ቃልህን ጠብቅ

ሳተናው!

አንተ የኃሳብህ፣ የእምነትህና የቃልህ(የድርጊትህ) ውጤት ነህ። ድርጊትህና ቃልህ የልብህ(የእምነትህ) ልጆች ናቸው። ቃልህን(ድርጊትህን) አእምሮህ በኃሳብ ይጸንሰዋል፤ ልብህ ደግሞ በእምነት ይወልደዋል።

በአእምሮህ ውስጥ የምታመዛዝነው፣ የምታብሰለስለው ኃሳብ ጠቃሚነቱ የጎላ ቢኾንም ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ(ኃይለኝነቱ) ግን ከልብህ እንሚወለደው ቃል አይኾንም። ለዚህም ነው ለምትናገረው ቃል፣ ለምትገባው ውል፣ ለምትሰጠውም ቃል ኪዳን ታማኝ እንድትኾን አብዝቶ የሚመከረው። 

ቃላት ኃይለኛ ናቸው። በድርጊት ፍጻሜያቸውን ስታጸና ደግሞ ቃልህ ከተግባርህ የተባበረልህ(የተስማማልህ) የቃልህ ሰው ትኾናለህ። ይኽን የምታደርገው ግን ለሰዎች ሳይኾን ለራስህ ነው። አንተ እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር(ግለሰብ) የሚኖርህ አቋም የምትናገረውና የምታደርገው አንድ ዓይነት መኾን አለበት።

አንደበትህ(ቃልህ) የሚያስተላልፈው መልዕክት ሌላ ድርጊትህ ሌላ ከኾነ ሲጀመር ያንተ ጥል ወይም ግጭት ከራስህ ጋር ይኾናል። አንተ ደግሞ በራስህ፣ ለራስህ ከራስህም ጋር ስምምነት ከሌለህ በአንተ ላይ(በአስተሳሰብህ ላይ) ቀውስ መፍጠሩ እሙን ነው። ቀውስ ባለበት በተለይም ደግሞ የኃሳብህ መጸነሻ በኾነው አእምሮህ  የቃልህ መፍለቂያ በኾነው ልብህ ቀውስ ሲፈጠር መላ ሰውነትህ ይታወካል።

ስለዚህም ስለምታስበው ኃሳብ ጠቃሚነት(ጤነኝነት) ብቻ ሳይኾን ከእነርሱ የተነሳ ስለሚወለደው ኃይለኛ ቃልህ ልትጨነቅ ይገባል።

ፍጻሜ
ቃልህን የማትጠብቅ የማትፈጽምም ሰነፍ አልያም ሰበበኛ ከኾንክ ምን የተቀደሰ ኃሳብ ቢኖርህ  ሲጀመር ሰላምህን ጤናህን ታጣለህ፣ ሲቀጥል ደግሞ ሌሎች ባንተ ላይ ያላቸው እምነት ይሸረሸራል ትናቃለህም።

ሳተናው! ቃልህን ጠብቅ!

በዘመናችን ቃልን መጠበቅ በስነስርዓት/ስነምግባር ላይ ሲኾን “አምባገነንነት”፣ የሕይወትህ አቋም ላይ ሲኾን “ግትርነት”፣ ታማኝነት ላይ ሲኾን “ሞኝነት” ተደርጎ ይተረጎማል። ይኽ ደግሞ እኛ ሰዎች ሊኖረን ከሚገባው ሞራላዊ እሴት ምን ያኽል እንደዘቀጥን እየዘቀጥንም እንደኾነ ያስረዳል።

በዚህ ዘመንም አንድ ሰው “መልካም” አሳቢ ለመባል “መልካም” አስቦ እንዳሰበውም ተናግሮና አድርጎ መገኘት ሳይኾን “መልካም” እንደሚያስብ አስቦም እንደነበር ማውራት ብቻ ይበቃዋል። እንዳሰበውም ላለማድረግ ኁልቁ መሳፍርት የሌላቸው ምክንያቶች አሰማምሮና ቀባብቶ ያቀርባል። 

“አርቆ አሳቢ” “ኃሳቡም ምጡቅ” እንዲባል በቃላት አስውቦና ከሽኖ ሲያቀርብ አፍ ያስከፍታል። “ግሩም ኃሳብ” በማቅረቡ ይወደስና ለስንፍናውና ለድብቅ ዓላማው መሸፈኛ ባቀረበው “አሳማኝ ምክንያት” ግን ባለመፈጸሙ ከወቀሳ “ይድናል”። ለ”መልካም” ኃሳቡም ሕልውና አለመሳካት ሌሎች ሰዎችን እኛ ሲሚዎቹን ጨምሮ ተወቃሽ ያደርጋል፣ እናደረጋለንም። “እኛ እንጂ እንቅፋቶቹ እርሱማ ቅን አስቦ ነበር እያልን” ማውራት እንጂ መፈጸም ለማይችለው ሰው ራሳችንን የጦስ ዶሮም እናደርጋለን።

ሳተናው ወዳጄ አንተ ከእነዚህ ከሁለቱ ራቅ አንደኛ የማትጠብቀውንና የማትፈጽመውንም ቃል አትስጥ አትግባም። ሁለተኛ ሌላው ቃሉን ላልጠበቀው ለስንፍናው ማምለጫ የስርቆሽ በር አትኹንለት ራሱ ባመጣው ይውጣው እንጂ።

ኃሳብህን በቃላት ስትገልጽ የቃል ዕዳ እንዳለብህና ስትፈጽመው ብቻ እንዲወራረድና እንዲከፈል(እንዲፈጸም) አስተውል።

ልምምድ
“ይኼን ደግሞ እንዴት ልለማመድ?” ካልከኝ 
1ኛ ከማንም ጋር ቢኾን አስበህ በመናገር፤ 
2ኛ የምትናገረው ቃል ሰውን ደስ እንዲያሰኘው ብቻ ሳይኾን ቃላባይ እንዳያደርግህ በእርሱ በመጽናት፤ 
3ኛ የማትፈጽመው ከኾነ ባለ ዕዳ እንደሚያደርግህ አስተውለህ በድርጊት መፈጸምን ተለማመድ።

አስረጅ፦ ብዙውን ጊዜ ከጓደኞችህ ጋር ስትኾን ገና ለገና “ይረዱኛል”፣ “ምክንያቴን ይቀበላሉ”፣ “ባይቀበሉም የራሳቸው ጉዳይ” እያልክ በቀጠሮህ ሰዓት የማትገኝ፣ እመጣለሁ ብለህ የውሃ ሽታ የምትኾን፣ “እመልሳለሁ” እያልክ ካስሩም የምትበደር፣ አደርገዋለሁም ብለህ የማትጀምር… ብቻ በቃልህ መገኘት የሚሳንህ ለዚህ ስንፍናህም ደግሞ አሳማኝ እንዲኾኑ ምክንያቶችን በዓይነት በዓይነት መከሸንን ልምድ ያደረግክ አትኹን በጭራሽ! በዚህ ጽሑፍም እነእንቶኔን ሳይኾን ራስህን ፈትሽበት!

ከዚህሞ የተነሳ ሰው ቆሎ ቆልቶም ደገሰ ፍሪዳ ጥሎ ሲጠራህ ላትኼድ “እሺ” ብለህ ለጊዜው አታስደስተው። እመጣለሁ ካልከው ወዲያ ኺድ እንጂ ቀርተህ ምክንያት በዓይነት አትሞሽር። አልያ ግን መጀመሪያውኑ ብርቱ ጉዳይ እንዳለብህና መምጣት እንደማይቻልህ አሳውቀው። እርሱም ታዳሚውን አስረግጦ አውቆ ይዘጋጃል፣ ተድላ ደስታውም ይፈጸማል።

ቃልህን አለመጠበቅን ወዳጆቼ ከምትላቸው ጋር በምንቸገረኝነት እየተላለፋችሁ ትቆይና ለሚናገሩት ቃል ጠንቃቆች የሰውንም ቃል አክባሪዎች ጋር ስትገናኝ አንተ እንደተልባ ስፍር በሚንሸራተተውና ለእርሱም ሰበብ በማያጣው ቃልህ ብዛት ኢ-ተኣማኒነትህ ይጨምራል። አንተ ደግሞ “ወዳጆቼ” የምትላቸው አበላሽተውሃልና አኹን አለመታለፍህ ለሰበብህም ተቀባይነት ማጣትህ “ሰዎቹ የማይረዱኝ ያለመረዳት ችግር ስላለባቸው ነው” በማለት ትበጻበጻለህ(ትረበሻለህ)፣ ትታወካለህም።

ታዲያ የሚገርምህ ነገር ሳተናው! 
ቃልህን ባለመጠበቅህ በቅቤው አፍህ የደለልካቸው ሰዎች ከሚርቁህ ይበልጥ ቃል-አባዩ አንተ ሰውን መሸሽ ትጀምራለህ። በዚህም የተነሳ የራስህን ጤና ታጣለህ፣ አእምሮህ የማይረጋጋልህ፣ ልቦናህ የሚረበሽብህ፣ ሕሊናህም እረፍት የሚነሳህ ይኾናል። ትክክለኛ መፍትሔ ካላበጀህለትም ለመረጋጋት፣ ላለመረበሽና የሕሊናህን ክስም “ዝም” ለማሰኘት ስትል ለብዙ ደባልና ጎጂ ዐመሎች ትጋለጣለህ።

ሳተናው!
ቃልን መጠበቅ ጥቅሙ ለራስ ነው። ሲቀጥል ደግሞ ለሚስትህና ለልጆችህ አርኣያ በመኾን የነገን ለቃሉ ታማኝ የኾነ ትውልድን ትቀርጽበታለህ። ይኼንንም ስታገባ “ትልቅ” ቦታ ስትደርስ ሳይኾን ዛሬ፣ አኹን፣ ባለህበት ቦታ እና ኹኔታ በያንዳንዱም ንግግርህ ውስጥ ቃልህን በመጠበቅ እርሱንም በመፈጸም መለማመድ አለብህ።

አበው ሲተርቱ “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ይላሉ። ቃል ምን ያክል ዕዳ፣ ምን ያክልም ብርቱ እንደኾነ አስተውል።

ሳተናው! ቃልህ የማይጨበጥ ጉም አይኹን!
ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *