በማን መቃን ሥር ትኖራላችሁ?

ሳተናው!
አንተ ባንተ መሠረትነት ሕንጻ ትዳር ሲታነጽ ሚስትህን ጨምሮ የቤትህን ሰዎች(ቤተሰቦች) ይወጡ ይገቡበት ዘንድ ስርዓት በርን ለክተህና አጽንተህ በመቃንም ወጥረህ ትሠራላቸዋለህ።

ከዚያም ማንም አንተን የሚያከብር፣ የትዳርህንም መሪነት የሚጠብቅ፣ ቤትህን ትዳርህን ብሎ የሚመጣ ሁሉ ካንተ ጋር ያለውን ሕብረትና አንድነቱን ማቆየት ከፈለገ መውጣት መግባቱን በሌላ በየትኛውም ክፍተት ሳይኾን በዚህ በወጠርከው መቃን ስር ያደርጋል(ሌባ ከኾነ ግን..)።

አንተ ትዳርን አስበህ የመረጥካትን ሴት ለመውሰድ ወላጆቿን(አሳዳጊዎቿን) ትጠይቃለህ። ልብ አድርግ! ከሰው ሰው ለይተህ፣ ለሰማይ ለምድር የከበዱ ሽማግሌዎችን መርጠህ ሽምግልና የምትልከው ይኽቺኑ የመረጥካትን ሴት እንደዲሰጡህ ነው።

እርሷን ሲሰጡህ ፈቃዷን ጠይቀው፣ አንተ እንዴት ልታኖራት እንዳለህ መርምረው፣ የአስተዳደግህን ነገር የማን ልጅ እንደኾንክና እንዴትስ እንዳደግህ ተማክረው ነው። ሲሰጡህም እጅ ነስተህ፣ ጉልበት ስመህ፣ አደራቸውን ተቀብለህ፣ ተመርቀህም ትወስዳታለህ። በዚህን ጊዜም እገሊትን አገባ፣ አገባሃት፣ ወሰዳት ይባላል።

ሳተናው!
እንግዲህ እነዚህን ቃላትን፣ ቋንቋን ስትመረምር በውስጡ ያለን ባሕል፣ ቀለም፣ ትረዳበታለህ። ከእኩልነት የተነሳ ለእርሱ ለሙሽራው የተነገረውን ወስዶ ለእርሷ ለሙሽሪት አልያም የእርሷን ለእርሱ ማድረግ ትርጉም ሲያፋልስ በእርሱም ውስጥ ሊተላለፍ የተገባውን ተፈጥሮኣዊ እውነት ያዛባል።

አንተ ስጡኝ ብለህ ደጅ ብትጠና እንጂ እርሷ እንደማትጠይቅ እንዲሁም አንተ ስጡኝ እንዳልክ ስትሰጥ ልትወስዳት እንጂ እርሷ ስጡኝ ብላ እንዳትወስድህ ሁሉ አገባት፣ ወሰዳት ቢባል እንጂ ወሰደቺው አይባልም።

ከእነዚህ አረፍተ ነገሮች የምትረዳው ባንተ መሠረትነት ለምትገነባው ሕንጻ ትዳር ባቀረብክላት በፍጹም ፍቅርና አክብሮት የታጀበ ጥሪ ወዳንተም ቤት(ሕይወት) በቀየስክላት መቃን ሥር ትገባለች እንጂ አንተም ኾንክ ያንተ ወላጆች ተለምነው፣ እሺ ተብሎም ስትሰጥ ለያዥ ለገናዥ አስቸግረህ፣ ወሰደችውም ተብለህ አትኼድም።

ስለዚህም አንተ አስቀድመህ ወዳዘጋጀህላት ሕይወት ትመጣለች እንጂ አንተ አትሄድም። ይኼ አስቀድመህ አንተ የምታዘጋጅላት፣ የአብሮነታችሁን ዙሪያ ገባውን የሚቃኝ፣ የሚወስን የትዳራችሁ መቃን እለዋለሁ። አንተ ታዲያ እርሷ ባስቀመጠችልህ መቃን ውስጥ ነህ ወይስ እርሷ ባንተ?

ሴት ልጅ ምን ዓለማዊም ኾነ መንፈሳዊ ትምሕርት ብትማር በሥነ-ልቦናም ይኹን በአካል ሄዳ፣ እርፍ፣ ደግፍ፣ ክትት፣ ስብስብ፣ ድብቅ የምትልበትን ወንድ ትፈልጋለች(በግልጽ አትነግርህም እንጂ)። ይኽን ማድረግ ካልቻልክ ግን (ምስኪን አልያም አልጫ ከመኾንህ የተነሳ) ደኅንነት አይሰማትምና ምንም እንኳ ባይረጋላት የሕይወት መቃን አበጅታ በዚያ እንድታልፍ ግድ ትልሃለች።

ይኼም ወደ ከፋውና ከዚህ ቀደም ወዳየነው ያደርስሃል፦ ሕግና ስርዓትን የምትሠራልህ ሳትፈጽማቸውም ስትቀር ተግባራዊ የምታደርግብህ(የማታከብርህም) ትኾናለች። ይኹን እንጂ ያ የውስጧን ጥያቄ የሚመልስ፣ የሚያሳርፋት ወንድ ሲገኝ አታመንዝር የተባለውን ሕግ ለመጣስ እንኳ “በቂ ምክንያት” ይኖራታል፤ “ትክክልም ነኝ” ትልሃለች።

ትዳር እንዴት ነው ሚስትህስ?
? “እኔስ በዚህ በጣም እድለኛ ነኝ እንዴት የምትረዳኝ ሚስት አለችኝ መሰለህ፦ ከጓደኞቼ ጋር ኳስ በማየቴ፣ አንድ ሁለት ብዬ በመግባቴ፣ ፊት አትነሳኝም
? “የእኔዋስ ብትል ‘የት ገባህ፣ የት ወጣህ፣ ከእገሊት ጋር አየሁህ’ አትለኝም”
? የእኔዋ ግን ከእናንተ ትበልጣለች ቤታችንን ቀጥ አድርጋ የምትመራው እርሷ ነች፣
? እኔ በጣም ስለማደንቃት ልጆቻችንን እንኳ ‘እናታችሁን ስሟት ከእኔም ይልቅ እርሷን አክብሯት’ እላቸዋለሁ፤
? ጎበዝና ጠንካራ ሴት ስለኾነች የቤቱ ኃላፊነት ባብዛኛው የእርሷ ነው፤ ከራሴ በላይም አምናታለሁ፤ የምትደብቀኝም የለም
? አንድም ነገር(የመኝታውን ጨምሮ) ፈቃዷን ሳልጠይቅ አልፈጽምም….

እነዚህና የመሳሰሉት ምስኪን ስንፍናውን አልጫ ፍርሃቱን የሚደብቅባቸው የ”አድናቆት” ቃላት ናቸው። ትዳርህን፣ ሚስትህን ባንተ መቃን አኑር።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *