“ምን ሠርቼ ላግዛት?”

የቤት ውስጥ ሥራዎች(በተለምዶ የሴት የምንላቸው) ያንተን ወንድነት የሚፈታተኑ ከኾነና ወኔህን የሚያደርቁት ከኾነ ደምህን የሚሞሉ ወኔ መላሽ የኾኑ ምን ዐይነት ሥራዎችን ሠርተህ ሚስተህን ታግዛታለህ?

****በዋናነት ራስህን ኹንላት
ወንድሜ! ተፈጥሮህ ሰው ከሰውም ወንድ ሰው መኾንህን በአስተውሎት ተረዳ። በሰውነትህ(human being) ከሚስትህ ጋር አንድ ዐይነት ስትኾኑ በወንድነትህ ደግሞ ትለያታለህ። ይኼንንማ አውቀዋለሁ ትለኝ ይኾናል እኔ ግን ብዙዎች በተለይ ዛሬ ላይ የዘነጉት ተፈጥሮኣዊ ደግሞም መሠረታዊ እውቀት ነው እልሃለሁ።

አንተ ራስህን ስትኾን ሚስትህን ታግዛታለህ። ይኽም ወንድ በመኾን ፈንታ ልስልስ፣ ቅልስልስ፣ልፍስፍስ(በአካልም በአእምሮም)፣ ምስኪን እና ስሜታዊ ጠባይ ስታሳያት ትቸገራለችና። ልብ አድርግ! የመግቦቱን(nurturing) ሥራ ለእርሷ ስትተውላት ላንተ ስንፍና ማምለጫ በር ሳመቻችልህ እንዳይመስልህ፤በጭራሽ! ላንተ የተሰጠህ በዓይነቱ ልዩ የኾነ ሚና ስላለህ እንጂ። እንደውም የቤቱን ሥራ አውቀኸው ግን በተለይ ላንተ ወደ ተሰጠህና ወደተጠራህበት ሚና መምጣትህ ያንተን ብልህነት ያስረዳል።

ሚስትህን የምታግዝበት አንደኛው ጥሪህ
*****መሪነት ነው
ቤትህን ለመምራት መጀመሪያ አንተ ራስህ የምትሄድበትን ማወቅ ያስፈልግሃል። ያወቅከውን ዐላማ አድርገህ መስቀል፣ እርሱንም እንደምትጨብጠው ማመን ወደ እርሱም መዘርጋትና ቤትህን ማስከተል ነው።

ወንድሜ የአታላይዋን ዐለም የእኩልነት ስብከት እርሳ፤ ቤትህን የምትመራው አንተ እና አንተ ብቻ ነህ። ይኽን ስልህ “በምክሩ ሚስቴ የለችበትም እንዴ?” ብለህ ከኾነ እንዴታ ያውም በየድድ ማስጫው ትኩስ ሻይ አልያም ቀዝቃዛ ቢራ ሳይኾን በዙፋንህ(በአልጋህ) በክብር ተሰይማ ከእቅፍህ ትኩስ ፍቅር እየተጎነጨች አንተም ከብልኃቷ እየተቋደስክ እንጂ እልሃለሁ።

ቤትህን በመምራት ሚስትህን ካላገዝካት ከዚህ በተሻለ የምታግዛት ሥራ የለምና ሚስትህ ድብርት በተደጋጋሚ የሚያጠቃት፣ ጭንቀታምና ኃዘንተኛ ትኾናለች። አዎን በእርግጥ “እርሱ ማነው እኔስ ዐላማ ሰቅዬ አልመራም እንዴ” ትልህ ይኾናል። አንተ ግን ከእቅፍህ በጣፋጭ የፍቅር ጨዋታ ጠቅልለህ ከዚህ ቀደም ብዬ የነገርኩህን መግቦት(nurturing) ለእርሷ ተፈጥሮኣዊ ስጦታዋ እንደኾነ፤ እርሷንና ልጆቻችሁን ደግሞ በሕይወት መንገድ መምራት ያንተ ተፈጥሮኣዊ ጸጋህ መኾኑን አስረግጠህ ንገራት፤ ከምንም በላይ ግን በተግባር አሳያት።

*****ማስተዳደር
አንድ ተቋም(ትዳርንም ጨምሮ) በአንድ ዐላማ ሥር አባላትን ሰብስቦ ሲጓዝ ዐላማው ይፈጸም ዘንድ አባላቱ የሚተዳደሩበት የጋራ የአፈጻጸም ሥርዓት ይኖራቸዋል። የኼንንም ሥርዓት ወይም ደንብ በአመራር ደረጃ የተቋሙ የበላይ አካል ይቀርጻል፣ ያሳውቃል አፈጻጸሙንም ይከታተላል እንደኣስፈላጊነቱም ደግም ቅጥ ያጡ አፈጻጸሞችን የእርምት እርምጃ ይወስዳል፣ ያስወስዳል።

ልብ አድርግ! ሕይወትህን የምትመራበት ሥርዓት ከሌለህ የሰቀልከው ዐላማ ጋር ሳትደርስ ብኩን ትኾናለህ። ስለዚህም በቅድሚያ አንተ ቅጥ ይዘህ ከዚያም ቤትህን ቅጥ ታስይዛለህ።
ቤትህን ለማስተዳደር ያንተ ወርኃዊ ገቢ፣ ሰውነት፣የተወለድክበት የቤተሰብ የኑሮ ደረጃ ከእርሷ የግድ መብለጥ የለበትም። ምንም እንኳ በአስተዳዳሪነትህ የቤትህ አቅርቦት እንኳ በቀጥታ ቢመለከትህም ቅሉ ስንፍናና ንዝኅላልነት ካልኾኑ በቀር የእጅህ ማጠር(ድህነትህ)፣ የቁመትህ ማጠርም ኾነ ዐለማዊው ትምሕርት ሚናህን ሊያሳጡ አይገባም።

ስለኾነም በዚህ ማሕበራዊ እና ሀገራዊ ፋይዳዊ ከፍተኛ በኾነው ተቋም ሥር ያሉትን የቤተሰብህን አባላት ሥርዓት ቀርጸህ፣ አንተ ቅጥ ይዘህ እነርሱን በማስያዝ(መክረህ፣ገስጸህ፣ ተቆጥተህ፣ ቆንጥጠህ) ስተዳድራቸው ሚስትህን ታግዛታለህ።

***አርኣያነት
ትዳር በተሰኘው ተቋም ውስጥ በመንፈሳዊነትህ(በታማኝነትህ፣ በአዛውንት አክባሪነትህ፣ በሰው ወዳድነትህ፣ ፈጣሪህን በመፍራትህ….) ፣በሀገር ፍቅርህ፣ በታታሪነትህ፣ በተማሪነትህ አርአያ ልትኾናቸው ይገባል።

እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን ካላደረግህ ለሚስትህ ሌላ የሥራ ጫና ትፈጥርባታለህ። ባል ይኼንን ሚናውን ተረድቶ በአግባቡ የማይወጣ ሰነፍ ኾኖ ሳለ ሚስት የግዷን የእርሱን ሚና ደርባ ስትሠራ ኑሮ ሸክም ይኾንባታል። አዎ! ወዳጄ ሚስትህ ቤቱን ስትመራ፣ አንተንም ኾነ ልጆቹን ስታስተዳድር፣ የጥንካሬ፣የስኬት፣ የአሸናፊነት አርአያ ስትኾን ባንተ ስንፍና ላይ የበቀለ ፍሬ አልያም ባለመኖርህ መኾኑን አስተውል። ከአንደበትህም እንዲህ ሲወጣ እፈር “ልጆቹ እኮ እናታቸውን ነው የሚፈሩት(የሚሰሙት)”፣ “ምን ማድረግ እንዳለብን እርሷነች የምታውቀው” አትበል ምክንያቱም ያንተ ሚና ነውና።
ባሏ ለሞተባት ወይም ለተለያት ሴት ግን እነዚህ ጥረቶች ምንም እንኳ ሴትነቷን ዋጋ ቢያስከፍሏትም እስካላገባች ድረስ ብቸኛ አማራጮቿ ናቸው።…….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *