በራስ መተማመንና አባወራነት

ሳተናው!

ማግኔት በተፈጥሮኣዊ ባሕርይው  ብረትን እንዲስብ በራስ መተማመንህም ሴቶችን(ሚስትህንም ቢኾን) ወዳንተ የሚስብ አመክንዮኣዊ፣ አልያም ሚዛናዊ ሳይኾን ደመነፍሳዊ(ተፈጥሮኣዊ) ስሕበት ነው።

በሌላም አገላለጽ፦ በራስ መተማመን ሴት ልጅ ከወንድ ከምትሻቸው እርሷንም ከግንዛቤዋ ውጪ ወደ እርሱ ከሚስቧት የወንዱ ጠባዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።

በራስ መተማመንህ አንተን ከአላዋቂነት፣ ከፍርሃት መንገድ አውጥቶ በራስህ ማንነት ያለማንም እና ያለምንም አጨብጫቢ(ቲፎዞ) እንድትጓዝ ያደርግሃል። በራስ መተማመንህ ከተፈጥኣዊው እውነት ገንዘብ ካደረግከው እውቀትና እርሱን በመኖርም ካካበትከው ልምድ ይመነጫል።

ሴቶች ራሱን ቤቱን መምራት ለሚችል ለሚያደንቁትም ወንድ ይማረካሉ። ይኽ ወንድ ታዲያ በአደባባይ ሥራው፣ በቤት አመራሩ እና በመኝታ ቤት ሚናው ተልዕኮውን የሚወጣ ግዳጁንም የሚፈጽም ነው። እርሱም ደግሞ በእነዚኽ በተጠቀሱት ቦታዎች ተልዕኮውን እንዲወጣና ግዳጁንም እንዲፈጽም አስፈላጊውን የእውቀትና የአቅም ዝግጅት ያደርጋል።

ይኼ ወንድ እኔ “አባወራ” የምለው ነው። ይኽን ወንድ ለመኾን “ምን ያስፈልጋል?” ብትሉኝና እኔም አስፈላጊ ጠባዮቹን ጨምቄ ወደ አንድ ባመጣቸው መልሱ “በራስ መተማመን” ይኾናል። በራስ መተማመን የወንድነትህ መለያ(ይጥበቅ) ለሌሎቹም ሚናዎችህ(አባትነት፣ ባልነትና ራስነት) ነቁ(ምንጩ) ነው።

ሳተናው!
በራስመተማመንህ ከየት እንደሚመነጭ፣ በምንስ ላይ እንደሚደገፍና የሚያስከትለውንም ውጤት አጢን። ዐለም እንደምትነግርህ በፍጹም የራስ መተማመንህን ከውጪ ባሉ ባዕድ ነገሮች ለምሳሌ ልብስ፣ ዝና፣ ደምግባት፣ ኃብት፣ ….. እና በመሳሰሉት ለመገንባት አትሞክር።

ትክክለኛ እና ተፈጥሮኣዊ እውቀት (ስለ ራስህም ኾነ ስለ ሴቶች ተፈጥሮ) ሲኖርህ ለመቀበል አትሰጥም፣ ለመመስገን አትኖርም፣ ለመወደድ አትወድም፣ ለ(በ)ጭብጨባ አትቆምም፣ …. ይልቁንስ ያመንክበትን እና የተገባውን ታደርጋለህ እንጂ።

ምስኪን ተፈጥሮኣዊውን እውቀትን ስለ ምሬቱና ጥጣሬው ሲል አይቀበለውም፣ ይንቀዋል፣ ይክደዋልም፤ ኋላ ላይ ግን እጅግ ብዙ ዋጋ ያስከፍለዋል። ይልቁንም እርሱ ዓለም በባርነት ቀንበር ሥር ይኖርላት ዘንድ የነገረችውን ጣፋጭና ለስላሳ ውሸት ይቀበላል። ከዚኽም የተነሳ ራሱን፣ ትዳሩን፣ ትውልዱንና ሀገሩን ይጎዳል።

አባወራን ከምስኪን የሚለየው በራስመተማመኑ ነው። እርሱ በተፈጥሮኣዊው እና እውነተኛው ሐቅ ላይ እውቀቱን ይመሠርታል። ከዚኽም የተነሳ በሰዎች መካከል በተለይም ደግሞ በሴቶች መካከል በሙሉ ልብ ይመላለሳል።

ይኹን እንጂ ዛሬ ዐለም ሰውን ከፈጣሪ እና ከፍጥረቱ ለመለየት በምታደርገው ያላሳለሰ ጥረት ለልከኛውና ለተገቢው የራስ መተማመን መጥፎ ስም ትሰጣለች። በእርሱ ፈንታም በ”ስልጣኔ”፣ በ”መንፈሳዊነት” እና በ”ፍቅር” ስም ወኔቢስነትን፣ ስንፍናንና ፍርሃትን ለትውልዱ ታስተምራለች።

ከዚኽም የተነሳ ወኔው የተሰለበው፣ በፍርሃትና በስንፍና የተተበተበው ለእነዚኽም ደግሞ የዳቦ ስም ሰጥቶ ከተፈጥሮኣዊው አቅሙ በታች የሚኖር ወንድ ምስኪን ይገኛል። ይኽም ምስኪን በራስመተማመኑ የወረደ ነውና በሴቶች ዐይን ደካማ ለትዳር የማይመረጥ ቢመረጥም የማያዘልቅ ይኾናል(ለሴቶች ግን “ምርጥ” ጓደኛቸው ይኾናል)።

በመጨረሻም ሴቶች ብዙውን ጊዜ ይኼን በራስመተማመን ሲሹት በተለምዶ “ጥሩ” ነው፣ “ምስኪን” ነው ብለው ከሚያስቡት ወንድ ዘንድ ሳይኾን በጠባዩ ያፈነገጠ እና “ዱርዬ” ሊባል ከሚችል ወንድ ዘንድ ያገኙታል።

እርሱ ደግሞ ከማሕበራዊ እሴት፣ ከመንፈሳዊ ስርዓት፣ ከዓለማዊው ሕግ ያፈነግጣልና ትዳርን መሥርቶ፣ ቤተሰብ ገንብቶ፣ ትውልድን አንጾ መኖር አይቻለውም። ይኹን እንጂ የሴቶቹን ልብ ከሚንከባከባቸውና ከሚሞትላቸውም ምስኪን በበለጠ የመርታት አቅሙ ከፍተኛ ነው።

ይኼን ጊዜ ነው እንግዲህ የእኛ በእውቀት እና በጥበብ የሚመላለሰው በራስመተማመንም የተሞላው አባወራ የሚመጣው።

ሳተናው!
አንተ ከፈለግክ እና ከወሰንክ በዚኽ ዘመን በቁጥር በጣም ጥቂት የኾኑትን አባወራዎች መቀላቀል ትችላለህ።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *