ቃሉን የማያከብር(ለሴቶች ብቻ)

ውቢቷ!

አፈ ቅቤነት በሚመረጥበት እና በሚያስወድስበት በዚህ ዘመን ቃሉን አክባሪ ሰው ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱ ለምን ይመስልሻል? አፈ ቅቤ ለመኾን ቃልን መጠበቅ ሳይሻ ከአፍ የሚወጣን ቃል ማጣፈጥ እና በአድማጭ ዘንድ (ጊዜያዊም ቢኾን) መወደድን ማትረፍ ነውና።

ሰው በተለይም ወንዱ አፈ ቅቤነትን ከዚኽም የተነሳ ሴት አውልነትን “ለምን ይመርጣል?” ብንል ቃልን መጠበቅ፦ እንደተናገሩት፣ በተናገሩት ልክ፣ በተናገሩት መጠን፣ ያሉት ቦታ፣ ባሉት ቀን ኾኖና አክሎ መገኘት ነውና፤ አስወደደም አላስወደደ የማይችሉትን አልችልም ማለት ነውና። እርሱም ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና ነው።

ይኹን እንጂ ዋጋ ከፍሎ ቃሉን ጠብቆ (“የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ብሎ) ከዚኽ ከቃል ጠባቂነቱ ተነስቶም ሌሎች ቃላቸውን እንዲጠብቁ ቢናገር ቢጠብቅባቸውም እርሱ “አካባጅ” ይባላል። ከዚኽም የተነሳ ይኽ ሰው በቤተሰብዓዊ ኑሮው፣ በማሕበራዊ ሕይወቱ፣ በሥራ ገበታውም ጭምር ይገፋል።

የመገናኛ ብዙኃኑ፣ ምሑራኑ፣ ኪነ-ጥበቡ፣ ወላጆ፣ የኃይማኖት አባቶች…. ሌሎችም አካላት ጣፈጠም መረረም ተገቢውንና ልከኛውን ቃል መናገርን በሕብረተሰቡ ዘንድ ከማስለመድ ይልቅ፤ “ሰዉ ምን መስማት ይወዳል?” እያሉ ተወዳጅነትን ለማትረፍ የማይፈጽሙትን ማውራት ሰበብ አብዝቶም በመሸሽ ቃላባይነትን ያስተምራሉ።

በዚኽ ዘመን ታዲያ ለመወደድ ቃሉን ሰጥቶ እንዳይችለው ሲያውቅ አስቀድሞ ይቅርታ መጠየቅ ተገብቶት ሳለ፤ “አሳማኝ”፣ “አሳማኝ” ምክንያቶችን በመደርደር “እንቅፋት ገጥሞኝ እንጂ እኔማ ቃሌን ጠባቂ ነኝ” ለማለት ይዳዳዋል።

ውቢቷ! ልብ አድርጊ!

ከምንም በላይ ቃላቸውን ለሚጠብቁ ወንዶች ቦታ ይኑርሽ። ቃል ጠባቂነት ስልሽ የጋብቻ ቃሉን መሓላውን ቢያካትትም እንኳ በዚኽች ጦማሬ ግን እሱን ማለቴ አይደለም። ዕለት ዕለት ስለሚናገረው ነገር እንጂ። የአባወራ መለያ ብዬ ከዚኽ ቀደም ከጻፍኳቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ቃል ጠባቂነት ነው።

ይኼም እንዴት ነው ቢሉ፦

1ኛ. አባወራ የሚናገረውን አስቦ፣ አውጥቶና አውርዶ ይናገራል።
2ኛ. በተናገረው ቃልም ዘንድ ይገኛል(ይጠብቀዋል፣ ይፈጽመዋልም)።
3ኛ. ያለውን ያድርገውም አያድርገውም ኃላፊነቱን እኔነኝ ሲል ይወስዳል።
4ኛ. ሰው ነውና እክል ቢገጥመው ቃሉን ላለመጠበቁ ሰበብ ሳያበዛ ይቅርታ ይጠይቃል።
5ኛ. አስቀድሞ እንደማይጠብቀው(እንደማይቻለው) ሲያውቅ ደግሞ ቃሉን አይሰጥም።

እነዚኽን እንግዲህ ከአንድ ወንድ ጋር ተዋውቀሽ በምታሳልፊያቸው የጓደኝነት ወቅቶች የምትታዘቢያቸው ናቸው።

የተዋወቅሽው ወንድ ከአፉ ከሚወጣው ቃል ይልቅ ከአፉ ለሚወጣው ጠረን የሚጨነቅ ከኾነ ከከንፈሩ ፍሬ ይልቅ ከንፈሩን የሚቀባው ቻፒስቲክ የሚያሳስበው ከኾነ ቆም ብለሽ ልታስቢበት ይገባል። አስተውዪ! የብስለቱ መጠን የአባወራነቱም ብቃት የሚለካበት አንዱ መንገድ ቃሉን መጠበቅ መቻሉ ነው።

ለምሳሌ፦ ቀጠሯችሁ 11፡00 ሰዓት ከኾነ ባለው ሰዓት ካለው ቦታ መገኘት አለበት። ሲኾንማ ቀደም ብሎ ቦታ መርጦ አሰናድቶም ይጠብቃል። አለበለዚያ ግን (አንድ ሁለት ቀን እሺ) ታኪሲ፣ ሥራ፣ አለቃ ሌላም ሌላም ሰበብ አስባብ እየመዘዘ የሰጠውን የቀጠሮ ቃል የማያከብር ከኾነ ምርጫሽን ደግመሽ እንድትመረምሪ እመክርሻለሁ።

ውቢቷ!
ቃል በጣም ክቡር፣ የሚከበር የሚያስከብርም ነው። ሰው በሚናገረው፣ በሚሰጠው ብሎም በሚጠብቀው ቃል ይታወቃል። በተለይም ደግሞ ወንድ ልጅ ይኽ ቃሉን የመጠበቅ ሥነ-ስርዓት ከሌለው ምን ኃብታም፣ ምን ባለስልጣን፣ ምን የተማረ ቢኾን ከንቱ ነው።

ከአፉ ለሚወጣው ቃል የማይታመን፣ እንደቃሉ የማይገኝ ቃላባይ፣ ልወደድም ባይ እንዴት አድርጎ ቤቱን ትዳሩን ልጆቹን ሀገሩን መምራት ይቻለዋል? አንቺስ አንድ ራሱን ችሎ በዚኽ ስርዓት ላልተገኘ ወንድ ከተማ የኾነ ልብሽን፣ ሀገር ተረካቢ (ትውልድ) ልጆችሽን እንዴት ትሰጪዋለሽ?…..

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *