ቃልህን ታከብራለች ወይ?

እጩው አባወራ ለሚስትነት ያሰባትን ሴት ከሚመርጥባቸው መስፈርቶች አንዱ “ቃሌን ትጠብቃለች ወይ?” ነው። የመጀመሪያው እና ቀዳሚው መስፈርትህ “የአባቷ ልጅ ነች?” ከሆነ ከሞላ ጎደል ሁለተኛውንና ሦስተኛውን መስፈርት(ሌሎችም ቢኖሩም) ታልፋለች። ለዚህም ነው ሁለት ሳምንት ወስደን ስለ “የአባቷ ልጅ” ያወራነው። መክፈል ያለብህን ዋጋ ሁሉ ከፍለህ አጽንዖትህን እርሱ ላይ ብታደርግ በብዙ ታተርፋለህ። እርሱ ሲሆን ሌሎቹ(መስፈርቶች) ሁሉ ይፈጸማሉ።

ልጄ፣ ወንድሜ፣ ወዳጄ መልክ፣ውበትና ደምግባትም ሁሉ ከንቱ ናቸው። መልከኛ እና ደመግቡ ነገር ግን ሞጋች እና እሺታ ዳገት ከሆነባት ሴት ይልቅ ቃልህን አክባሪዋ የአንደበቷ ለዛ በእሺታ የተሟሸ ፉንጋ የቤትህ ሰላም፣ የውስጥህ እረፍት፣ የደስታህ ማዕከል ትሆናለች።

ስለዚህ ለእጮኝነት የምታስባትን ሴት ቃልህን ማክበሯን በእያንዳንዱ ቅጽበት ተመልከት። እንዳው ዝም ብለህ በደፈናው እወድሻለሁ፣ ደስትይኛለሽ፣ ካላንቺ መኖር አልችልም፣ እታዘዝሻለሁ፣ እያለክ የአመክንዮ ሚዛንህን አስተው ስሜትህን ብቻ በሚያራግቡልህ “ጥበብ” ተብዬ ሥራዎች ተከልለህ አትጎተት። ሲጀመር አንዲትን ሴት አንተ እወዳታለሁ ካልክ እና እርሷ ግን አንተ የምትላትን ከመቀበል ይልቅ የምትሞግትህ ከሆነ ምኗን ወደድከው? ቆም ብለህ እስቲ አስብ……..

ወንድ ልጅ መከበርን ወይንም የክብሩ መጠበቅን በተለይ ከሚወዳት ሚስቱ ይፈልጋል። በአንጻሩ ደግሞ ሴቷ መወደድን መፈቀርን ከባሏ ትጠብቃለች። ይህ እንግዲህ ተፈጥሮአዊ ሲሆን ረቂቅም በሆነ መለኮታዊ ብዕር በልባችን ሰሌዳ የተጻፈ ነው። ምን ተማርን ብንል እኔ እና አንተ ይህንን ተፈጥሮአዊ እውነት አንቀይረውም። ለዚህም ነው ክብሩን በተመለከተ ወንድ ብዙ መንገድ ሲጓዝ ሴቷ ደግሞ መውደድ እና ፍቅር ፍለጋ የምትኳትነው። አንተም የቃላት ድርድርም ሆነ የሙዚቃ ቃና ተጠቅመህ ይህንን ተፈጥሮአዊ ስዕል ማድመቅ እንጂ ሌላ ዘመን የወለደው ባዕድ ማንነት ራስህ ላይ በመጫን ሕይወትህን የፈተና ጉዞ ልታበዛባት አይገባም ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አንተ ለምንድነው ቃልህን የምታከብር ሴት መምረጥ ያስፈለገህ?
ቃልህን ታከበራለች ማለት ታዛዥ ነች ማለት ነው። ይህ ደግሞ ራሱን ችሎ የምንወያይበት ሲሆን ሲቀጥል ግን አንተ ለቤትህ በምትሠራው ሥራ(ከጥቃቅኗ ጀምሮ እስከ ትልልቅ ሥራዎች) ሚስትህ ዋጋ የምትሰጠው ፣ ክብርህን መጠበቋን የምታሳየው፣ ያንተን የቤት ውስጥ አባወራነት የምትገልጠው ቃልህን ስትጠብቅ ብቻ ነው።

እርሷ ቃልህን ስታከበር (የወንድ ልጅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ነው ብዬሃለሁ አይደል?) ወንዳወንድነትን የሚያላብሱህ በሰውነትህ ውስጥ ያሉት ንጥረነገሮች ከያሉበት ይመነጫሉ በእነርሱም ወንዳወንድነትህ ይፋፋማል በዚህም ቃልህን በማክበር ለተነቃቃው ሴቴነቷ ምላሽ መስጠት የሚችል እና የሚያሳርፍ ወኔ ከአቅም ጋር ፣ ፍላጎት ከድፍረት ጋር ይኖርሃል።

ሴት ልጅ ቃልህን ስታከብር ብቻ ነው ያንተ ግብዣ፣ ሽልማት፣ ምስጋና፣ ጨዋታ፣ ስጦታ፣ የመጨረሻው እና ከሁሉም የማያንሰው ወሲብ(ተራክቦ) ዋጋ የሚኖራቸው። አለበለዚያ ግን ቃልህ ካልተከበረ ቤትህ ውስጥ ብትኖርም ካለህ የማትቆጠር ምክርህ ተረት ተረት፣ ተግሳጽህ ስላቅ፣ ቁጣህም ጩኸት ብቻ ይኾናሉ(ባጭሩ የሰርከስ ውስጥ አንበሳ ትሆናለህ)፤ ከዚህስ ይሰውርህ። ሚስትህ ቃልህን ካላከበረች ልጆችህን አክብሩ ማለት ውጤት የለሽ ድካም ነው።

ልጆችህ ዝምተኛ ሊሆኑ ይችላሉ ቃልህን መጠበቅ ግን ውስጣቸው አይኖርም። ለዚህም ነው የዚህ ዘመን አባቶች አስቀድመው ሚስታቸው ቃላቸውን እንደማታከብር ሲያውቁ ወይም እንደማይከበሩ ሲያውቁ፣ እርሱንም ማስጠበቅ ጦርነት ያመጣል ብለው ሲያስቡ ማልያ(መለያ ልብስ) ቀይረው “የፍቅር ሰው ፣ ተወዳጅ አባት” በሚለው በመጫወት አለመከበራቸውን ሸፈን ያደርጓታል። ለዚህም ምልክት ልጆቻቸውን አይቀጡም አንድም እነርሱ ዘመነኛ ስለሆኑ ልጆችን በፍቅር መያዝ እንጂ መቅጣት ኋላ ቀር ነው ሲሉ፤ አንድም ደግሞ የዘመኑን መክፋት ምክንያት አድርገው ያቀርባሉ። ይህ እንግዲህ ከተፈጥሮ እውነት በብዙ ይርቃል።

አንተ ግን ቃልህን የምታከብር ሴት ካገኘህ ልጆችህ “ይህን አድርጉ አታድርጉ” ብዙም ሳያስፈልጋቸው ባንተ ቃል እና በእናታቸው አርአያ ይሄዳሉ።
አስረጅ አንድ ሰው ቤተሰቡን ይዞ ሲጓዝ መንገዳቸው ላይ ጋሬጣ(እንቅፋት) ቢያገኝ እና እርሱን አንስቶ በእዚህ በእዚህ እለፉ ሲል ቢናገር ሚስቱ ቃሉን አክብራ ፈጠን ብላ ስታልፍ ልጆችም እርሷን ተከትለው የሚልፉ ይሆናሉ። አለበለዚያ ግን ሚስት ድካሙን ንቃ እርሷ ቀርታ፣ ቃሉን ንቃ ከመፈጸም ይልቅ እንደገደል ማሚቶ ለልጆቹ ብታስተጋባ እና የተለመደውን የሚስቶች ትዝብት “ውይ የዛሬ ልጆች መች ሰው የሚላቸውን ይሰማሉ” ብትል ልጆቹ ንቅንቅ አይሉም …..የቤቱ ሰላምም ይደፈርሳል ማለት ነው።

ሌላው የባሏን ቃል የማትጠብቅ ሴት ከባሏ ወንዳወንድነቱን ስታጣ ወሲባዊው እርካታዋም የሕልም እንጀራ ነው። በእልፍኝህ ቃልህ ካልተከበረ በመኝታ ቤትህም ያው ስለሚሆን ድካምህ የትም አያደርሳትም። ቃልህን የማታከብርን ሴት ወደ ወሲባዊ እርካታ ማማ ከማድረስ ተልባ መስፈር የተሻለ ስኬት ይኖረዋል(ይህንንወደፊት ብንኖር በደንብ እናየዋለን)።…ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *