ስሜቱን መቆጣጠር የሚችል (ለሴቶች)

ውቢቷ!
ሦስተኛውና ሌላኛው መሠረታዊው የነገውን (የትዳርሽም ኾነ የሀገር) መሪ፣ የልጆችሽን አባት፣ የቤተሰብሽን ምሰሶ ወንድ የምትለይው ደግሞ “ስሜቱን መቆጣጠር ይችላል ወይ?” ብለሽ ነው። ነገር ግን ስሜቱን መቆጣጠር የሚችለው አባወራ እና ስሜቱን የሚያፍነው ምስኪን ሊመሳሰሉብሽ ይችላሉ እና ጠንቀቅ በይ።

“ስሜታዊነትን እንዴት ትገልጸዋለህ አትዪኝም?”

ንሺ እንግዲህ ልዘርዝርልሽ፦

? መልክሽን አይቶ ደርሶ የሚዝረከረክ፣ ፎቶሽን ይዞ ማምለክ የሚቀረው፣ ድምጽሽን ሰምቶ ልቡ የሚርድበት፣ ዐይንሽን አይቶ(ዐይንሽ አይቶት) እግሩ የሚጋጭበት እርሱ ስሜታዊ ነው።

? በጋራ ለሰማችሁት ኃዘንም ኾነ ደስታ ከማዘኑም ኾነ ከመደሰቱ የተነሳ ለግብረ መልሱ የሚፈጥን ከኾነ እርሱ ስሜታዊ ነው።

? የሚያበሳጭ ነገር ሲገጥመው (አንቺም በአጋጣሚ አበሳጭተሽው ቢኾን) በአንድ አፍታ ደሙ የሚፈላበት፣ ዐይኑ የሚደበላለቅበት እርሱ ስሜታዊ ነው።

? በይበልጥ ደግሞ አኩራፊ ከኾነ፣ ማኩረፉ ሳያንስ አባብሉኝ ባይ ከኾነ፤ ይኽን ሰው ጭንሽ ላይ ታቅፈሽ ደረትሽ ላይ አስተኝተሽ ወይም በጀርባሽ አዝለሽ ታባብይዋለሽን? እርሱም ስሜታዊ ነው።

? ታላላቅ እና ወፋፍራም ስሕተቶችን ወይም ጥፋቶችን አልፎ አልያም ታግሶ በውሃ ቀጠነ የሚበሳጭ ከኾነ፤ ስለሚያበሳጨውም ኾነ ስለሚያስደስተው ነገር መያዣ መጨበጫው ሲጠፋ፤ እርሱም ስሜታዊ ነው።

? ቁጣውንም ኾነ ደስታውን በወቅቶ እና በመጠኑ ራሱንም በመቆጣጠር መግለጽ ሳይችል ቀርቶ አጠራቅሞ፣ አጠራቅሞ አንድ ቀን “ሰይጣኔን አታምጪው!” ብሎ የሚያንባርቅ ከኾነ እርሱ ስሜታዊ ነው።
.
.
.

አንድ ለወደፊቱ የትዳር ጓደኛሽ አድርገሽ የምትመርጪው ወንድ ስሜቱን መቆጣጠር የሚችል መኾን አለበት። ስሜቱን መቆጣጠር ካልቻለ፣ ቤቱን እና በዙሪያው ያለውን መቆጣጠር አይችልም።

በአከባቢው(በዙሪያው) ካሉት ጋር ያለውን ስሜታዊ፣ ስነልቦናዊም ኾነ ማሕበራዊ እሴት፣ ባሕላዊ ወግ፣ መንፈሳዊ ሕይወት ከስሜታዊነት ልቆ በጽኑ መሠረት ላይም ኾኖ መግዛት፣ መግራትና መምራት መቻሉን አስተውይ።

አንድ ወንድ ደግሞ ይኽንን ለማድረግ ራሱን አውቆ ባወቀውና በያዘው ተማምኖ መቆም መቻል አለበት። ይኽን ለማድረግ ይኹንታንና ጭብጨባን (ያንቺንም ቢኾን) ሳይፈልግ ሳይጠብቅም ሊለማመደው፣ ሊኖረው፣ ሳይናገረም(እኔ እንዲህ ነኝ ሳይል) ሥራው ሊያወጣው(ሊገልጠው) ይገባል።

ውቢቷ!

አንቺ የውብ ዳር እህቴ እንዳንች ያለችው የውበት ጥግ ራሱን የሚቆጣጠር የሚገዛም ወንድ ይገባታል። የምትመርጪው ወንድ ዘወትር አንቺን ለማስደሰት የሚሮጥ እንጂ ለራሱ የሚሮጥለት ርዕይ ከሌለው አያሳርፍሽም።

“እንዴት?” ብትይኝ ለራሱ ያለውን ስሜት መግዛትና መንዳት ያልቻለ አንቺም አይደለሽ ስሜቶችሽ የሚዘውሩት ምስኪን ይኾናል። ይኽንንም ወንድ ብታገቢው አንቺን መምከር፣ ማረም መገሰጽም የማይችል ነገር ግን ሁልጊዜ(አብዛኛውን ጊዜ) ካንቺ ጋር የሚስማማ ይኾናል።

“እርሷን ካጣሁ ያበቃልኛል” ከሚለው ድብቅ ውሉ “እርሷን ካስደሰትኳት ታስደስተኛለች” ከሚለው ስውር አጀንዳውም የተነሳ ስሜቶቹን መደበቅ ማፈንም እንጂ መግዛት የማይቻለው ነው። በተጨማሪም ልጆቹን መክሮ፣ ገስጾና ቀጥቶ ማሳደግ የማይችል “ኾደ ቡቡ” ይኾናል። ከስሜተ ስስነቱም የተነሳ “የልጆቼን(የልጆችን) እንባ ማየት አልችልም” ይላል።

ይኽንንም ጎዶሎ ስሜቱን በቁሳዊ ስጦታዎችና ጭብጨባዎች ለመሸፈን ይሞክራል። ከዚኽም የተነሳ በዐለማዊው ትምሕርት የመጠቁ፣ በርካታ ንብረትን ያካባቱ፣ በአለባበስና በአነጋገር ወደር የማይገኝላቸው ነገር ግን መረን የኾኑ ትውልዶችን ያፈራል።

አንድ ወንድ ስሜቱን መቆጣጠር ስለመቻሉ የሚናገረውን፣ እርሱንም ከሚሠራው አነጻጽሪ፤ ድንገትም ለሚከሰቱ ገሃዳዊ ክስተቶች የሚያሳየውንና የሚሰጠውን ግብረ መልስ አስተውዪ።

አንቺ የውብ ዳር!
ስሜቱን (የደስታውን፣ የኃዘኑንም ኾነ ሌሎች) መቆጣጠር የማይችል ወንድ ለጊዜው ወደድኩሽ ከነፍኩልሽ፣ ሳላይሽ አልውልም(አላድርም)፣ ሲልሽ “ወዶኛል፣ ወዶኝ ይኾናል ሊወደኝም ይችላል” አትበይ።

ወይም ደግሞ ደርሶ ከሀሳቦችሽ ሲስማማ፣ ያንቺም ኾነ የሌሎች ሴቶች መብት ተሟጋች ሲኾን ቆም ብለሽ አስተውዪ። ይኽን የሚያደርገውስ እውን ልከኛው ነገር ገብቶት ስለእውነትም ዋጋ ለመክፍል ዝግጁ በመኾኑ ወይስ ባንቺም ኾነ በሌሎች ሴቶች ዘንድ ለመወደድ፤ አስተውዪ!

እርሱም “እውን ስሜቶቹን ይቆጣጠራል ወይ …..?”

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *