ስለትዳር የማታማክራቸው ሁለት ሰዎች

ሳተናው!

ስለትዳርና ስለምትመርጣትም ሴት ጭምር አንስተህ ልታወያያቸው፣ ልታማክራቸውና ሀሳባቸውንም ልትቀበላቸው የማይገቡ በተለይ ሁለት ሰዎች አሉ። እነዚህም ምስኪንና ሴታውል ናቸው፤ “እንዴት?”

እንዴት ማለት ጥሩ
ምስኪን ስለሴት ያለው አመለካከት ከተፈጥሮ የራቀ፣ በፍርሃትና በአጉል”ፍቅር” የታጠረ፣ በ”ስልጣኔም” የታወረ ነው። እርሱ የሚቀርባቸውን ሴቶች ከያዙት እሴት፣ ካደጉበት አስተዳደግና የቤተሰብ መሠረት እንዲሁም ትውልድን ለማስቀጠል ካላቸው የጋራ አቋም የተነሳ አይመረምርም።

ይልቁንስ በስሜት ተነድቶ ያገኛት ላይ ወዳቂ፣ “ካለእርሷ ምንም ነኝ” ባይ ድቃቂ፣ “ሴት ከእርሷ ውጪ” ብሎ ተመጻዳቂ፣ የመሠረተውን ሳይገነባ የሰው አድማቂ፣ የእርሱ እየቀዘቀዘ የሰው አሟሟቂ ነው ።

ወንድም-ዓለም! ስለሴት ምርጫ፣ ስለትዳር እና ኑሮውም የተፈጥሮን ሕግን(ተፈጥሮኣዊ ግዴታውን) መፈጸም ከማይችል፣ ከፈጣሪው ትዕዛዝ ይልቅ የብልጣብልጧ ዓለምን ተረክ የሚያስቀድም፣ በፍርሃትና በስንፍና ተሸብቦ ከሚኖር ምስኪን ምክርን አትስማ።

እርሱ ተቀመጥበት የተባለውን ወንበር ምራበትም ተብሎ የተሰጠውን በትር በእኩልነት ስም ለሚስቱ ሰጥቶ አደግድጎ የሚሰናበት “እሜ..ት” ብሎም የሚመለስ ሚናው የጠፋበት፣ ዓላማውን የዘነጋ ርዕይ አልባ ነው።

መለየት
ይኼን ታዲያ በምን ልለየው ካልከኝ ደርሶ በሰው ሁሉ ተወዳጅ ለመኾን ሲከጅል፣ ከሁሉ በሁሉ ሲስማማ፣ ውዳሴን(በተለይ በሴቶች) ሲወድ፣ መጠላትን ሲፈራ ታገኘዋለህ።

ለምን ምክሩን አትሰማም?
ምክንያቱም እርሱ ደረቅ ተፈጥሮኣዊ ሐቅን፣ በዚያም ባለ እውነት ራሱን አበልጽጎ መኖር ከጠማማዋ ዓለም ስለሚጋጭበትና ፈተና ላይም ስለሚጥለው ከመጋጨት ይልቅ ተሞዳምዶ መኖርን ይመርጣልና ነው። ከዚህም የተነሳ ከተፈጥሮው አቅም በታች ከተጠራለትም ዓላማ በራቀ፣ በተውሸለሸለ እና ፈቀቅም በማይል ኑሮ ስለሚዳክር።

ሴታውልንስ?
ሳተናው! ስለምትመርጣት ሴት፣ ስለትዳርና መጪው ሕይወትህ በጭራሽ ከሴታውል ጋር አትማከር። ሴታውል ከአልጫና ምስኪን በተለየ መሠሪ ነው። ከእነርሱም በዋነኛነት የሚለየው የሴትን ልጅ ተፈጥሮ ጠንቅቆ ማወቁ ነው። በዚህም ላይ የአንደበቱ “ማር”፣ ከአለባበሱ ማማር ጋር ተጨምሮ እንኳን ሴቷን አንተን ያስትሃል፤ ስለዚህም በእባብ ይመሰላል።

እርሱ የወሲብ ሱሰኛ ነው። ይኼም ሱሱ ቦታን፣ ጊዜን፣ ሴትን አያስመርጠውም። በደረሰበት ቦታ፣ ባገኘው ጊዜ ሁሉ ከሴት ለመተኛት ይመቻቻል፤ የሚተኛትን ሴትም ባለትዳር ነች፣ ዘመዴ ነች…. ብሎ አይመርጥም። ሴሰኝነቱ ክፉኛ እርሱን ከመጣባቱ የተነሳ አግብቶም ኾነ የፈለጋት ሴት አግብታ ወደኋላ አይልም። “ድመት መንኩሳ ዓመሏን አትረሳ” እንዲሉ።

ታዲያ አንተ እንዲህ ዓይነቱን ወንድ ስለምትመርጣት ሴት ማማከር ማለት እርሷን አሳልፈህ መስጠት፤ በትዳርህም ስላለው ክፍተት ማወያየት ማለት በሽንቁሩ ሽብልቅ እንዲሰድ መፍቀድ ይኾናል።

ሳተናው!
ሴታውል ሴሰኛ ስሜቱ የተቆጣጠረው፣ የሚገዛውና የሚነዳውም ነው። ለዚህ ዓላማው ሲንቀሳቀስ እንደ ድመት አድብቶ፣ እንደ እባብም ለስልሶ ነውና በአንተም ኾነ በትዳርህ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው።

ሴቶች ልባቸው በሴታውል ይሸነፋል። አንተም መሠሪነቱን፣ ክብረ-ቢስነቱን፣ ዓላማ-ቢስነቱንና ሴሰኛነቱን ተረድተህ ካንተ፣ ከሚስትህና ከትዳርህ ልታርቀው ይገባል። እርሱ የሚፈልገውን እስኪያገኝ ድረስ እነርሱ(ሴቶች) መስማት የሚፈልጉትን፣ ያልኾኑትንና የሚመኙትን ወዳሴ ያዘንብላቸዋል እንዲሁም የፈለጉትን ቢናገሩ ይሰማቸዋል። በዚህም ለእነርሱ ከባላቸው የበለጠ የሚረዳቸውና የሚረዳቸው(ጠብቆና ላልቶ ይነበብ) ይመስላቸዋል። እርሱ ግን የስሜት ሞገዱን በእነርሱ ልክ የሚያደርግበት ሌላ ድብቅ ዓላማ ስላለው እንጂ።

ሴቶች “ከባሌ የበለጠ የሚረዳኝና የሚረዳኝ ወንድሜ እርሱ ነው” ሲሉ….. እዚያ ቤት የባል ሚና ተከልሷል ማለት ነው።

ሳተናው! ዘወትር እንደምነግርህ የሴቶች ስሜት እንደ ባሕር ማዕበል ነው። ወጣ ስትለው ይወርዳል ጸጥ ብሎ ዋለ ስትለው ከእግርህ ስር ይነሳል። በባሕርም ማዕበል አቅራቢያ ሁለት ዓይነት ነዋሪዎች አሉ፦

?አንደኞቹ ማዕበሉ ሲነሳ እንደማዕበሉ ጠባይ አብረው ብድግ ቁጭ የሚሉ፣ እዚህ ጋር ናቸው የማይባሉ፣ ባሉበት የማይጸኑ ከባሕሩ ለመጠቀም ሲሉ ብቻ አብረው የሚነሱና የሚቀመጡ፣ ለጥቅማቸው አድልተው የሞገዱን ግብር ግብራቸው ያደረጉ ናቸው(የውሃ ላይ ኩበቶች)።

?ሁለተኞቹ ከባሕሩ ዳር ያሉት አለቶች ናቸው። እነርሱ የመርከቦች ማረፊያ፣ የባሕረኞች ምልክት፣ የሞገዱም መቆሚያ ናቸው። በተፈጠሩበት ቦታና ልክ የባሕሩን ድንፋታና ግጭት ታግሰው ነገር ግን ባሕሩን በቦታ አርግተውና ቅርጽ ሰጥተው ያኖሩታል።

የቀደመውን ለሴታውል የኋለኛውን ለአባወራው አድርገህ ተርጉም።

ወንድምዓለም!
የሴትን ልጅ የስሜት ጠባይ እንዲህ በምሳሌ የምነግርህ ታተርፍበት በዓላማም ትኖርበት ዘንድ እንጂ ለፌዝና ለጨዋታ አይደለም።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *