ሴቶች ምን ይፈልጋሉ?

ሳተናው!
አንተ በአባወራነትህ ራስህን በመገንባት ሂደት የሴቶችንም ተፈጥሮኣዊ ባሕርይ እያወቅህና እየተረዳህ መሄድህ ትልቅ ትርፍ ነው።

ይኸውም አብረሃት የምትኖራት ሴት የምትፈልገውን ሳይኾን የሚያስፈልጋትን አውቀህና ተዘጋጅተህ ካልተገኘህ በስተቀር ዘወትር አንተ እርሷን ለማስደሰት ስትዳክር እርሷ ግን ጥረትህን ከምንም ሳትቆጥር ትኖራለችና ነው።

ርዕይ ሰንቀህ፣ ዓላማ ሰቅለህ መጓዝ የማትችል ዘወትር ከስሜታዊነቷ የተነሳ ደስታዋ ለቅጽበት ሲሰበሰብ ደግሞም እንደ ጉም በኖ ከፊቷ ሲጠፋ እያየህ ቀንህን የምትጀምር ከኾነ አንተ ብኩን ነኽ። ከዚኽ የተነሳም የሕይወት መርሕ ሥርዓት የሌለህ ነህና ልጆች ወልዳ የምታሳድግበትን ትዳር፣ ቤት የመምራት ብቃቱ እንደሌለህ ትገነዘባለች። ስለኾነም በትዳርህ ውስጥ ማትረፍ ከፈለግህ እነኾ እነዚህን አጢን፦

፩ኛ ሴቶች ሥነ-ሥርዓት ይዞ እነርሱን፣ ቤታቸውን(ትዳራቸውን)፣ ልጆቻቸውን ሥነ ሥርዓት የሚያሲዝላቸው ወንድ ይፈልጋሉ፤ እንዲህ ብለው ግን አይነግሩህም።

፪ኛ የሚሠማሩበትን ድንበር የሚያሰምር እርሱንም የሚያስጠብቅ፣ የሚጠብቅና የሚጠብቃቸውም ወንድ ይፈልጋሉ፤ ይኼንንም አይነግሩህም። 

ከእነዚህ ሁለቱ ውጪ የሚያገኙትን ወንድ ግን ምን “እወድሃለሁ” ቢሉት ልባቸው የማይከፈትለት፣ ክብር የማይሰጡት ከዚኽም የተነሳ ከፍላጎታቸው የማያሳርፋቸው ለንቀትም ተላልፎ የተሰጠ ይኾናል።

፩ኛ ሴቶችና ሥነ-ሥርዓት

ሳተናው!

አንተ የቤትህ ራስ ተደርገህ የተሰየምክበት ኃላፊነት በይበልጥ የሚታየውና የሚመዘነው ቤትህ የሚመራበትን፣ ሚስትህ የምትከተለውን፣ ልጆችህን የሚያንጸውን ሥርዓት መዘርጋት፣ ማስጠበቅና ማስቀጠልም ስትችል ብቻ ነው። ካለበለዚያ ግን ቤትህ በእማወራ ቢተዳደር እንጂ ያንተ አባወራነት የሠርግ እና ተዝካር መጥሪያ ወረቀት ከማድመቅ የዘለለ ሚና አይኖረውም።

ነገር ግን ሥርዓትን ለመቅረጽ፣ ለማስጠበቅ እና ለማስቀጠልም ደግሞ መጀመሪያ አ.ን.ተ.ው. ራስህ በወላጆችህ በሥነ-ሥርዓት ታንጸህ ያደግህ አልያም ራስህን በሥነ-ሥርዓት የገራህ መኾን ይጠበቅብሃል።

አለበለዚያ ግን አንተ ጋር የሌለውን ከየት አምጥተህ በቤትህ ትዘራዋለህ? ወዴትስ አብቦ እንዴትስ ኾኖ ለፍሬ (ለትውልድና ሀገር) ይደርስልሃል?

ሳተናው!
አንተን ከሰነቅከው ርዕይ፣ ከሰቀልከው ዓላማ፣ ካስቀመጥከው ግብ ጋር የሚያገናኝህ ድልድይ ቢኖር አንድ እርሱም ሥነ-ሥርዓት ነው። ሥነ-ሥርዓት ሥነምግባር ማለት አይደለም ። እነዚህ ሁለቱ ብዙውን ጊዜ የሚምታቱ ርዕሶች ቢኾኑም አንድ ወንድ በአባወራዊ ጉዞው ለይቶ እና አንጥሮ ተረድቶ ገንዘብ ሊያደርጋቸው የሚገቡ እሴቶች ናቸው።

ሥነ-ሥርዓት ወደ አንድ ወደ ተወሰነ ግብ ለመድረስ የምንሄድበትን(የምንሠራበትን) መንገድ ፣ መጠን፣ አቅጣጫ፣ ፍጥነት ሥራውን በሚመራው አካል (በእኛ ዐውደ ንባብ አባወራ) ተለክቶ፣ ተሰፍሮና ተወስኖ  የሚሰጠን ከእርሱም የተነሳ ከግባችን የምንደርስበት ነው።

ታዲያ ይኼንን ሥነ-ሥርዓት በተለይ ሴቶች ዘርን ከእኛ ወስደው፣ አርግዘው፣ ወልደውና ተንከባክበው ለማሳደግ ሲሉ በእጅጉ ይሹታል። ኾኖም ግን የሴታቆርቋዡ አመለካከት (Feminism) ሴቶቻችንን ሴትነታቸውን ክደውን ወንድነትን ካላበሰ የወንዶቻችንንም ሥነልቦና ሰልቦ አልጫ ካደረገ ወዲህ ሴቶቹም ይኼን ፍላጎታቸውን በግልጽ በአፋቸው አይናገሩትም፤ ወንዶቹም አይኖሩበትምና አያኖሩበትም።

ከዚኽም የተነሳ ራሱን በሥነ-ሥርዓት ያለማኖር ስንፍና ሌሎችን(በተለይም ሚስቱንና ልጆቹን) በሥነ-ሥርዓት ያለማኖር ፍርሃት ይዞት ነገር ግን በ”ፍቅር አምናለሁ” ፣ በ”ውይይት አምናለሁ” እያለ ራሱን ይሸውዳል።

ስለኾነም እርሱ አቋም የለሽ አልጫ ሲኾን አንድ ቀን አቋም ቢይዝ ኢ-ምክንያታዊ የኾነ ግትር(አንባገነን) ይኾናል። ሚስቱም የተማረችው ዶክትሬትና ማስትሬት ሳይመክራት(ሳያንጻት) ቀርቶ አይደለም ተግባሯ ከአንደበቷ የሚወጣው ቃል እንኳ ሥርዓት አልባ ይኾናል። ከልጆቹስ ምን ይጠበቃል? ምን ምሑራን ቢባሉም ያልተማሩ አባቶቻቸውን የሠሩትን ሥርዓትና ሀገር ከማፍረስ ውጪ ፋይዳ የላቸውም።

ዛሬ ታዲያ አብዛኛዎቹ ሴቶቻችን (ሁሉም አላልኩም እማወራዎች አሉና) በግልጽ ቃል ባይናገሩትም እንኳ ትንሿን ሀገር፦ትዳራቸውን፣ በሥነ-ሥርዓት የሚያስተዳድር ራሱንም እንዲሁ የሚመራ እርሱንም የሚያሰፍን ወንድ እርሱም አባወራን ይፈልጋሉ። 

ነገረ ግን እንኳን ሰውን በሥነ-ሥርዓት ማኖሩ ቀርቶ ለራስ መኖሩም ከፍተኛ ብርታት ይጠይቃል። ማናችንም ብንኾን ታዲያ ሁለት ዋጋ የሚያስከፍሉ አማራጮች አሉን፦ በሥነ-ሥርዓት ለመኖር ዋጋ መክፈል አልያም ኋላ ላይ የቁጭትን ዕዳ ማወራረድ። ይኽ እንግዲህ ወደድክም ጠላህም ጣፈጠህም መረረህም ተፈጥሮኣዊ ሐቅ ነው!

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *