ባልሽን ኩሽና ባላስገባሽ እጅሽን በ’ጅሽ ባ’ላጣሽ

(ምን ይለኛል ብቀኘው፤ ይፈታልኛ)

(ካለፈው የቀጠለ)
ቀድሜ እንደገለጽኩላችኹ ወንዶች የመጋቢነት ሙያውን ያለጸጋቸው ሲወስዱ አስቀድሞ የነበራቸውን፣ ያስወደዳቸውን(የሚያስወድዳቸውን)፣ ጠባይ ያጣሉ። በተፈጥሮኣችን ዋነኛው ሴቶችን ከወንዶች የሚለየው ስሜታዊነት ነው(ሴቶች በአብዛኛው ስሜታዊ ናቸው)። የቤተሰቡን አባላት እንደየዓመላቸው ለማሳደር ስሜታቸውንም ለመረዳት ተረድቶም ለመመገብ ስሜታዊ መኾንን ይሻል። ምክንያቱ ደግሞ ስሜት ከስሜት ተናባባቢ ነውና።

ስለዚህም ወንዱ በተፈጥሮው ምንም እንኳ ቆዳው ወፍራም(ከስሜታዊነት የራቀ) ቢኾንም ቅሉ በዓዲሱ ልምምድ ግን ስሜታዊነት ገንዘቡ ይኾናል። ታዲያ ስሜታዊ ቢኾን ምንድነው ችግሩ? ችግሩማ ሚስት ስሜታዊ ናት “እንዲህ ነኝ” ባትልም መኾኗን ታውቀዋለች። ጾታዊ ፍቅር ውስጥ ስትገባ ግን ፍላጎቷን ስሜቷን ተረድቶ የሚያደርስ፣ ጥሟንም የሚቆርጥ እንጂ በእርሷ ወደብ ፈላጊነት ላይ የሚደመር ሌላ ስሜት የሚነዳው “ወንድ” አትሻም (ቢያንስ ምክንያቱን ባትገልጸው ወንዱ ግን አይማርካትም)።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ወደ መጋቢነት ያስገባችው ለቤተሰቡ የተንከባካቢነት ሚናን በብዙ እጅ ያስያዘችው ባሏ ስሜታዊነቱ ለጾታዊ ፈቃዷ ለወሲባዊ መሻቷ እንዳትነሳሳ ይዳርጋታል። ባሏን እኮ ትወደዋለች፣ ባሏ እኮ “እንደሌሎች” ወንዶች አይደለም። አሳቢነቱ እና ተንከባካቢነቱ ከቤተዘመድ እስከ ባዕድ፣ ከጎረቤት እስከ መሥሪያቤት የተመሠከረለት ነው።ግና የቀናቸው መቋጫ፣ የድካማቸው ማስረሻ፣ የፍቅራቸው ማጣፈጫ፣ ለናፍቆታቸው እረፍት የኾነው ወሲብ ጋር ስትመጣ ግን ልቧ ለእርሱ ቦታ አይኖርም። ምክንያቱን እርሷም አታውቀውም፤ አልያም የመሰላትን ምክንያት ትሰይማለች።

*** ከዚህ ቀደም ስለተቃራኒ ዋልታዎች ጠባይ የተነጋገርነውን አስታውስ***

ባሏ ግን ምንድነው የኾነው? ምንስ ዐይነት ለውጥ ተለውጦ ነው? ስንል በጥቅሉ ስሜታዊ(sensitive or emotional) ሰው ነው የኾነው።

ከዚህ ቀደም የሚኾነውን ይኾናል የማይኾነውን አይኾንም የሚል የነበረ አኹን ግን የመጋቢነት ሚናውን ሲረከብ በአቋሙ ከመጽናት ይልቅ በተመጋቢው ወገን ስሜት ላይ የተመረኮዘ አቋም ይታይበታል። ይኼ ደግም ላይ ላዩን ስታዩት ጥሩ የሚመስል ነው፤ የእርሷን ይመስላልና። ይኹን እንጂ ይኽ ተመሳሳይነት በፊናው ደግሞ ኹለቱን ጾታዎች ያራርቃቸዋል (like poles repel each other)።

*ሲቀጥል ይኼ ስሜታዊነቱ ለሚስቱም ኾነ ለልጆቹ ወደብ ከመኾን ይልቅ በተለይ በሚስቱ የስሜት ማዕበል ላይ ሞገድ የሚጨምር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ…… ነው።

* በሚፈልገውም ነገር ግልጽ አይኾንም(ከወሲብ ጀምሮ…)

* ግልጽም ስለማይኾን ሚስቱም ኾነ ልጆቹ እርሱን ለማስደሰት ይቸገራሉ። በሒደትም አይፈልጉም።

* የሚፈልገውን ነገር አያገኝም፤ አይሰጠውምም ግልጽ አይደለምና።

*እድሜው ሲገፋ ሚስቱም ኾነ ልጆቹ እየራቁት ብስጩና ብቸኛ ይኾናል።

*ግልጽ ሳይኾን ቀርቶ ራሱ ጎትቶ ያመጣው መኾኑን ረስቶ ፍላጎቱን ማመቁ ብስጭቱንም ማፈኑ የኑሮ ዘዴ መንፈሳዊ ልምምድም ሊመስለው ይችላል።

*ፍላጎቱ ባይፈጸምለት ዝምታ አልያም ኩርፊያ የግሉ ነው።

* ልጆቹን በወጉ መቅጣት አይኾንለትም። የታመቀ ብስጭት በጉያው ነውና ቁጣው ስሜታዊ ኾኖ ያስደነግጣል እንጂ አያስተምርም።

* ከስሜታዊነቱ የተነሳ እርሱ የራሱ የኾነውን ከመናገር ይልቅ ሰዎች መስማት የሚፈልጉትን በመናገር ስሜታቸውን መጠበቅ ይሻል።

* ሰዎች ስለእርሱ ሥራም ኾነ አቋም ያላቸው አስተያየት ያስጨንቀዋል።

* የሚሠራው ሥራ ትክክል ነው አይደለም ብሎ ሳይኾን የሚሠራላቸው ሰዎችን ስሜት የጠበቀ ያስደስታቸዋልም ብሎ ያሰበውን ነው።

* ብዙውን ጊዜ በቤት ውስጥ ሥራዎች አሰልቺነትና በሌለውም ጸጋ የመውተርተሩ ነገር ተጨምሮበት በውጭ ሥራ የደከመው የሰውነቱን ወኔ፣ ኃይል፣ ደም ሙጥጥ አድርጎ ይወስድበታል።

* በአልጋቸው ጨዋታ ለሚስቱ የሚቀር ደም፣ ወኔ አይኖረውም። ልብ አድርግ በተፈጥሮ ሰጪ አንተ ነህ እርሷ ደግሞ ተቀባይ ይኹንና በተሟጠጠው ደምና ወኔህ እንደነገሩ ተንጎዳጉደህ እንደመውደቅ ለሚስትህ ቅስሟን የሚሰብር ነገር የለም። ለነጋ ጠባ የጭቅጭቅ ቁርስም ይዳርግሃል።

ይኼ ኹሉ እንግዲህ “ምን አድርጌ ላስደስታቸው”? “ምን ሠርቼ ልጠብቃቸው?” እያለ ሚስቱንም ኾነ ልጆቹን አብስሎ የሚያበላ፣ አብልቶም የሚያስተኛ በነገሮች ኹሉ ስሜታቸውን ለመጠበቅ የሚሞክር ወንድ መገለጫ ናቸው።
በተጨማሪም “ባሌ የልጆቹን ሽንት ጨርቅ በመቀየር፣ ልጆቹን በማብላት፣ በማስተኛት ወዘተርፈ ካላገዘኝ” ለምትል ሴት “እጄን በእጄ” የሚያሰኛት የጥፋት ሥራ ይኾናል።

ወንድሜ በጄ ብለህ ስማ! ትወድህ ይኾናል ግን ባለውለታዋ ኾነህ ትቀራለህ እንጂ ጾታዊ ፍላጎቱ፣ የወሲብ ግለቱ፣ የመዳራት ወላፈኑ ሲያምርህ ይቀራል።

ሩቅ ዐልመህ የጀመርከው ሕይወትህ፣ “ሚስትህን ልትማርክበት” በገባህበት ሥራ ሚስትህ ስትማረርብህ ትዳርህም ከእጅህ ሊያመልጥ ሲሙለጨለጭ ያን ጊዜ ማጣፊያው አጭር ይኾናል። ከምዕራብያውያን ተሞክሮን ስትወስድ ወንድሜ ይኼንን ግን ተወው ፍቺያቸውንም አብረህ ትቅመዋለህና።

ብንኖር ታዲያ “ወንዱ(ባሏ) ምን ሠርቶ ያግዛት?” ….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *