በጠዋት ስለ መነሳት

(ከሰኞ እስከሰኞ ከዓመት እስከ ዓመት)

እንግዲህ አባወራ መኾን ፈልገህ የለ? ስንፍናን፣ በራድነትን ገፈህ ልትጥል አይደል? በጠዋት የመነሳት ልምድ ከሌለህ አኹኑኑ ጀምር።

👉ድሮ ድሬ እያለሁ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩበት የብስራተ ገብርኤል ት/ቤትን ከማስታውስባቸው ነገሮች አንዱ የሚከተለው ጥቅስ ነበር።
“Early to bed early to rise makes a man healthy, wealthy and wise” Benjamin Franklin
👉 ሲቀጥል በልጅነቴ አንድም ቀን አባቴን ቀድሜ የተነሳሁበት ቀን ትዝ አይለኝም። ሁልጊዜ ከሁላችንም ቀድሞ በመነሳት በግቢ ውስጥ ብዙ ሥራዎችን ሠርቶ እናያለን ጽናቱም ያስደምመን ነበር።
👉የምሥራቋ ከተማ ድሬን ፀሐይ ጠዋት በብርሃኗ ብቻ ሳይኾን በሙቀቷም የምትቀሰቅሳት ናትና የመተኛት እድል አትሰጥም።

እነዚህ ሦስት ነጥቦች እኔን በጠዋት የመነሳት ልምድ ሰጥተውኛል።

👍ወንድሜ ቀንህን በንቃትና በትጋት ለማሳለፍ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ አልጋህ ላይ እያለህ ፀሐይ አትውጣብህ። ግዕዛን የሌላቸው ወፎች እንኳ በደመነፍስ ሰላም ስለማደራቸው ሲያመሰግኑ እየሰማህ፤ “ድቅድቁ ጨለማ ተገፈፈ የብርሃን ተስፋ ፈነጠቀ” እያሉ ሲያወድሱ እየሰማህ፤ አንተ በአርአያው የፈጠረህ ልጁ እንዴት አስችሎህ ትተኛለህ።

ትላንትን አልፈህ ዛሬ የመኖርህ ምክንያት ከታናሹ ሞት(እንቅልፍ) ተቀስቅሰህ የመንቃትህም ጉዳይ የተፈጠርክበትን ዐላማ ያልጨረስክ፣ ዛሬም ሥራ ስላለህ ነውና ጠዋትህን በአኮቴት(በምስጋና) ጀምር።

ጠዋት በመነሳትህ፦
፩ኛ ውጤታማነትህ ይጨምራል፦ አእምሮህ ታድሶ መነሳቱና ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት መተኛታቸው በዚህ ሰዓት የምትሠራቸውን ሥራዎች ውጤታማነት ይጨምራል። ተማሪ ብትኾን ብታነብ፣ ደራሲ ብትኾን ብትጽፍ፣ መንፈሳዊ ብትኾን በታረምም ብትደመም ይህ የተሻለ ሰዓት ነው።

፪ኛ ዐዳዲስ ሐሳቦችን ለማፍለቅ፦
ቀን ለምትሠራቸው ሥራዎችም ኾነ ሌሎች ማሕበራዊም ኾነ ግላዊ ጉዳዮችህ ዐዳዲስ ኃሳቦችን ለማፍለቅና ለመገምገም ይረዳሃል።

፫ የአእምሮህን ውጥረት ትቀንሳለህ፦
ቀን በብዙ ግጭቶች የዛለውን አእምሮህን ተጨማሪ ሥራ ከምትሰጠው በጊዜ እንዲያርፍ እድል ሰጥተህ ጠዋት ከታደሰ በኋላ ብታስብበት አይለግምም አይወጠርምም።

ይኼንን ለማድረግ ደግሞ
፩ኛ በጊዜ መተኛት፦ ወንድሜ የፌስቡክ፣ የፊልም፣ የጌም፣….. ቀበኛ ኾነህ ከማምሸት በጊዜ የመተኛት ልምድ ይኑርህ። ነገ ሌላ ሥራ ነገ ሌላ ኃላፊነት ይጠብቅሃል።

በተቻለህ መጠን የTV እና የFacebook አጠቃቀምህን ወደ ዜሮ አስጠጋው ከቁም ነገራቸው ይልቅ በዋዛ ፈዛዛቸው ጊዜህን መብላታቸው የዐለምን እውነታ እንዳትረዳ ይጋርድሃል።

፪ኛ በጠዋት መነሳትን ጥቂት በጥቂት ተለማመድ
እስከዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ስትነሳ ከነበረ ነገ 11፡00 ሰዓት ለመነሳት አትሞክር። ባይኾን 12፡30 ከዛም 12፡00 እያልክ አሻሽል እንጂ።

፫ኛ ማንቂያ ደውልህን(Alarm) ካንተ አርቅ
ይኼን ብዙዎቻችን እናደርገዋለን። በእንቅልፍ ልብ ደውሉን(Alarm) ፈልጎ ማጥፋት። አንተ ግን ዐላማ አለህና ማንቂያ ደውልህን ካንተ አርቀህ አስቀምጥ።

፬ኛ ስትነሳ አንድ ቋሚ ሥራ ይኑርህ
ጠዋት ተነስተህ የምትሠራው ሥራ ከሌለህ ወይም ግራ ከገባህ ተመልሰህ መተኛትህ ነው። ስለዚህ ቢያንስ እለት እለት የማይቀር አንድ ከቻልክም ኹለት ሦስት ሥራ ይኑርህ። ማስታኮት(ማመስገን)፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከምሳሌ ይጠቀሳሉ።

፭ኛ ራስህን አንቃ
በቀዝቃዛ ውሃ ፊትህን ከደፈርክም ገላህን ታጠብ።ቀለል ያለ ልብስም ልበስ ተጀቧቡነህ ብትቀመጥ እንቅልፍ ይጥልሃል።

፮ኛ ሥርዓት መር ኹን
ይኽንን ማድረግ ከቻልክና ልምድ ሲኾንልህ ሌሎችንም ያንተ እንዲኾኑ የምትሻቸውን ልምዶች እንዲሁ ገንዘብ(ያንተ)ማድረግ ይቻልሃልና የጠዋት ግብሮችህን እንደቅደም ተከተላቸው ፈጽማቸው።

ውሳኔህና ጽናትህ ሥራውን ይሠሩታልና ፉከራውን አልያም ሰበቡን ትተህ ተነስተህ በጊዜ ተኛ።
ጠዋት ተነስተህ አእምሮህን በንባብ፣ መንፈስህን በአኮቴት፣ ማሕደራቸውን(ማደሪያቸውን) ሰውነትህን ደግሞ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ አስታጥቅ።

ሀገርህ፣ ወገንህ፣ ቤተሰብህ፣ ሚስትህ ልጆችህ ፈጣሪ የሰጣቸው በምድር ላይ የሚያዩት ተስፋ (አርአያ) አንተ ነህ የዓለምን እንቶ ፈንቶ ለመቃረም ቦታና ጊዜ አይኑርህ።

ከደረትህ ሰፋ ከወገብህ ጠበብ ተደርገህ ትልልቅ ጡንቻዎችንም የተቸርከው ባጋጣሚ ሳይኾን በምክንያት ለዓላማ ….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *