“በብዙ ሴቶች ተከብቤ ሚስት አጣሁኝ” ላልከኝ

ወዳጄ!

ደግመህ ደጋግመህ ስለሚስት ማጣትህ ስለምን ታወራለህ ትጽፋለህስ? ሚስትን አንተ ትመርጣለህ እንጂ እርሷ ልትመርጥህ ትሻለህን? ወይንስ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ባለባት ሀገር ውስጥ አንድ ላንተ ፈቃድ የተስማማች አጣህ?

ትዝብት በክታበ ገጽህ ላይ
(On The Posts of Your Facebook Profile)
====================!!============
ከንግግሮችህም ኾነ ከክታብ ገጽህ(Facebook) እንደምረዳው አንተም ያኔ እኔ እንዳለፍኩበት የንክር ምስኪንነት ዘመን እያለፍክ መኾንክን ነው። ዐየህ ዓለም በዘፈኖቿ፣ በመገናኛ ብዙኃኖቿ፣ “በኪነጥበቦቿ” እና በመሳሰሉት ለሴቶች ሊኖረን የተገባውን፣ ለዘመናት ጠንካራ ማሕበረሰብ(በምግባር፣ በአስተሳሰብ እና በስልጣኔ) የገነባውን ተፈጥሮኣዊ እውነት ያለውን እውቀትም ኾነ አመለካከት አዛብታብናለች፣ ዋሽታናለችም።

ላንተ በብዙ ሴቶች መከበብ (በገጽህ ዙሪያ)የብዙዎቹን ጭብጨባና ይኹንታም ማግኘት እንደ ትልቅ ነገር ቆጥረኸው እያተረፍክበትም ይመስልሃል። እውነቱን ግን ልንገርህ ትልቅ ነጥብ እየጣልክ ነው። እስቲ አንድ ነገር አስተውል ቢነበብ ሁለት ደቂቃ የሚፈጅ ጽሑፍ በገጽህ ለጥፈህ በግማሽ ደቂቃ ውስጥ በርካቶች ሲወዱትና ሲያጋሩት ከእነርሱም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች ሲኾኑ ጽሑፍህ እንዳልተነበበ አትጠረጥርምን?

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

ደግመህ ደጋግመህ ስለ”ሴቶች መብት”፣ ስለ”ሴቶች መደፈር”፣ ስለ”ሴቶች እኩልነት” በገጽህ ትጽፋለህ(መጻፍህ በፍጹም አይነቀፍም)። ያው ቀደም ብዬ እንደነገርኩህም ጽሑፍህን ሳያነቡ በቅጽበት የሚወዱና የሚያጋሩ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮችም አሉህና እነርሱም “ምነው ወንዱ ሁሉ እንዳንተ አሳቢ በኾነ?” እያሉ “ሲያሞጋግሱህ” አንተ ሐሴት ታደርጋለህ።ነገር ግን አንዳቸውንም እንኳ ብታገኛቸው ባላቸው እንድትኾን የማይፈቅዱ “እርሱኮ ወንድሜ ማለት ነው፣ አንተ እኮ ወንድሜ ማለት ነህ” ሲሉ፤ ድርጊትህ አንተን ከወንድምነትም አልፎ እህታቸው ሊያደርህ እንደሚችል አትጠረጥርም።??

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

በተደጋጋሚ የራስክን ምስል የምትለጥፈው ነገርስ፤ ለሚሰጥህ መወደድና ለተሰጡህ “ሸበላው”፣ “ቆንጆው” ለሚሉ አስተያየቶችስ “አመሰግናለሁ፣ ጠፍተሻል” ለማለት የሞባይል ካርድ ስትሞላስ ከወንድነት ጠባይ እየራቅክ መኾንክን ተገንዝበኸዋልን?

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

ለ”ሴቶች መብት እኩልነት እንጮሃለን” ከሚሉት ሴቶች ክታበ ገጽ(Facebook) ገብተህ ጦማራቸውንና ፎቶኣቸውን ስትወድ፣ አስተያየት ስትሰጥና ስታጋራም ታዝቤያለሁ። ከእነርሱም ጋር በመኾን “አባወራዊ ስርዓት አምባገነን ነው! የሴቶችን መብት የረገጠ ነው!” በማለትም ከብዙዎቹ ጋር ተስማምተሃል ሁሉም ኃሳብህን ወደውታል።

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

ትዝብት በገሃዳዊው ኑሮህ

(On Your real life)

ከብዙ ሴቶች ጋር ሻይ ማኪያቶ እንደምትጠጣ አውቃለሁ። ከብዙዎቹም ጋር ከከተማ ወጥታችሁ እንደተዝናናችሁ፣ የተለያዩ የመንፈሳዊም ኾነ ሀገርህን እወቅ መርሐ-ግብር ላይ አብራችሁ እንዳሳለፋችሁ ሰምቻለሁ። ብዙዎቹም በዙሪያህ ያሉት ሴቶች “ረጃጅምና ቆጃንጆዎች” እይደኾኑ ሰምቻለሁ።

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

የብዙዎች ችግር ደራሽ፣ ለብዙዎችም እንባ አባሽ እንደኾንክ ሰምቻለሁ። ብዙዎችን በማጫወት፣ በመሸኘትና በመንከባከብ ለትዳር እንደምታበቃም አውቃለሁ። እነርሱም ጥሩ ወንድምነትህን ሲመሰክሩ በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ።

ይኹንና ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

ብዙ ሴቶች ያንተን “ንጹሕ” ወንድምነት አድንቀው፣ በዓመለ-ሸጋነትህም ተደምመው ነገር ግን ካንተም ኾነ ከሌሎች ተደብቀው ከዱርዬ ጋር ሲላፉ ትሰማለህ፤ ሰምቼያለሁም። በዚህም ምክንያት እንኳ ችግር ውስጥ ገብተው ጥቂቶቹን ታድገህ ታውቃለህ። ይኼ ጠባይህም በብዙዎቹ ሴቶች ዘንድ እንደሚያስወድድህ ስታውቅ፦

ነገር ግን አሁንም ሚስት አጣሁኝ ትለኛለህ?

ድሮም በትምሕርት ቤት ሳውቅህ እንዲሁ ነበርክ። ሴቶች ሲወዱህ፣ ወንድምነትህን በአንድ ድምጽ ሲመሰክሩና ወንዶች ሁሉ እንዳንተ ቢኾኑ ምኞታቸው እንደኾነ ሲያወሩ ትዝ ይለኛል። ነገር ግን አንዳቸውንም እንኳ ጓደኛ(girlfriend) ማድረግ እንዳልቻልክ እና እነርሱም እንደ ወንድማቸው አይተውህ እሺ እንዳላሉህ አውቃለሁ።

ዛሬም እንደበፊቱ ኑሮህ በክታበ ገጽህም(Facebook) ኾነ በገሃዱ ዓለም ብዙ ሴቶች ተከታዮችን ብታፈራም “በተከራየኋት ክፍል በብቸኝነትና በብርድ የማሳልፈው ሌላ ጨለማ ክረምት ደረሰብኝ” ትለኛለህ።

እንግዲያውስ ጥያቄው ካንተ ይምጣ ብዬ እንጂ እኔማ ይህ እንደሚኾን አስቀድሜ አውቄያለሁ። ንገረኝም ካልከኝ ደስ የማያሰኝህን ነገር ግን ሚስት የምታገኝበትን መንገድ እጠቁምሃለሁ። በዚህ አመለካከትህ ማግባት ያዳግትሃል፤ ማግባትም አይገባህም ደግሞም እንኳንም አላገባህ ብታገባ ኖሮ ወንድ(አባወራ) ሳትኾን ነበርና የምትገባው ብዙ ትቸገር ነበር።

ጥያቄ፦ ብዙ ሴት ጓደኞች እያሉህ፣ ብዙዎቹም ተወዳጅ መኾንህን እየነገሩህ፣ እነርሱም ወንዶች ያንተን አርኣያ እንዲይዙ እየወተወቱ፤ አንተ ወዳጄ ግን ለምን ሚስት አልወጣልህ አለ? ሴቶቹስ አንተ አለህ ካሉት ምግባር በብዙ ያነሰ ወንድ እንዴት አገቡ?

መልሱ፦ አንተ የወጣለት ምስኪን ስለኾንክ ነው። አሁን ወደ መፍትሔው… ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *