በፈተና ስለመሠራት

(ወረቅ በእሳት እንዲነጠር(እንዲወጣ) ጀግናም በፈተና ይጠራል(ይወለዳል))

ወንድሜ ድሮ ከትምሕርት ቤት ታሪክህ ብትማር ፈተናን ሰነፍ ተማሪ እንጂ ጎበዝ ተማሪ አይፈራም። ምንም እንኳ ተማሪ ምን ጎበዝ ቢኾንም ፈተና ካልተፈተንኩ ብሎ እንዳያስቸግር ወላጆችም ትምሕርት ቤት ብዙ ገንዘብ ከፍለው የሚያስተምሩበት ዐላማ ለፈተና ባይኾንም ከተማርን ግን መፈተናችን እርግጥ ነው።

ፈተናዎች ታዲያ እኛ ከክፍል ክፍል የሚያዛውረን እውቀታችንን የሚሞግቱ የዘነጋናቸውን የሚያስታውሱ ናቸው። እነዚህ ፈተናዎች ባይኖሩ ግን ትምሕርት ምን ዐይነት መልክ ይኖረው እንደኾነ መገመት ከባድ አይኾንም።

በሕይወትህም እንዲኹ ነው ምንም እንኳ ፈተናን ላክልኝ ተብሎ ባይለመንም እንኳ ዐይነቱና መጠኑ እየተለያየ ፈተና በእኛ ላይ መፈራረቁ አይቀርም። ከእኛ የሚጠበቀው እንደ መምሕራችን የፈተናውን ጽዋ ከኛ እንዲያርቅ መጸለይ ብቻ ነው። እርሱ በፈቀደ መጠን ግን መፈተናችን አስተዋይ ልቡና ካለን ደግሞ መውጫውንም መታደላችን እርግጥ ነው።፩ኛ ቆር፲፥፲፫

ይኹንና ፈተና ለብልህ ሰው ራሱን በጸጋ (በመንፈሳዊ ጥበብ) የሚያሳድግበት ትክክለኛ ራሱንም የሚያገኝበት፣ ትምሕርት ቤት ነው። ከዚህም ብዙ ከራሳቸው አልፈው ለሰው የተረፉ ጥበበኞች ተመርቀውበታል።

ቢላዋና እርሳስን በዚህ ጊዜ አለማሰብ አይቻልም።

ቢላዋ ለሚፈለግበት ዐላማ ይውል ዘንድ ከብረትነቱ ይበልጥ ስለትነቱ ተፈላጊ ነው። ስለዚህም ያለርሕራሔ ዱልዱማቱን መሞረድ፣ ማስወገድና ስለቱን ማውጣት ግድ ይላል። አለበለዚያ ቢላዋ የሚለው ስም አይገባውም።

ለእርሳስም እንዲኹ በስለታሙ መቅረጫ ገላው ተገፎ ነው የምንጠቀምበት።

ማስተዋል ያለብን ታዲያ ቢላዋውን የመሞረዱም ኾነ እርሳሱን የመቅረጹ ሥራ የአንድ ጊዜ ሳይኾን ተከታታይነት ያለው መኾኑን ነው።

ለአባወራም እንዲኹ ነው

ወንድ ልጅ ራሱን ፣ ቤቱን፣ ሚስቱን፣ አምልኮውን፣ ሀገሩን ለመምራት የሚያስችሉትን ጸጋዎች ተሟልቶ ተሰጥቶታል። ነገር ግን መሪ አድርጎ መቅረጽ የራሱ የግለሰቡ፣ የቤተሰቡ፣ የማሕበረሰቡ ሥራ ነው።

አንተ ወደዚህ በተፈጥሮ ወደተሰጠህ የመሪነት ሚና መምጣት ትሻለህን? ወይስ …. መልስህ አዎን ከኾነ ግን እንደ ቢላዎውና እንደ እርሳሱ ለመሠራት ዝግጁ ኹን። ያንተ ሞረድ ያንተ መቅረጫ ግን የሕይወትህ ፈተና ነው።

ቢላዎ ሞረድን ፈርቶ ቢላዎነትን እንደማያስጠብቅ፤ እርሳስም መቅረጫን ሸሽቶ እርሳስ መኾን እንዳይችል፤ አንተም ፈተናን ሸሽተህ አባወራ መኾን አትችልም።

አባወራነትን ስላገባህ ብቻ፣ ቆመህ መሽናትም ስለቻልክ፣ አልያም ሱሪ ስለታጠቅክ፣ ወይም ማስረገዝ ስለቻልክ አታገኘውም። ብዙዎች(በተለይ የዛሬ ወንዶች) በዚህ ስር የሚመደቡ ናቸው።

አንተ አባወራ ስትኾን ራስህን፣ ቤትህን፣ ሚስትህን፣ ልጆችህን መምራት ስነሥርዓት ማስያዝ(መምከር፣ መገሰጽ፣ መቅጣት) አለብህ፤ አባትነትህን፣ ባልነትህን፣ ወንድነትህን፣ ራስነትህን ሳትዘነጋ መገኘት አለብህ። ይኼን ለማድረግ ስትወስን እና ማድረግም ስትጀምር ያን ጊዜ ፈተና(ሞራጅህ፣ መቅረጫህ) ወዳንተ ይገሰግሳል።

ልብ አድርግ! ፈተና ወዳንተ እስከመጣ ድረስ ክብርህን ጠብቀህ፣ በወጉ ታጥቀህ፣ በማዕረግህ ኾነህ እንደ ጀግና ፊትለፊት ተጋፈጠው እንጂ ራስህን(ክብርህን) ጥለህ በጭራሽ ዝቅ ብለህ አታሳልፈው። ወዳጄ ይኽ ፈተናም ስታገለው ይሠራኛል፣ ይቀርጸኛል፣ ያገዝፈኛል በል እንጂ በጭራሽ ያፈርሰኛል፣ ያጠፋኛል፣ ያኮስሰኛል አትበል። እንደአፍህ እንዳይኾንም ተጠንቀቅ።

አንተን እንዲህ ደፍሬ በራስህ ላይ እንድትጨክን የምመክርህ እኔ እነዚህን ፈተናዎች ፈርቼ በምስኪንነት ከኖርኩበት ዘመን ይልቅ ወደ አባወራነት ማማ ለመውጣት በማደርገው ጥረት በተፈተንኩት ብዙ አትርፌያለሁና ነው።

አዎን ፈተናን ማንም ከተኛችበት ቀስቅሶ ከጉያው አይከታትም። ነገር ግን አንተ ራስህን ስትኾን፣ ተፈጥሮህን ስታደንቅ፣ በሚናህ ድርድር ስታቆም፣ የስነሥርዓት ሰው ስትኾን ሌላም ሌላም…..እስከዛሬ ያወራናቸው የአባወራውን ስብዕና መያዝ ስትጀምር ያኔ ፈተና ይመጣል፣ ያኔ ትምሕርትህ ተጀመረ ማለት ነው።

ይኼን ጊዜ ፈተናውን ሳይኾን ከፈተናው ኋላ ያለውን ቁም ነገር አስተውል፤ ምን እማርበታለሁም በል።

ትልቁ ፈተናህ፦ ትልቁ ሞረድህ ትልቁ መቅረጫህ ነው። እርሱም አንተን ከመቼውም ጊዜ ከማንኛውም ሰው የበለጠ የሚቀርጽህ ሲኾን ብዙ ወንድ ግን እድለቢስነት፣ አለመባረክ፣ አለመታደልም ብሎ የሚያስበው ነው።

ብታስተውል
የነጠረ ራስህን፣ የሚና ቦታህን፣ የጠራ ዐላማህን ከብዙ እርባና ቢስ ግሳንግሶችህ ውስጥ ሞርዳ የምትቀርጽህ ሚስትህ ናት። ይኽ የሚኾነው ግን ከእርሷ ጋር መጋጨትን እስካልፈራህ እስከፈቀድክም ድረስ ብቻ ነው። ….ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *