በልዕልና ኃላፊነትህ ስትገኝ ሚስትህ በትኅትናዋ ታርፋለች

ሳተናው!
በትዳርህ፣ በቤትህ ውስጥ ለሚፈጠሩት፣ ለሚኾኑት አንኳር እውነቶች ኹሉ ኃላፊነት ውሰድ። ለልጆችህ ደስታ ለሚስትህ እርካታ ለፍቅራችሁም መስመር ኃላፊነቱን መውሰድ ተለማመድ።

ይኼን ለማድረግ ግን መጀመሪያ አንተ የራስህን ሕይወት በሙሉ ኃላፊነት መምራት ተለማመድ። አንተ ያልኖርከውንና የማትኖረውን ስርዓት ሌሎች እንዲተገብሩት ማድረግ ልትሸከመው ያልፈቀድከውን ቀንበር መጫን ነውና።

አንተ ስለራስህ ሕይወት ከሰበበኛነትና ከከሳሽነት ወጥተህ ራስህ ሙሉ ኃላፊነቱን ስትወስድ ብቻ ብቁ የቤተሰብ ኃላፊ መኾን ትችላለህ።

ሲቀጥል ኃላፊነት ስትወስድ ተጠያቂነትም አለና በሥርህ ላሉት ሁሉ ይከተሉት ይጠብቁትም ዘንድ ስርዓት ልትሠራላቸው ይገባል። ልቅነትና ገደብ የለሽነት ሚስትህንም ኾነ ልጆችህን ምግባረ ብልሹ ቢያደረጋቸው እንጂ የፍቅር መግለጫ አይኾንም። ስለዚህ ለምግባራቸው አጥር ቅጥር ሠርተህ ወደ ትልቅነት ከፍታ ልታመጣቸው ይገባል።

ሳተናው ወንድሜ !
በተለይ በስነስርዓት ሕይወትህን መምራትና በሕይወትህ ውስጥ ላሉ ጥንካሬዎችህም ኾነ ድካሞችህ ኃላፊነትን መውሰድ ሳታገባ በፊት ተለማመድ። አልያማ እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛነሽ ይኾናል። ድሮም ሰበበኛነትና ከሳሽነት የሕይወትህ አካል ከነበሩ ትዳርህን በኃላፊነት ላለማስተዳደር የፍቅር ሕይወትህን በዋነኛነት ላለመምራት ምክንያት ማብዛትህ የማይቀር ነው።

ወንድሜ ትዳርህ ሙሉ ለሙሉ ያንተ እና ያንተ ኃላፊት ነው። ኃላፊነትህ ተግባራዊ ይኾን ዘንድ ግን በቤትህ ቁልፍ ሚና የምትጫወተው ሚስትህ እርሷም የአባቷ ልጅ የኾነችው ናት። ቁንጅና፣ ደምግባት፣ የትምሕርት ደረጃ፣ የገቢ መጠን ወንድሜ ምንም ቦታ የላቸውም። ይልቅስ እጮኛህ የአባቷ ልጅ መኾኗን ብቻ እርግጠኛ ኹን።

እርሷን ካገኘህ …. ማንበቡን ቀጥል
በአደባባይ ውሎህ
በትምሕርትም ኾነ በሥራህ ከኹለት በአንዱ ወይም በሁለቱም ብቻ እንደዝንባሌህ ራስህን ለውጠህ(አሻሽለህ) ቤትህን(ትዳርህን) ለመሥራት ተፋጠን።ብትችል ከአንድ የበለጠ ሙያ ባለቤት ኹን።

በእውቀት(በሙያ)፣ በስነ በምግባር እና በአካል ብቃት ራስህን በማሻሻል ግዴታህን ተወጣ። አንተ ኹለገብ ኾነህ ስትልቅ(ስታድግ) ትዳርህም ያድጋልና። ልብ አድርግ ግን! ጥረትህ ጤናማ፣ ማደግህም ሌሎችን ወደ ታች የሚጥል ሳይኾን የሚያነሳቸው ይኹን እንጂ።

ሳተናው ወንድሜ!
በእልፍኝህም..በውጭ እንዳለው እንደሚኾነውም ኹሉ በቤትህም እንዲኹ ይኾን ዘንድ ስርዓት ማበጀት ለኾነውም ነገርም ኃላፊነቱን መውሰድ ይልመድብህ። ልብ አድርግ የኔ ጀግና! አንተ ከደረስክበት የስነስርዓት፣ የስነምግባርና የሞራል ብቃት አንፃር በቤትህ ለሚስትህና ለልጆችህ የሚኖሩበትን፣ የሚመሩበትን እና የሚከተሉትን መቅረጽ፣ ማሳወቅ ተፈጻሚነቱንም ማረጋገጥ ያን ኃላፊነት ነው።

በጭራሽ “ሚስቴ ከእኔ ትሻላለች” እያልክ ቤቱን ማስተዳደር ቅጥ ማስያዙንም ለእርሷ አትተው። አስተውል! የኃላፊነት ስልጣን የሚሠጠው ሰው ሥራውን በኃላፊነት በአመክንዮ እንጂ በስሜታዊነት የማይሠራ ከተጠያቂነትም የማይሸሽ ነው።

ያንተ ተፈጥሮ በአመክንዮ የሚወስን የእርሷ ደግሞ ስሜቶቿን የሚያገናዝብ ነው። ይኽ ታዲያ በደቂቃዎች፣ በሰዓታቶች፣ በቀናት ከሚለዋወጠው ስሜቷ ጋር ውሳኔዋም መለዋወጡ ነው። ይኽን ከተረዳህ አንተ ኃላፊነትህን የመወጣት፣ የመምራትና የማስተዳደር አቅሙ ቢያጥርህም ተፈጥርዓዊው መሠረት አለህና እርሱ ላይ ትገነባዋለህ(ከሌሎች በመማር) እንጂ የቤትህን መሪ ለእርሷ አትሰጥም።

ልብ አድርግ! አስተውልም!
ቤትህን በኃላፊነት የሚያስተዳድረው ከኹለት አንዳችሁ አይደላችሁም። የትምሕርት ደረጃ፣ የገቢ መጠን፣ የተክለ ሰውነት አቋም፣ ውበት፣የቤተሰብ ኃብት ሌላም በሌላም የበለጠው ታይቶ ሳይኾን ቤትህን ማስተዳደር ያንተና ያንተ ብቻ ነው።

ሳተናው
በመጨረሻም ከላይ ከጠቀስናቸው ከሁለቱ (ከአደባባይና ከቤት) ኃላፊነት ቢበልጥ እንጂ የማያንሰው የመኝታ ቤት(የወሲብ ሕይወታችሁ) ኃላፊነት ነው።

ሚስትህ አብዛኛውን ጊዜ (ለሁልጊዜ የተጠጋ “አብኛውን ጊዜ” ነው) ከተፈጥሮ፣ ከባሕልና ከኃይማኖት የተነሳ በወሲብ ጉዳይ ላይ ጭምት ናት። እመነኝ ግልጽ የምትባለው ሴት ራሷ ጭምት ናት። ግልጽ ነች ብለህ ግን አንደበቷን ብትሰማና እርሱንም ብታምን የምታጎድለው ብዙ ነገር አለ።

እርሷ ስሜቷን ሳትነግርህ አውቀህ፣ መፍትሔም ፈልገህ፣ አፈጻጸሙን ተረድተህ ፍላጎቷን ጥግ እንድታደርስላት ትሻለች።
ከዚህ በላይ የሚበትጥ ኃላፊነት አለብህን?…. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *