም ተብሏል፦
“ተመስገን ይለዋል ሰው ባያሌው ታሞ
ያማረሩት እንደሁ ይጨምራል ደግሞ”

ወንድሜ ስለዚህ ከምቾትህ ውጣ፤ የሰውነትህ እንቅስቃሴ፣ የአእምሮም ምርምርህና የነፍስህም ፈተና አንተን ከፍ ያደርጉሃልና። ይኹን እንጂ ፈተናን ላክ ብለህ ወደ ሰማይ አንጋጥ ጦርነትንም ውለጂ ብለህ ምድርን እርገጥ አላልኩህም። ለመለወጥ ስትወስን ፈተናው ራሱ ይመጣል እንጂ።

አንተ እንዲህ ስትሠራ ልጅህን፣ ትውልድን በዚህ መልክ መቅረጽ ትችላለህ። ሰይፍን ቀጥቃጭ እንዲሠራው ዘወትርም ስለቱን እንዲጠብቅ፤ አንተም ልጅህን ትውልድንም ትሠራለህ እድገቱንም በስርዓት ትቀርጻለህ….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *