ራስህን ግዛ፤ ቃልህም ከግብርህ ይስማማ

ሳተናው!
ማደግ፣ መለወጥ መበልጸግም ትሻለህን? እንግዲያውስ ከቁሳዊ ስኬትህ በፊት ለፍላጎቶችህ ልጓም ለብልቶችህም ስርዓትን ሥራላቸው። አእምሮህ የሚያስበውን አይንህ ይመስክር፣ ምላስህም ይናገር፤ ምላስህ የተናገረውን እጅህ ይፈጽም፤ ሆድህ ላባውም ብቅልን አትፈልግ።

አንተ የምታስበውና የምትናገረው መያዣ መጨበጫ ከሌለው እንዴት አድርገህ ቤተሰብህን ትመራለህ? እንዴትስ ቃልህን አምነው ከሚውሉ ጋር መኖር ትችላለህ? ኧረ እርሱን ተወው፤ እንዴትስ ከራስህ ከህሊናህ ጋር አብረህ ትኖራለህ? ……. ውስጥህ እየነደደ፣ ጥርስህ እንዳገጠጠ፣ ሰው ይርቅካል እንጂ!

ሳተናው!
በግል የብቸኝነት ሕይወትህም ኾነ በምትመሠርተው ትዳር ውስጥ ትልቁ ሥራህ ዘወትር ራስህን በአእምሮ፣ በመንፈስ እና በአካል ብቃት ማሳደግ መኾኑን አጫውቼሃለሁ። ይኽንንም ለማድረግ ደግሞ ከራስህ ለምትጠብቀው ለውጥ ሌላ ማንንም ሳይኾን ራስህኑ ተጠያቂ ማድረግ እድገትህን ከማፋጠኑ በተጨማሪ ከራስህ ጋር በስምምነት እንድትኖር ያስችልሃል።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ቤተሰብ መሪነትህ ከሚስትህ፣ ከልጆችህና ከሌሎችም የቤተሰብህ አባላት በቤትህ ውስጥ እንዳላቸው ሚና ያስቀመጥክላቸው ግብ፣ የምትጠብቀውም ልክ መኖር አለበት። ከዚህም የተነሳ እነርሱ ወዲዚያ ግብ ሲያቀኑ እድገታቸው የማያጠያይቅ አለመኾኑ ብቻ ሳይኾን ለኑሮኣቸው ትርጉም ያገኙለታል።

ይኹንና አንተ ለራስህ ቃላባይ፣ በተናገርክበት የማትገኝ፣ እንኳን ለሰው በሰጠኸው ቃል አይደለም በራስህም ለራስህ ያልተገኘህ ከኾነ ሚስትህን እንደ አባወራ መምራት ልጆችህንም በስርዓት መግራት አይቻልህም። ከሞከርከውም አምባገነን ከመኾን፣ በዚህም ሚስትህንና ልጆችሀነ ከማስጨቅን ወጪ የምታተርፈው የለም።

ሳተናው!
ይኼንንም ስነግርህ ወይም ደግሞ ሌሎች ወዳጆችህ ሲነግሩህ በስብዕናህ ከፍ እንድትል ልቀህም እንድትገኝ እንጂ ነው። አንተ ከራስህ የምትጠብቀውን፣ ለሰውም ከሰጠኸው ቃል ማሳካት ስትችል በራስ መተማመንህ ይጨምራል ሌሎችም ባንተ ላይ ያላቸው እምነት ይጠነክራል።

እንደዚሁም ከሚስትህ የምትጠብቀው ልክ፣ ለልጆችህም የወሰንክላቸው ከፍታ ሲኖር ዘወትር በማደግ ኺደት ላይ ይኾናሉ። ይኽን ለመወጣት ግን መሪያቸው አንተ ስሜትህን የገዛህ፣ ቃልህ ከምግባርህ የተስማማልህ፣ በብልቶችህም ላይ የማዘዝን ስልጣን የተቀዳጀህ መኾን አለብህ። ምክንያቱም ካንደበትህ ይልቅ ምግባርህ ይመራቸዋልና።

በሚስትህና በልጆችህ ፊት የሚታይና የሚመሠክሩለት የማይለዋወጥ፣ የማይቋረጥ በፈተና ውስጥም ማለፍ የሚችል ልምምድን አሳያቸው። በጠዋት መነሳትህ፣ ስፖርት መሥራትህ፣ ጸሎት መጸለይህ፣ መጽሓፍ ማንበብህ፣ አመጋገብህ፣ አነጋገርህ ሁሉ ምሳሌ ሊኾናቸው የሚችል ይኹን።

ሳተናው!
አደራህን ራስህን ሳትገዛ፣ በቃልህ መገኘትም ዳገት እየኾነብህ “አባወራ ነኝ ቤቴን እመራለሁ” ብትለኝ እኔ ግን “አምባገነን ነህ እንኳን ሚስትህን(ቤትህን) አንድ ራስህን አትገዛም፣ በራስህ ቃል የማትገኝ አንተ ሚስትህንም ኾነ ልጆችህን በቃሌ ተገኙ ስትል አታፍርም ወይ” እልሃለሁ።

ይቆየን

ቴሌግራም
https://t.me/abawera

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *