በቤትህ አንተ ትቀድማለህ

ሳተናው!

ቤትህ ስላለህ ክብር
======================================================
በቤትህ ያለህ የመሪነት ሚና በግልጽ የሚታይ፣ የታወቀና የተረዳ መኾን አለበት። አባወራነትህ ምናባዊ፣ አፍኣዊ አልያም በውስጠ-ታዋቂ መኾን የለበትም።

አኹን ባለንበት ዘመን እንኳ የቤት መሪ “አባወራው ነው” ቢባልም ቅሉ ብዙዎች ቤት ስትገባ የምታየው ግን ከዚህ ፍጹም የራቀ ነው(የራስህን ቤት ታዘበው)።

አንተ በቤትህ ይኽ ስልጣንህ ተገፎ ከመሪነት ይልቅ ተከታይነት፣ ከአዛዥነት ይልቅ ታዛዥነት ቢታይብህ ዋነኛው ጥፋተኛ አንተው ብትኾን እንጂ ሌላ ማንም አይኾንም።

አንተ ያላከበርከውን ስልጣን፣ አንተ ያልተቀበልከውን ሚና፣ አንተ ያቀለልከውንም ክብር ማንም ይጠብቅልኛል ይሰጠኛልም ብለህ ተስፋ ማድረግ ሞኝነት ነው።

በቤትህ ያለህ ስልጣን ከእርሱም የመነጨውን ክብርህን ፈጣሪህ የሰጠህ አንተ ጠብቀህ የምታስጠብቀው እንጂ ሚሰትህም ኾነች ልጆችህ የሚሰጡህ አይደለም።

ወደህና ፈቅደህ አልያም በንዝህላልነትህም የጣልከው የመሪነት ሥልጣንህ ግን ትዳርህን፣ ትውልድንና ሀገርን ሳያሳጣህ አይቀርም፤ ያሳጣሃልም። ምክንያቱም ከተፈጥሮ ስርዓት፣ ከፈጣሪህም መመሪያ ውጪ እየኖርክ ነውና።

የዓለምን ስንፍና ስላለመከተል
=======================================================
ሳተናው! የዓለምን አሉባልታ አትከተል። ደጋግሜ እነግርሃለሁ! ለምትወዳቸው ሰዎች በተለይም ለሴቶች እና ለሕጻናት(ለሚስትህና ለልጆችህ) ካንተ በላይ አዛኝ ከየትም አይመጣም።

ዓለም ግን አንተ የስርዓት ሰው ስትኾን፣ ስርዓትንም ስትሻና እርሱንም ስታስፈጽም አምባገነን፣ ራስወዳድ እና ርህራሄ-ቢስ አድርጋ ስምህን ታጠፋለች።

ሲቀጥልም ለ”ሴቶች መብት የቆመ” ለ”ሕጻናት ደህንነት የሚከራከር” ተቋም ትመሠረትና አንተ ተፈጥሮኣዊ ሚናህን እንዳትወጣ ታሸማቅቅሃለች።

ባለፉት ሳምንታት የ”ሴቶች መብትን” ተገን በማድረግ ወንዱ ላይ ስለሚሠራ የተቀናጀ ሴራ አጫውቼሃለሁ። የወለድካቸውንም ልጆች ካንተ በላይ አሳቢና ተቆርቋሪ በመምሰል አንተንም በመሸወድ ልጆችህን በስርዓት መግራት እንዳትችል እንዴት እንደሚያደርጉህ ልንገርህ።

በዚኽም ሴራ ልጆችህን እየወደድካቸውና እያየሃቸው እንደቀልድ ከስርህ ታጣቸዋለህ። በአካል ባታጣቸውም ልባቸው፣ ኃሳባቸውና ድርጊታቸው ኹሉ ግን ፍጹም ያንተን የአባታቸውንና የአያቶቻቸውን አይመስልም።

በ”ቅድሚያ ለልጆች” ስም አባወራው ላይ የሚሠራው ደባ
======================================================
ሳተናው ልብ አድርግ! ይኽ ኹሉ የተንኮል ሥራ(“የሴቶች እና የሕጻናት መብት” ተብሎ) ዓላማው አንተ አባወራውን መስለብ(ምክንያቱም ለእነርሱ ብለው ሲመጡ አትጨክንምና) ነው። አንተ ላገባሃት ሚስትህ ለወለድካቸውም ልጆች ካንተ የበለጠ የሚጨነቀው ግን እርሱ ማን ነው?

እንቆረቆርላቸዋለን የሚሉት እነርሱ ትዳርህን የሚያፈርሱ፣ ልጆችህን የሚነጥቁህ ሲኾኑ፤ አንተም ይኽንን ፈርተህ የወጣለት አልጫ እንድትኾን፣ ትውልዱንም መረን በማድረግ ሀገርህን ለቀማኞች አሳልፈው የሚሰጡ ናቸው።

ልጆችህ የአንተን መንገድ እንዳይከተሉ፣ እንዳይሰሙህም እየተሠራ ነው። አንተም ስርዓት እንዳታሲዛቸው ቅጣቱን አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እያሉ በ”ሳይንስ” የተደገፈ ክልከላ ያውጁብሃል። በዚህም ልጆችህ ለጊዜው ባንተም ኾነ በስርዓትህ ላይ ሲያምጹ በየማታ የማታ ግን ለምድራዊው መንግስትም ኾነ ለፈጣሪ የማይገዙ አመጸኞች መኾናቸው አይቀሬነው።

ኾኖም ግን እነዚህ አካላት “የሴቶችና የሕጻናት መብት” ብለው በንባቡ ይሸውዱሃል። ነገር ግን ሳተናው! አንተ የፈጣሪህን ቃል ተከተል በልብህም ጽላት ጻፈው ቤትህን የምትመራበትም መመሪያህ እርሱ ይኹን።

ይኸው ቃል እና የአባቶችህም ፈለግ ያንተን፣ የሚስትህንና የልጆችህንም ተፈጥሮ የምታይበት፣ የምትመረምርበትና የምትረዳበትም መሣሪያህ ይኹንህ። በፍጹም ስልጣኔ ገብቶኛል ፍቅርም ዘልቆኛል ብለህ ቃሉን አታስተባብል።

አባወራው በቤትህ አንተ ትቀድማለህ!!!
=================================================
በማዕድ፣ በመቀመጫ፣ በመዝናኛ(ቲቪ/ራዲዮ)፣ በአልባሳት፣ በመንገድ፣ በጸሎት፣ በንግግር እና በሌሎችም አንተ ቅደም። በጭራሽ የፍቅር መግለጫ መስሎህ ልጆችህን አታስቀድም። ይልቁንስ አንተ እነዚህን ስትፈልግ ልጆችህ እንዲያገለግሉህ አድርግ እንጂ።

የቤቱ ንጉስ አንተ ነህና በቤትህ ውስጥ ያለው ግልጋሎት አንተን ያስቀደመ እነርሱን ያስከተለ እንጂ ለልጆችህ ቅድምና የሰጠ አልያም “እኩል” የሚያስኬድ ከኾነ ቤትህን በቅጡ መምራት ይሳንሃል። ልጆችህ ኾድህን አባብተው የቤቱን ስልጣን መሪነቱንም እንዳይቀሙህ ተጠንቀቅ።

በፍጹም አንተ ቆመህ ልጆችህን አታስቀምጥ፣ አንተ ዜና ልታይ ልጆችህን አትለማመጥ፣ እነርሱ ቁጭ ብለው ሠራተኛ አታስታጥብህ፣ አንተ ምሳ ሳትጠግብ ምሳ ለበሉት ልጆችህ ኬክ ለመጋበዝ አትቸኩል፣ አንተ በቅጡ ሳትለብስ ልጆችህን ለማዘነጥ አትጣደፍ።

ሳተናው ልብ አድርግ!
ልጆችህ አንተ የምትታየውን፣ የምትሰማውን(ጠብቆ ይነበብ) እና የምትዳሰሰውን መጋቢና ጠባቂ ምድራዊ አባታቸውን ሳያከብሩ የማይታየውን፣ የማይሰማውን እና የማይዳሰሰውን የሰማዩ አባታቸውን አያከብሩምና።

ለሚስትህም ቢኾን አንተን ማክበር መለኮታዊ ትዕዛዟ ነው (ላንተ እርሷን መውደድ)። ይኽም ባንተና በእርሷ መካከል ለሚፈጠረው የፍቅር ስበትም ኾነ ግለት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት አስተውል።

ሳተናው! ማክበርና መውደድ ትርጉማቸውን፣ አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን መርምር….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *