ራስህ ላይ ትሰለጥን ኃይልንም ትታተቅ ዘንድ

ሳተናው!
አንተ ንጉስ የንጉስ ልጅ፣ ጀግናም የጀግና ዘር ነህ። ዛሬ ተጎሳቁለህ ተልፈስፍሰህ አቅመቢስ ብትመስልም ስሜታዊ ኾነህ ማንም ቢነዳህም ውስጥህ ግን ወደ ተፈጠርክበት ንግስና ወደ ጀግንነቱም መመለስ ይችላል።

ይኽ ግን አንተ ስትፈልግ፣ እንደምታደርገውም ስታምን፣ ስታደርገውም ብቻ የሚኾን ነው። ጀግናው ከማያከብሩህ (ከሚንቁህ) ጋር ጊዜህን አታጥፋ። አንተም ራስህ ብትኾን ለራስህ የስንፍናን ቃል አትናገር። ይልቁንስ ተፈጥሮኣዊ ኃይልህን ከሚያድሱልህ ጥንካሬያቸውን ከሚያጋቡብህ ሰዎች ጋር ዋል። እውነትንና እውቀትን ከሚያቀብሉህ መጻሕፍት ጋርም ተነጋገር።

እኔ በሕይወት ውጣውረድ የተጠቀምኩባቸውን ኃይል የኾኑኝንም አሥር ነጥቦች ላቀብልህ። ነገር ግን “እነዚህ ብቻ ናቸው” እያልኩህ አይደለም። ሌሎች የማላውቃቸው፣ አውቄያቸውም ገንዘብ ያላደረግኳቸው አሉ። በመዳፌ ሥር ያለፉትን ልስጥህ ብዬ እንጂ።

፩ መጻሕፍትን አንብብ
“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” ሲባል ሰምተሃል፤ እውነት ነው። እውነት ከኾነ ደግሞ ዋጋ ከፍለህ የሕይወት ዘመን ልምምድ ልታደርገው ይገባል። እመነኝ አንባቢ ትውልድ ስናፈራ ራሳችንን፣ ትዳራችንን ብሎም ሀገራችንን በብዙ መቀየር እንችላለን።

አኹን አኹን ግን እኮ አንብቦ መረዳት፣ መርምሮ መቀበል መዝኖም መፍረድ የማይችል ትውልድ እያፈራን ነው። ከዚህም የተነሳ ትውልዱ ስሜታዊ ሲኾን ስሜቱንም መቆጣጠር ሲያቅተው የብልጣብልጦችም መጠቀሚያ ሲኾን እያስተዋልን ነው።

አንተ ግን በየትኛውም መስክ ልቀህ ለመገኘት ማንበብ ኹነኛ መሣሪያህ ነው። አየህ ስታነብ ማንነትህን ትረዳለህ፣ ንጉስነትህን በፍጥረት ላይ ልትሰለጥን መፈጠርክን ትገነዘባለህ፣ ያንን ማንነትም ለመኖር/ለመኾንም ትጥራለህ።

የሰው ልጅ ከፍጥረት መለያው በእነርሱም ላይ እንዲሰለጥን የረዳው ኃይለኛም ያደረገው አእምሮው ነው። ስለ ተፈጥሮህ ስታነብ ራስህን ታውቃለህ፤ ያወቅከውን ማንነት ስትኾን ደግሞ ታይላለህ።

፪ ራስህን ኹን
ምንም ብታነብና ምን ብትመረምር ከሰዎችም ልምድ ብትቀስም አንተ ግን በራስህ ከሌሎች ልዩ ነህ።ሌሎች በሰውነት ቢመስሉህም አንተ ግን አንድ አንተ ነህ። እንደግለሰብ ብቸኛው፣ የራስህ ማንነት ያለህ፣እንደማሕበረሰብ አባል ደግሞ የራስህ ባሕል፣ እንደ ዜጋ ደግሞ የራስህ ሀገር እና ባንዲራ የተቸርክ ነህ።

ከሰዎች መማርህ እውቀትንም መቅሰምህ እነርሱን እንድትመስል ሳይኾን ራስክን እንድትኾን እርሱንም እንድታሻሽል እንጂ። አንተ ራስህን ስትኾን ደፍረህ ራስህን መግለጽ፣ ነጥረህም ከሰው መሐል መውጣት በሙሉ ስልጣንና ኩራትም መመላለስ ይቻልሃል።

አልያ ግን የሰውን ሥራ እንደራስህ፣ የተውሶ ባሕል እንልብስህ፣ የሌሎችን ጉትቻ እንደ ግልህ ብታጊጥባቸው ፤ አቅመ ቢስ፣ ፈሪ ፣ ለራሱ ዋጋ የሌለው፣ ባለውም የማይኮራ ብኩን ቢያደርጉህ እንጂ አይጠቅሙህም። ወዳጄ! የሰው የኾነው ኹሉ የሰው ነው። አንተ ደግሞ የራስህ ነህ።

፫ ስሜቶችህን ግዛ
ሳተናው ራስን መግዛት ቁርጥ ውሳኔንና ከባድ ልምምድን ይሻል። ነገሩ እንዲህ ነው፦ ራስክን ለመግዛት የምትገዛው አንተን ማወቅ ይቀድማል፤ ጀበና ማንነቱን ለማወቅ ሸክላ ሠሪው ጋር ቢሄድ አግባብ እንደኾነ አንተን ደግሞ ራስህን ለማወቅ ፈጣሪህ ጋር መሄድህ ያጻፈልህንም ማንበብ ተገቢ ነው፤ ያነበብከውን አንተን በሕይወት መኖር(ራስህን መኾን) ልምምድ ሲኾን ራስክን መግዛት ስትችል ብቻ ገንዘብ ታደርገዋለህ።

ሚስትህንና ልጆችህን በዓላማ፤ በሥራ ገበታህም ላይ በሥርህ ያሉትን ለአንድ ግብ ስሜታቸውን ገርተህ ከማሳደርህ በፊት አንተ የራስህን ስሜቶች ለተፈጠሩለት/ለተፈጠርክበት ዓላማ ይውሉ ዘንድ ግዛቸው አሰልጥናቸው። የኋለኛውን ካልቻልክ የፊተኛው አይኾንልህም።

፬ ራስህን ምራ
ራስህን መግዛት ስሜቶችህንንም መቆጣጠር ስትችል በዙሪያህ የሚከሰቱት ነገሮች ባንተ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ እየቀነሰ ይመጣል። ይኽ የሚኾነው ተጽዕኖ ስለማይኖራቸው ሳይኾን አንተ ስለማትፈቅድላቸው እንጂ። ስሜትህን ገዝተህ በዓላማ ስትመላለስ የት፣ መቼ፣ እንዴት መሄድ እንዳለብህ ሰዎች ሳይኾኑ አንተ ራስህ ትወስናለህ።

ሳተናው ልብ አድርግ ራስክን ስትመራ ብቻ ቤትህን፣ ትዳርክን፣ ሚስትህንና ልጆችክን መምራት ይቻልሃል። ከእንዳንተ ዓይነትም አብራክ ኹነኛ የሀገር መሪ ይገኛል።

፭ ራስክን ቻል

ወንድሜ በእድሜክ ኹሉ ከሰው ጥገኝነት ተላቀቅ። ከሰው አትረዳዳ፣ አትደጋገፍም አይደለም ነገር ግን መሠረታዊ ፍላጎቶችህን በራስህ በላብህ በወዝህ ጥረት አሟላቸው ለማለት እንጂ። በሰው ላይ ጥገኛ ስትኾን በራስህና በመንገድህ ላይ መወሰን ይከብድሃልና።

፮ ስፖርት ሥራ

ማየልህ በአእምሮ ብቻ ሳይኾን በአካልም እንደኾነ አንድም ደግሞ ለአእምሮህ ብቃትም ስለሚያግዝህ ሰውነትህን በስፖርት አሰልጥነው። አእምሮህ በደረሰበት ርቀትና ምጥቀት መጠን ሰውነትህ ታዞ እንዲሠራ ይኹን። አልያ ግን የተልፈሰፈሰ ሰውነት የዛለ ጡንቻም ይዘህ አቅመቢስ ብትኾን እንጂ ኃይለኝነት ሲያልፍም አይነካካህ።

፯ ጾምን ተወዳጃት

ብዙዎቻችን ስለጾም ጥቅም ብንጠየቅ መንፈሳዊ ዋጋውን ከመጥቀስ ውጪ ለስጋችን ስላለው ፋይዳ፣ ለአእምሮኣችን ምጥቀት ስለሚሰጠው ጥቅም ምን ያክል እናውቃለን? አንተ ሳተና! በየትኛውም ኃይማኖት ውስጥ ኹን እንደ ጾም በሰውነትህ ላይ ልዕልና በስሜቶችህም ስልጡን የሚያደርግህ መሣሪያ የለም።

ቀላል ምሳሌ፦ “መኪና ሙሉ ሰርቪስ ይደረጋል” ሲባል ሰምተሃል? አዎን ሞተር አውርደው የሚሰጡትን አገልግሎት ነው የምልህ። በዚህ ጊዜ የመኪናው የውስጥ ክፍሎች የተለመደውን አገልግሎት አቁመው የሚታደሱበት ወቅት ነው። መኪናው ይኽንን የእድሳት ሥራው አልቆለት ከጋራዥ ሲወጣ ወደ መጀመሪያው(የፋብሪካ) አቋሙ ይመጣል(ከተሳሳትኩ ልታረም)።

አንተ በምትጾምበት ጊዜም ሰውነትህ ከውስጡ መርዛማ ንጥረ ነገሮችንንም ኾነ ትርፍ የምግብ ክምችቶችን ያስወግዳል። በዚህም ወደ ተፈጥሮኣዊውና ውጤታማ የሚያደርግህ አካላዊ ብቃት ይመልስሃል። ….ይቆየን

የሚከተሉትን በኢሜይልህ እልክልሃለው.
፰ ወሲብን በቋሚነት ያለድርድርና ልመና ከሚስትህ…
፱ ለትዕግስትህ ገደብ፣ ለይቅርታህ ልክ፣ ለፈቃድህም ወሰን አብጅለት

፲አመስግን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *