ቅጣት ወይስ ጥቃት

ሳተናው!

አኹን እኔና አንተ የምንኖርበት ዘመን በብዙ መልኩ የስነስርዓትና የስነምግባር ዝቅጠት ይታይበታል። ይኽ የኾነው ደግሞ በሌላ በማንም ሳይኾን እንደእኔና እንዳንተ ባሉ ወንዶች የአባትነት እና የመሪነት ሚናን(የአባወራነቱን) በአግባቡ መወጣት ባለመቻላችን ነው።

ወንድሜ የችግሮችህን ኹሉ መንስዔ ካንተ ውጪ አድርገህ፣ ትላንት የምታደርገውን ተመሳሳይ ድርጊትም ዛሬም እየደገምክ ሌሎች ሲለወጡ እለወጣለሁ ብለህ የምታስብ ከኾነ መቼም አትለወጥም። ይልቁንስ በተፈጠረው ችግር ውስጥ “የእኔ ድርሻ ምን ነበር?” ብለህ ያንተን ጉድለት ብትሞላ እንደሚጠበቅብህም ብትለወጥ በብዙ ታተርፋለህ።

ይኽን ስልህ ግን ራስህን የችግሮችህ ኹሉ ምንጭ እንድታደርግ አይደለም!

ከዚህ በፊት በነበሩ ጽሑፎች፣ ምሳሌዎችና ማብራሪያቸው ለማየት እንደሞከርነው ስልጣን የወንድነት መሠረታዊ መለያ ጠባዩ ነው። 

1ኛ ስልጣን(መሪነት) በራሱ ፍላጎት፣ ዝንባሌ፣ ስሜት ላይ፦ ከሴቷ በተሻለ ራሱን መግራት ፣ ማስተማርና መምራት እንዲችል። 
2ኛ ስልጣን(መሪነት) በትዳሩ፣ በሚስቱ፣በልጆቹ፣ በቤቱ ላይ፦ ማነጽና ማስከተል እንዲችል
3ኛ ስልጣን(መሪነት) በኃይማኖቱ፣ በማሕበረሰቡ፣ በሀገሩ ላይ፦ ወደ አእምሮኣዊና ቁሳዊ ብልጽግና ማድረስ እንዲችል ነው።

አንድ ወንድ ፍላጎቶቹን፣ ስሜቱን በመግራት፣ በማሰልጠንና ራሱን ወደሰቀለውና ወደተፈጠረበትም ርዕይ መምራት ካልቻለ ትዳሩን፣ሚስቱን፣ ልጆቹን መምራት አይችልም።

ይኽንንም በቅጡ ሳይመራ በመንፈሳዊ ተቋማትም ኾነ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ በንዝሕላልነት እና በአምባገነንነት ጽንፍ ይወድቃል አልያም ይዋልላል። ከዚህም የተነሳ ስልጣኑ በሌሎች መሰሪዎች እጅ ሲወድቅ እርሱም የእነርሱ መጠቀሚያ ይኾናል።

ይኽ በተፈጥሮ ወንድነትህ የሚሰጥህ ስልጣን ይበልጥ ተፈላጊነቱ የሀገር፣ የትውልድ፣ የሕብረተሰብ፣ መሠረት በኾነው ትዳርህ ውስጥ ነው። በቤትህ ውስጥ የተሰጠህ ስልጣን በዋናነት ባንተ ሥር ያሉትን (ሚስትህን ጨምሮ) ስነስርዓትና ስነምግባር የምታስተምርበት እና ተጠሪነታቸውን ታዛዥነታቸውን እንዲጠብቁ(ለጊዜው ላንተ ለዘለቃው ደግሞ ለአምላካቸው) የምታሰለጥንበት ነው። እንዲኹም ከእነርሱ የምትጠብቀውን ቅጠኛ ኑሮ ግድ የምትልበትም እንጂ።

ሳተናው!
አንተ ከፈጣሪ ሕግ ተነስተህ ሚስትህና ልጆችህ ሊኖራቸው ስለሚገባ ስርዓትና ምግባር ግድ ማለትህ በተፈጥሮኣዊ  ሰውነታቸው ብሎም በጾታቸው፣ ሲቀጥልም በቤትህ ውስጥ ስላላቸው ሚና የተቃና አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል።

አልፎ ተርፎም ስለጾታቸው ጤናማ ግንዛቤ ሲኖራቸው ከራሳቸው አልፈውም ለቤተሰብ፣ ለወገን እና ለሀገር ብቁ ማድረግ ይቻልሃል።

ይኹን እንጂ አኹን ያለው በሴታቆርቋዥ (Feminism) አስተሳሰብ የተበከለው ዓለም በተደጋጋሚ ይኼንን የአባወራውን ስልጣን “የወንድ ልጅ አላስፈላጊ ሚና” አድርጎታል። ይኽን ስልጣን ሚስትን፣ ልጆችን፣ ቤተሰብን ቅጥ የሚያሲዝ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ በቤተሰቡ ላይ ከአባወራው የሚሰነዘር “ጥቃት” ተደርጎም ይፈረጃል።

በአባወራነቱ ስልጣኑን ተጠቅሞ ሚስቱንና ልጆቹን ስነስርዓት ለማስያዝ፣ ስነምግባርንም ለማስተማር፣ ቤቱንም በቅጡ ለመምራት የሚሞክር ወንድን “አምባገነን” እርምጃዎቹንም “ጥቃት” ማለትም ተለምዷል።

ከዚህም የተነሳ ዛሬ ዛሬ ቤቱን ቅጥ የሚያሲዝ አባወራ፣ ሚስቱን የሚገስጽ ባል፣ ልጆቹንም የሚቀጣ አባት እየጠፋ ነው። ይኽ ደግሞ በፈንታው ቤታችንን(ትዳራችንን) እያፈረሰ፣ ሚስቶቻችንን ከእኛ እያራቀ፣ ልጆቻችንንም መረን እያወጣ፣ ሀገራችንንም የወላድ መካን እያደረጋት ይገኛል።

በሴታቆርቋዡ(Feminism) አስተሳሰብ የተወሰዱት ተጠርንገውም የጠፉት(ወንዶችም ኾነ ሴቶች) በሁለቱ ጾታዎች መካከል ተፈጥሮኣዊ የሚና ልዩነት እንደሌለ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ይኽንንም ልዩነት ይሽራሉ መሐል ሰፋሪም ይኾናሉ(ወንድ አይሏቸው ሴት)።

በዚህ ኺደት በተለይም ቅጣቱ “ጥቃት” የተባለውንና  ቦታ ያጣውን የወንዱን ስልጣን ከሥሩ መንግለው ለመጣል ይጥራሉ። ይኽ ሲኾን ታዲያ የሚወድቀው የወንዱ ስልጣን ብቻ ሳይኾን የቤተሰብ፣ የማሕበረሰብ፣ የትውልድ ብሎም የሀገር መሠረት የኾነው ትዳርም ጭምር ነው።

የአባወራው ስልጣን የቤተሰቡ አባላት ለተፈጠሩበትና ለተጠሩበት ዓላማ መሳካት አስፈላጊ ነው። እርሱም ቅጠኛ ሕይወት ከመመሥረቱና እርሱንም ከማጽናቱ አንጻር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

እዚህ ጋር ማሰተዋል ያለብን ሴቶች እና ሕፃናት የአባወራውን ስልጣን መኖር ቢያውቁም ጥቅሙንና ከስልጣኑ የተነሳ ቅጥ ለማስያዝ የሚተገበረውን ቅጣት ለመረዳት ግን ይቸገራሉ። ይኹን እንጂ ታዛዥነት ስጦታቸው ነውና(ኾኖ መገኘቱን ባይሹትም) ለአንድ ለሠራ ቅጥ(ስርዓት)፣ መምራትም በሚችል ወንድ እቅፍ ውስጥ ስልጡን ናቸው።

አንድ ስልጣን በሰውም ኾነ በኹኔታዎች የሚፈጸምን አእምሮኣዊ፣ ስነልቦናዊ ቀውስ መታደግ ይችላል። ቅጠኛ ስርዓት እንዲኖርና እርሱም እንዲጠበቅ ስልጣን ያለው አካል ወሳኝ ነው። ሕጉ አልያም ስርዓቱ ባይፈጸም ቅጣቱ ቢተገበርና ከዚህም የተነሳ ፍርሃትንም ቢፈጥር ተገቢ ነው። 

ሳተናው!
እንደአባወራ በቤትህ ውስጥ ቤተሰብህን የመምራቱ ከፍተኛ ስልጣን ያንተ ነው ቢኾንም አንተ ቀድሞውኑ በስርዓትና በምግባር በልጽገህ ልትገኝ ይገባሃል። ይኹንና ራስህን ስሜትህን፣ ንዴትህን መቆጣጠር የማትችል ሞገደኛ ከኾንክ ቅጣቶችህ ኹሉ ሕግን ከማስተማር፣ ስርዓትን ከማስጠበቅና አለመታዘዝን ከማቃናት ስተው ጎጂ ይኾናሉ።

ልብ አድርግ! 
ስርዓት ካልጠበቁ፣ የስነምግባር ጉድለትም ካሳዩ እና አንታዘዝምም ካሉ ምን እንደሚከተላቸው አስቀድመህ አሳውቃቸው። እርሱንም ተረጋገግተሀ ፈጽም እንጂ በመሥሪያ ቦታህ የተናደድከውን ሚስትህ ላይ፣ በሚስትህ የተናደድከውን ልጆችህ ላይ ምክንያት አገኘኹ ብለኽ አታንባርቅ አትሰንዝርም። ይኸ ከኾነ ግን በቃልም ኾነ በአካል የምትሰነዝረው “ቅጣት” ወደ ጉዳት አድራሽ ጥቃት መሻገሩ አይቀሬ ነው።

አንተ ለቤተሰብህ መሪ ስትኾኖ ስነስርዓት አስተማሪ ኾነህም ብትቀጣ ጥቃትም እንዳይደርስባቸው ራስህንም ሰውተህ እንድትጠብቃቸው እንጂ እንድትበድላቸው አይኹን።

ቤትን ያለ ስርዓት መምራት እንደማይቻል የተዘረጋውንም ስርዓት የሚያስከብር ስልጣንና ባለስልጣን ማስፈለጉ ግድ ነው ። አንተ ደግሞ ይኽን የመፈጸም ግዴታ ተሰጥቶኃል። የተሰጠህን ኃላፊነት ብትንቅና ብትዘነጋ ሳትጠቀምበትም ብትቀር ግን ሚስትህ የምትንቅህ፣ልጆችህም እርሷን ተከትለው የማያከብሩህ ቤትህም ኾነ ትውልድ ወደ ቀውስ የሚያመራ ይኾናል።

ይኽ የቤትህ ቀውስ ደግሞ ከሌሎችም ጋር ተደምሮ ማሕበራውዊ፣ ሕብረተሰባዊ፣ ሀገራዊ ወደመኾን ያድጋል።

አባወራው በሌለበት ትዳር አይመሠረትም(ከምስኪን፣ ከሴታውሉና ከዱርዬው ስለይ አባወራ አልኩ)። አባወራው የማይመራው ትዳር አልያም እርሱ የሌለበት የሚወለዱ ልጆች ደግሞ መረን መኾናቸው ግልጽ ነው። ከዚህም የተነሳ ማሕበረሰብ፣ ሕብረተሰብ፣ ሀገር የሚባሉ ቀጣይነት ያላቸውና  ዘመናትን የሚሻገሩ ሰብዓዊ እሴቶች አይኖሩንም።

አባወራው በሌለበት ልጆች የጾታ ልዩነቶቻቸው እንኳ ግልጽ አይኾንላቸውም። 

ሳምንት ብንኖርና ጌታም ቢፈቅድ “እማወራነትንና መዘዙን” እናያለን …. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *