ሴት ልጅ በልቧ ጀግናን ታከብራለች

ሳተናው!
ስለሴቶች ማወቅ ካለብህ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ልባቸው ለጀግና እንደሚሸነፍ ነው። የትኛዋም ሴት ልፍስፍስ፣ ደካማና በራሱ የማይተማመን ወንድ አትሻም። በትዳር ተሳስረህ አብረህ መኖር ጀምረህ ቢኾን እንኳ ኋላ ላይ መልፈስፈስ ቢታይብህ ላንተ ያላት ስሜት እየቀዘቀዘ መኼዱ እሙን ነው።

ወንድሜ አኹን ላይ ዐለም ወንዶችን ፈሪ፣ ስሜታዊ፣ ጭፍን፣ ልፍስፍስና ወኔ ቢስ እያደረገች እያሳደገች ነው። ይኼ በየመገናኛ ብዙኃኑና በየተቋማቱ የሚሠራው ወንዶችን ለስላሳና ምስኪን ማድረግ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና በደል ለመቀነስ ታስቦ እንደኾነ ይተረካል። ችግሩ ግን ወንዶች ለስላሳና ምስኪን እየኾኑ በኼዱ ቁጥር ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በዓይነትም ኾነ በቁጥርም ይጨምራል እንጂ አይቀንስም።

ከዚህም የተነሳ የዚህ ዘመን ወንድ ከየትኛውም አቻዎቹ ከኖሩበት ዘመን የወረደ ከሴቶችም ጋር የማይገጥም ወንድነት ሊኖረው ግድ ኾኗል።

ሳተናው ወንድሜ! ስለ ሴት ልጅ የመገናኛ ብዙኃኑ ለሚለፍፉት ውሸት ቦታ አትስጥ። ይልቁንስ አንተንም ኾነ እርሷን የፈጠረ ሥሪታችሁንም ለሚያውቅ የፈጣሪህ ቃል ጆሮህን ስጥ በልብህም አስቀምጠው። እርሱም እንዲህ ይላል፦
1ኛ የጴጥሮስ መልእክት ም3 ቁ 7
” እንዲኹም እናንተ ባሎች ሆይ ደካማ ፍጥረት ስለኾኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሯቸው።”

ሴት ልጅ ምን ዓለማዊ ብዕል(ኃብት)፣ እውቀት፣ ስልጣን ቢኖራትም ቅሉ ልቧን ከማንኛውም ዓይነት ስጋት የሚያሳርፋትን ለተሸናፊው ስሜቷ ብርታት የሚኾናትን ወንድ ትፈልጋለች።

ይኽ ከእውቀት ማሕደርህ ልትጨምረው የተገባህ መሠረታዊና ተፈጥሮኣዊ እውነት ነው። በየትኛውም አጋጣሚ ሴት ልጅ የወንድ ወዳጅ የትዳርም አጋር ስትሻ ጀግና ወንድን ትፈልጋለች እንጂማ “እወድሻለሁ”፣ “ካላንቺ ሕይወቴ ባዶ ነው” “ሲያምሽ ያመኛል” እያለ የሚያላዝንባት ፍላጎቷን ቢዘጋው እንጂ ቦታም አትሰጠውም።

ከእቅፉ መግባት፣ ክንዱንም መንተራስ፣ እግሯንም ማንሳት ልቧ የሚፈቅደው ግን ለጀግናው ነው። ይኽ ጀግና ምናልባት በማሕበረሰቡ ዘንድ “ዱርዬ” ቢባልም እንኳ። ምክንያቱ ደግሞ ደካማ ጎኗን ደካማ ሳይል ድካሟን ግን አውቆና ተረድቶ በእርሱ ድፍረትና ጀግንነት ያድሳታልና ነው።

አንተ ወንድሜ ሴትን ልጅ በምንም ዓይነት መልኩ አሳዝነሃት፣ ራርታልህ፣ውለታም አብዝተህባት (አስተምረሃት፣ እናቷን አስታመህላት፣ አባቷን ጦረህላት) እንድታገባህ አታስገድዳት፤ በጭራሽ ስልህ!

ኾኖም ግን ከውለታው የተነሳ፣ አንድም አማራጮችን ከማጣት የተነሳ፣ ባጋጣሚዎችም ተገዳ፣ በተሳሳተው ዘመንኛ መረጃም ተነድታ ምስኪኑን ልታገባ ልትወልድለትና 10፣20ና 30 ዓመትም ሊኖሩ ይችላሉ ነገር ግን ልቧ አርፎ አይደለም።

ሴቶች ልፍስፍስና ምስኪን ወንድ ለትዳር እንደማይኾን ደመነፍሳቸው ይነግራቸዋል።ወንድሜ ምስኪንነትህን በማጉላትህ ሴቶች ቢቀርቡህ ወንድማቸው እንድትኾን ከመፈለግ ውጪ ሌላ ቅንጣት ታህል የወሲብ(ጾታዊ ግንኙነት) ዝንባሌ እንደማይኖራቸው እወቅ።

ብታገባህና ብትወልድልህ እንኳ ልቧ ተማርኮና ተሸንፎልህም ሳይኾን የስጋ ገበያው ካቀረባቸው ወንዶች ውስጥ ለትዳር የሚኾን(ቤተሰብ መመሥረት የሚችል) ወንድ ብሎ አንተን ብቻ ስለሰጣት እንጂ። ዱርዬውና ሴት አውሉ ቤተሰብ መመሥረት አይኹንላቸው እንጂ ከምስኪን በብዙ እጅ እንዲሻሉ አስረግጣ ታውቀዋለች።

ይኹንና የሕሊና ዳኝነት ችሎት ባጣበት፣ ሞራላዊ እሴቶቻችንም በተሸረሸሩበት በዚህ ዘመን አንዲት ሴት አንድ ልፍስፍስ ምስኪን ከምታገባ ሕሊናዋን ሸጣ ከዱርዬ ወይም ከሴት አውሉ ጋር መዳራቱን ትመርጣለች። በዓለም የምታየውም ይኽን ይመሰክራል።

ለዚህ ደግሞ እርሷ ሳትኾን እኔና አንተ ተወቃሽ ነን። “እንዴት?” አልከኝ እንዴት ማለት ጥሩ። ፈጣሪ የባሕርይ በኾነው ጥበቡ የፈጠረውን ፍጥረት ሲያውቅና እንዲህም ኑሩ (…. ደካሞች ስለኾኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል ኑሩ….) ስንባል(ልንጀግን ሲገባን) ምስኪን ኾነን ልናሳርፋቸው ስላልቻልን ለእነርሱ ለማይጨነቁት ሴታውልና ዱርዬ አሳልፈን ስለ ሰጠናቸው ነው እልሃለሁ።

ሳተናው ወንድሜ!

እባክህን ያስወድደኛል፣ ከእረሷ ያቀርበኛል ብለህ ፈተና ሲገጥምህም ኾነ ሲበረታብህ ሚስትህ ፊት አታላዝን። ስታዝን አይታ የምትደነግጥልህ አንድ እናትህ ናት። ሚስትህ ግን ላንተ ሳይኾን ለራሷና ለልጆቿ ነው የምትደነግጠው። ” ይኼ ሰው ለራሱ እንዲህ ከተርበተበተ እኔንም ኾነ ልጆቼን እንዴት መታደግ ይችላል?” ማለቷ የማይቀር ነው።

ልብ አድርግ! ሴት ልጅ ለጀግና ብቻ ልቧ ይማረካል ብሎም ይሸነፋል!
ዝም ብለህ ዓመታትን ስለቆጠርክ “የኔ ሚስትማ ልቧ ከኔ ጋር ነው እተማመንባታለሁ” አትበለኝ። ይልቅስ ትወደኛለች ብለህ ከምትንሰፈሰፍ እንድታከብርህ ጀግን።

ከምትወድህ ሴት ይልቅ የምታከብርህን…… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *