በርዕይ(በዓላማ) ስለመኖር

ሳተናው!

ወንድም-ዓለም የመውጣት የመግባትህ ነገር ለትልቁ ርዕይህ መሳካት አንዳች ፋይዳ ሊኖረው ይገባል። አንተ ወደዚህች ምድር ስትመጣ ምን ልትከውን እንዳለህ መርምር። በእርግጥ የኾነ ቦታ ላይ ወይም በሰማይ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ባታገኘውም ከበዛ ትጋትህ የተነሳ ከምትሞክራቸው መስኮች በአንዱ ታገኘዋለህ።

በጭራሽ ግን ያለ ርዕይ አትኑር። በመጽሐፍ ርዕይ አልባ ትውልድ መረን እንዲኾን መጻፉን አስተውል(መጽ ምሳሌ ፳፱፥፲፰)።

ሳተናው!

ሀገርህን እያት አታሳዝንህምን? አንተ ዝም፣ ችላ በማለትህ ብቻ እየኾነባት ያለውስ አያስቆጭህምን? እግዚኣብሔር አንተንስ በዚህ ወቅት፣ በዚህች አገር ላይ ለምን እንደፈጠረህ አትጠይቀውምን? የአባቶቻችን የድካማቸውስ ፍሬ እንዲህ በወንበዴዎች ከታሪክ ማሕደር ሲሰረዝና ሲደለዝ መቀለጃም ሲኾን ሕሊናህ አይወቅስህምን?

ወይንስ አንተም እንደ ብዙኃኑ “የኢትዮጲያ ትንሳኤ ቅርብ ነው ይታየኛል” ባይ ሕልመኛ ነህ። ልብአድርግ! የኢትዮጲያ ትንሳኤ ሕልም(ውሸት) ነው እያልኩህ አይደለም። ነገር ግን ይህን ርዕይ እውን ለማድረግ አንተ ምን ያክል ድርሻህን እየተወጣህ ነው? እንጂ ጥያቄዬ።

ሳተናው!

ሀገራችን በተረት ወይንም በትንቢት አልቆመችም። ይልቁንስ ደምና አጥንት የተከፈለበት ርዕይ ውጤት ነች። ከዘመናቸው ብዙ ርቀት ወደፊት ዓይተው፣ ያዩትንም እውን ለማድረግ ተግተው በሠሩ፣ የሠሩትንም ባስጠበቁልን አባቶቻችን የተገኘች እንጂማ እኔ እና አንተ ሶፋ ላይ ተኝተን የቲቪ ሪሞትም ጨብጠን በአረብ ቻናል ውስጥ እየዋኘን “ብር የለኝም እንጂ ሕልምስ ነበረኝ” እንደምንለው በስንፍና ወሬ እዚህ አልደረሰችም።

ርዕይ ያለ ጸጋ(ርዕዩን እውን የምናደርግበት) አይሰጠንም። ይኹንና ብዙዎች ይኼንኑ ስጦታቸውን ለተፈጠሩለት ርዕይ ከመጠቀም ይልቅ በእንቶፈንቶ ጉዳይ በጉንጭ አልፋም ንትርክ ያባክኑታል። ለርዕያቸው ያላቸውን ዝንባሌ ለይተው ስለእርሱም ያላቸውን ዕውቀት አጥርተው ወደ እርሱም በመዘርጋት 30፣ 60፣ 100ም ያማረ ፍሬ አፍርተው ማለፍ ሲችሉ የአንዱን አጀንዳ በማንሳት የሌላውን በመጣል ጊዜያቸውን ያጠፋሉ።

ሳተናው!

የርዕይህ ዋነኛው መነሻ ፈጣሪህ ሲኾን እርሱንም ግን ለማወቅ ጠቋይ ቤት መኼድ፣ “የሚታያቸው” እንቶኔ ጋር መኼድ አይጠበቅብህም ከብዙ ትጋትህ መካከል፣ ከፈጣሪህ ጋርም በሚኖርህ ውይይት ታገኘዋለህና። እንጂማ ርዕይህንም ኾነ የውሎህን አጀንዳ ከፌስቡክ የምትቃርም አልያም ይገልጥልህ ዘንድ ካንዱ “ባለራይ ነኝ” ባይ ጋር እግርህን የምታነሳ ከኾነ የጨላጣ (professional) ጠንቋዮች መጫወቻ ከዚህም የተነሳ መያዣ መጨበጫ ለሌለው፣ በየእለቱም ማብቂያ በድብርት እና ተስፋ መቁረጥ የሚጠናቀቅ ሕይወትን ታተርፋለህ።

ለሰሞኑ የርዕይ ጭብጥ መጠቅለያ፦

፩ኛ ርዕይ ይኑርህ፦
አንተን፣ ቤትህን፣ ትውልድንና ሀገርን የሚጠቅም። ለቲፎዞነት፣ ለጭብጨባ፣ አስተያየት ለመስጠት፣ በሁሉ ነገር “አዋቂ” ይመስል ለመተንተን እና ለሌላው ድምቀት እንድትኾን አልመጣህም፤ እንዲሁም ስላልኾነ በእነዚህ አታርፍም(ልብህ እረፍት አታገኝም)።

“ርዕይ የለኝም” ካልክስ ባታውቀው ባትፈልገውም እንጂ እርሱማ አለህ። እምቢ ካልክ ግን ሞተው ከተቀበሩት በምን ትለያለህ? ለካ ይኼን ጽሑፍ ታነባለህ(እነሱ አይችሉማ) ይኹን እንጂ በቁም ሞተሃል። ተነስ አስብ፣ ሥራ ርዕይህን ከስንፍናህ፣ ከ”አዋቂ ነን” ባዮች ዘንድ ሳይኾን ከትጋትህ ዘንድ ታገኘዋለህ።

ርዕይ ከሌለ ሞተሃል(መርነሃል፦ መረን ወጥተሃል)!

፪ኛ ርዕይህን ስትተው ራስህን ታጠፋለህ፦
ርዕይህ የኑሮህን ትርጉም የምታገኝበት፣ ሕይወትህን የምትቀጥልበት፣ በፈተናዎችህ ውስጥ አሻግረህ ተስፋን የምታይበት ገንዘብህ፣ ጸጋህ(ስጦታህ) ነው። እርሱን በምንም አትደራደረውም፣ አትለውጠውም፣ አትተወውምም። !

ርዕይህን ተሰፋ ቆርጠህ የጣልከው፣ የቀየርከው፣ የተውከው እለት ያን ቀን አንተ ከሞቱት በላይ፣ ከሚኖሩት በታች በቁምህ የሞትክ፣ በድንህንም ይዘህ የምትዞር ትኾናለህ።

ርዕይን መጣል ራስን ማጥፋት ነው!

፫ኛ “ርዕይ አለኝ!” ፉከራ ብቻ፦
“ርዕይ ይኑርህ፣ ኑሮህን በምክንያት ለዓላማ ኑረው” ስልህ ደግሞ በዓይነ ሕሊናህ ስታየው፣ ለሰውም ስታወራው የሚያፈዝ አስደናቂ ርዕይ ይዘህ ነገር ግን አንዲትም እርምጃ ካልተራመድክ በፉከራ ብቻ ትቀራለህ።

“ምርጥ” ዓላማ ሰቅለህ ግን ምንም ሳትንቀሳቀስ እርሱን ብቻ እያደነቁና ባልጨበጡት ነገር እየተኩራሩ መኖሩ ባዶ ጉራ ብቻ ይኾናል። ይኼም የቀን ቅዠት ይኾናል።

ፉከራ ብቻ ርዕይ የቀን ሕልም ነው!
……..

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *