ቅርፊት ሰበራ

ቀድመን ያለንበትን ነባራዊ ኹኔታ መዳሰሳችን እና በእርግጥም የችግሩ ሰለባ መኾናችንን መቀበል ከተፈጥሮኣዊ ባሕርያችን ውጪ እንድንኖርበት ለተጫነብን ቅርፊት መስበሪያ ወኔን ይሰጠናል።

ልብ አድርግ ወዳጄ! የምመክርህ በጋረደህ ቅርፊት ላይ ተንጠልጥለህ እንድታመልጥ አይደለም እንድትሰብረው እንጂ። ምክንያቱም መንጠላጠል ተመልሶ ለመውደቅ ዕድል አለውና። ሰባብረህ መውጣት ግን ወደፊት፦ የተሰጠህን ጸጋ፣ በወንድነትህ ያለህን ሚና፣ የተፈጠርክበትንም ዐላማ ሲያስረዳ፤ ወደኋላ፦ ደግሞ ያፈረስከውን የውሸት አጥር፣ በድካምና በጉስቁልና የኖርክበትንም አመድና ፍርስራሽ የኾነውን የቀደመውን ዘመንህን ያሳይሃል።

የወንድነትህ ውበቱ ነፃነቱ ነው። መኾን የፈለከውን አንተ ትወስናለህ እንጂ አጥርና ቅጥር ተሠርቶልህ ከዚህ ውጪ እንዳታስብም ተብለህ ጫጩት ኾነህ ነፍስ ዘርተህ ግን ደግሞ ከቅርፊቱ ሳትወጣ ጫጩት ኾነህ እንድትሞት አትፍቀድ።
ያንተን የወደፊት ማንነት ፈጣሪህ በሰጠህ ጸጋ ሥራው አብጀው። ይኼን ጊዜም ነው ከተሠራህበት የፈጣሪ ቃል(manual) ተነስተህ አንተነትህን የሚሰጥህን ሥርዓትና ቅርጽ የምታወጣው።

ይኼ ሥርዓት(discipline) አንተን ይገልጽሃል። በእርሱም ውስጥ ሚስትህ ልጆችህ ሲካተቱ አንተ ደግሞ የትዳርህ መሪ ነህ። ወደ መልካም ዳርቻ እንደምትመራቸው ኹሉ ክፉ ነጣቂ ተኩላ(ጠላት፣አስተሳሰብ) ቢመጣም የምትመክት መስዋዕት መኾን ካለብህም ከሚስትህና ከልጆችህ በፊት የምትሰዋ አንተ ነህ።

በዚህ ያንተ ሥርዓት ውስጥ ከዘመኑ እንቶ ፈንቶ እርቀህ ሚስትህ ከአንተ ከባሏ በወንድነትህ ብቻ ልታገኘው የሚገባትን ፍላጎት ያለድርድር ወይም ጥያቄ(ለምን አገባችህና ነው?) ልታሟላላት እርሷም እንዲሁ ፈቃድህን ልትፈጽም ይገባታል። በዚህም አንድነታችሁን የሚያጸናው፣ ተባርኮና ተቀድሶም የተሰጣችሁ ወሲብም ግሩም ድንቅና ዘወትርም ይኾናል። ይኽንንም ሥርዓትና ቅርጽ መወሰን ያንተና ያንተ ብቻ ነው።

ምሳሌ ከራስ ተሞክሮ፦
👍እኔ ዘወትር አሥራ አንድ ሰዓት ስነቃ ልጆቼ ደግሞ (ዕድሜያቸው 5/12 እና4) አሥራ ሁለት ሰዓት ይነሳሉ። ይኼም ዓመቱን ሙሉ 365ቱንም ቀናት ይኾናል።(Early to bed early to rise makes a man healthy wealthy and wise እንዲሉ)
👍እኔ የሞባይል ጌም አልጫወትም ልጆቼም እንዲጫወቱ አልፈቅድም ሲጀመር ይኽን ጽሑፍ የማዘጋጅበትን tablet እንኳ ከእኔ ፈቃድ ውጪ አይነኩም።
👍እኔ መጽሐፍ ማንበብ እወዳለሁና ከሁለት ዐመታቸው ጀምሬ አነብላቸው ስለነበር(ዐመቱን ሙሉ 365ቱንም ቀናት) ማታ ያለንባብ “ተኙ” ማለት ቅጣታቸው ነው።

እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው በእኔ ቤት እኔ በራሴ ስልጣን እኔንም ኾነ ቤተሰቤን ወደስኬት ያሸጋግራሉ ብዬ የሠራኋቸው ሥርዓቶች ናቸው። ሰው ነኝና አልፎ አልፎ ክፍተት ሊታይብኝ ይችላል።

እናንተስ ቅርፊቱን መስበር ትሻላችሁን?

የመጀመሪያው እርምጃ ይኽን ቅርፊት ከሚጭኑባችሁ አካላትና መሣሪያዎቻቸው መላቀቅ ነው። እነርሱም የመገናኛ ብዙኃንና ማሕበራዊ ድረገጾች ናቸው። ዐለም ላይ የሚኾነውን ነገር አትስሙ ማለቴ አይደለም።

እውነትም ይኹን ውሸት ክፉም ይኹን ደግ ዜናዎችን ስሙ ልክም ይኹን ስህተት አዋጆችን አድምጡ ነገር ግን “እያዝናናን ቁምነገር እናስጨብጣለን” እያሉ ጊዜያችኹን ከሚገድሉት ተለዩ። እነርሱ ተፈጥሮኣዊን እና ማወቅ ያለባችሁን እውነት ሳይኾን እናንተ ብትሰሟቸው ደስ የሚላችኹን፣ ምቾታችሁን የሚጠብቁ ፕሮግራሞች አዘጋጅተው እናንተን ባዶ አድርገው የእነርሱን ኪስ ይሞላሉና ነው።

ወንድነታችሁን ከሚሰልቡ፣ የልባችሁንም ጥንካሬ ከሚንዱ ፉከራን፣ ጀግንነትን ሳይኾን በፍቅር ስም (በአፍቅሬ ነው ሰበብ)የልቅሶ ሙሾ ከሚያስተምሯችሁ ዘፈኖችም ተለዩ። ሁላችንንም ጋዜጠኛ፣ ሁላችንንም photographer ፣ ሁላችንንም activist ፣ ሁላችንንም political commentator ፣ ሁላችንንም መካሪ(እኔ ባልብስ) ካደረጉን ማሕበራዊ ድረገጾች ተቆጠቡ።

ወዳጄ ከቅርፊቱ መውጣት ትፈልጋለህ ባለህበት መርገጥህን አቁምና እንደምንም ብለህ አንድ እርምጃ ወደፊት ስትራመድ ሁለተኛውና ሶስተኛውን የምትቀጥልበት አቅም እንዳለህ ትረዳለህ ። እያንዳንዷ የዕለት ተዕለት ድርጊትህ፣ ልማድህ በቀረጽከው ሥርዓት ውስጥ አንተን ወደ ዐላማህ የምትስብህ መኾን አለባት።

ተፈጥሮህን እወቅ፣ እውነትንም ፈልግ በተለይም መንፈሳዊነትህ እነዚህን ትረዳቸው፣ የፈጣሪህንም ዐላማ ታውቅበት እንጂ የምድራዊውን ንጉስ ዐላማ ማስፈጸሚያ አይደለም። ከዚያም አንተነትህን የሚገልጽ ስነ-ሥርዓት አንተ ራስህ አብጅ። ትዳርህን ልጆችህንም በዚህ ውስጥ ቃኝ።

ወንድ ተደርገህ ተፈጥረሃልና ወንድነትህን ተቀብለህ፣ እርሱንም በማበልጸግ በልዕልና ኑር። በጭራሽ ራስህን ከመኾን ይልቅ ሰውን ደስ ያሰኝልኛል የምትለውን ማንነት አትያዝ።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *