በአባወራው ቤት እማወራ የለችም

ሳተናው!

ከዚህ በቀደሙት ሁለት ጦማሮች የአባወራውን ሚስት ከእማወራውዋ ለይተህ ማየት እንድትችል ጽፌያለሁ።

ለማስታወሻ
የአባወራው ሚስት “የአባወራ ሚስት”፣ አልያም “ስንዱ”(ከሚናዋና ከሙያዋ በመነሳት) ብትባል እንጂ እማወራ አትባልም። እማወራ የምንላት ሴት ግን ባሏ በቤቱ ኖረም አልኖረም ፈቀደም አልፈቀደም(ተገዶም ይኹን በፈቃዱ) ቤቱን የምታስተዳድረዋ ሴት ናት።

የአባወራው ሚስት ተፈጥሮኣዊ ሚናዋን የምታውቅ ፣ እርሱንም የምትፈጽም፣ በመፈጸሟም የተፈጠረችለትን ዓላማ በማሳካቷ ደስታ የሚሰማት ናት። ይኽንንም ሚናዋን ምን አጓጊ የኾነ ሥራ፣ “ሕልም”፣ ዝንባሌ ቢኖራት እኳ የማትለውጥ፣ የማትተው፣ የማትንቅም ናት።

አባወራውም ደግሞ ይኼንን ተፈጥሮኣዊ ሚናዋን ቢያግዝ፣ ቢደግፍ፣ እንጂ አይገፋውም፣ አይጠቀልለውም፣ እርሷንም አይንቅበትም፣ አይቀማትምም፤ ጸጋውም የለውምና። ይልቁንስ እርሷን በሚናዋ እንደ መተው እና እርሱም በሚናው እንደ መሰየም፣ ሚናዋንም መወጣቷን አይቶ እንደማመስገንና እንደመሸለምም ያለ መተጋገዝ አይኖርም፤ ቢኖርም ይኼንን አይመጥንም።

ለእማወራዋ ግን በተፈጥሮኣዊ ሚና መገኘት እርሱንም መወጣት “ለወንድ ማጎብደድ”፣ “በበታችት(በባርነት) መኖር”፣ “ከሰው(ከጓደኛ) በታች መኾን” ይባላልና፣ ሲባልም ትሰማለችና መስሎም ይታያታልና በቦታዋ አትሰየምም።

በተለይም ደግሞ ስንፍናውንና ፍርኃቱን በ”መንፈሳዊነት” እና በ”ፍቅር” ስም እያስታከ የሚኖር አልጫ ባል ካላት የእርሷንም ሚና ወስዶ ጠቅልሎ በመያዝ ይዳክራል። እርሷም የወደደውን ለቅቃለት(ትታለት) ያልቻለበትን መሪነት ትረከበዋለች።

ይኼ የኋለኛው በተለይ በብዙ የዘመናችን ትዳሮች በተለይም በአብዛኛው ከተማ ቀመስ በኾኑት  ቤቶች ላይ ይስተዋላል።

በተለይ በዘመናችን “የተማሩት” ሴቶች(ሁሉንም አላልኩም) የምዕራባውያን የሴታቆርቋዥ (Feminism) የ”ነፃነት” እና በእርሱም የሚገኘው የ”ደስታ” ትርክት ልባቸውን አጥፍቶታል።

ከዚኽም የተነሳ ትዳር ከመመሥረት ይልቅ ቁሳዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ስልጣናዊ፣ ስልጣኔያዊ(ሰይጣናዊ) ሕልማቸውን ለማሳካት ሲሉ ወርቃማ እና እሸት(ለጋ) እድሜያቸውን (ጊዜያቸውን) የሚያባክኑ ናቸው።

እነዚኽ የእማወራነት አባዜ የያዛቸው ሴቶች ቀድመው በለጋ እድሜያቸው ቢያገቡም እንኳ ፈጣሪ ለእንቦቀቅላ ልጆቻቸው የሰጠውን ምትክ የለሹን የጡት ወተት የሚነፍጉ ናቸው። ስለ ራሳቸው ጥቅም በልጆቻቸው ላይ መጨከናቸው ሳያንስ መልሰው ለእነርሱ “(ለልጆችና ለሴቶች) መብት ቆመናል” ብለው ያፌዛሉ።

በዚኽም ብቻ አያበቁም የገዛ ልጆቻቸውን ተንከባክቦ፣ ለማሳደግ(ለማብላት፣ ለማጠጣት) አልያም “ምን አገኙ? ምንስ አገኛቸው?” ለማለት እንኳ ባላቸውን የሚሞግቱ፣ ሙግቱንም ችሎት ፊት ከማቅረብ የማይቦዝኑ ናቸው። “ለምን?” ብትሉ ለእነርሱ ከልጆቻቸው የሚበልጥ ሕልም (ሥራ፣ ትምሕርት)፣ ዝንባሌ፣ ጨዋታ አለባቸውና ነው።

በእማወራ እናት የሚያድጉ ልጆች (ቆፍጣና አባት የሌላቸው) የሞግዚት ሰለባ የመኾን እድላቸው ሰፊ ነው። ባይኾኑም እንኳ ከአመጋገባቸው ስርዓት ማጣት የተነሳ ከእድሜያቸው ጋር ያልተመጣጠነ የሚዋዥቅም የአእምሮ፣ የመንፈስ(የስነልቦና) እና የአካል እድገት ይታይባቸዋል።

እማወራ በምታስተዳድረው ቤት ውስጥ ባል(ካለ) ስጉ(ፈሪ) ነው። አጥፍቶ አይደለም እርሷ ባጠፋችው ይቅርታ ጠያቂ እርሱ ነው። ዘወትር አለመግባባት ሲከሰት ትዳሩ ፍቺ ፍቺ፣ ቤቱ ፍራሽ ፍራሽ(የፈረሰ)፣ ቤተሰቡም እንደትቢያ ብንን ብንን ይላል። ይኽም እማወራዋ ባሏ ላይም ኾነ ልጆቿ ላይ የምታሳርፈው የዛቻ ጅራፍ ነው።

ማሳሰቢያ
ይኽ የእማወራ ገለጻ የማይወክላት ወይም የማይገልጻት፣ ባሏን በእግዜር በሽታም ኾነ በአደጋ አጥታው ነገር ግን “ወንድ ከሱ ወዲያ ላሳር” ብላ የምትኖረዋን አያካትትም። እርሷስ ልዩ ናት።  ልዩነቷም ባሏን ከነሙሉ ክብሩ በልቧ ይዛ ራሷን፣ ልጆቿን እና ቤቷን እርሱ በሠራላት ስርዓት አስከብራ የምትኖር ናት። ስርዓቱን ከነ አፈጻጸሙ ምግባሩንም ከነ አኗኗሩ በመያዝ ለልጆቿም አርኣያ የምትኾን በዚኽም ባሏን በተለይም ራሷን የምታስመሰግን ናት።

ማጠቃለያ
እማወራ ከአባወራ ቤት አትገኝም። በዚኽ ዐውደ ንባብ እማወራ ስል አባወራ (አባት፣ ባል፣ ወንድ፣ ራስ) የማትፈልግ ናት። እርሷ ከ”መማሯና”፣ ከ”መሰልጠኗ” የተነሳ ለባሏ የምታሳየው ትሕትና የሌላት፣፤ በጠቅላላው ወንዶችን የምትንቅ በተለይም ባሏን በአደባባይም ቢኾን ከመዘርጠጥ ወደ ኋላ የማትል ይኼንንም ወግ መስሏት የምትመካበት ናት።

ሳተናው!
ይኽ አንተን ለማስደሰትም ኾነ ለማስከፋት አልተጻፈም። ጣፈጠህም መረረህም ይኸ ደረቅ እውነት ነው። ይልቁንስ አንተ ከወዴት እንደበቀልክ፣ እንዴትም እንዳደግክ መርምር አቋምህንም ማስተካከል ሲቻልህ ለስንፍናህ(ለድካምህ) ሰበብ አታብጅ።

……

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *