ባንተ ልዕልና እና በእርሷ ትሕትና ስለሚኾነው

ሳተናው!

አንተ ትዳርህን በአባወራነትህ ስትመራ እና ሚስትህም ስትከተልህ በመካከላችሁ መተማመን፣ ተግባቦት፣ መዋደድና አክብሮት ኖሮ ነው። ይኼንን ለመተግበር ምንም የተወሳሰበ ምርምር፣ እልህ አስጨራሽ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር አልያም ደግሞ እሰጥ አገባ አያስፈልገውም።

ትዳርን እንደተቋም የመሠረተ በእርሱም ውስጥ ያለውን ዓላማ የሰጠን ፈጣሪ ምንም በማያሻሙ ቃላት ግልጽ አድርጎ ሚናችንን አስቀምጦልናል። ሰምቶ መተግበር ያንተ ፈንታ፤ ተጠቃሚውም አንተ እና ዘርህ ናችሁ። የተጻፈውን ከስጋም ኾነ ሌላ ፈቃድ የተነሳ አጣሞ መተርጎም ያልተጻፈውንም መረዳት ጉዳቱ ላንተም ኾነ ለትውልድህ ይተርፋል።

ይኸውም በቀላል አረፍተ ነገር ሲቀመጥ ትዳርህን አንተ ትመራለህ ሚስትህ ትከተላለች አለቀ።

ማሳሰቢያ!
ሳተናው!
ዐለም በተለይም በሴታቆርቋዡ (Feminism) አንተርሳ ዘወትር የምትግትህን የጾታ እኩልነት ከዚህ መርህ ጋር ለማስታረቅ ወይም አብሮ ለማስኬድ አትሞክር። ምክንያቱም የዐለም ተልዕኮ ይኼንን ጥንታዊ ተቋም(ትዳር) መናድ ነውና በፍጹም አይገጥምልህም።

አንተ በትዳርህ ያለህ የልዕልና ብሎም የመሪነት ሚና ሚስትህ ካላት የትሕትና ብሎ የተከታይነት ሚና ጋር ተጋጭቶ በተፈጥሮ ከጎንህ የመገኘቷን ነገር(አቻነቷን) አያፋልስም።

በአንተ የልዕልና እና በእርሷ የትሕትና ወይም በሁለታችሁ ባለ ዋልታነት መካከል በሚፈጠረው የኃይል ቅብብሎሽ ከፍተኘኛ የኾነ ጉልበት ያለው ተኣምር መሥራት የሚያስችል አቅም ይገኛል፤ እርሱም ፍቅር ይባላል።

ሳተናው!
ይኼንን ዓይነቱን ፍቅር ለማግኘት/ለማትረፍ ግን እርሷ ትዳሩን የመምራትና የመቆጣጠሩን ሚና ላንተ ለቃ፣ ውሳኔና ምሪት ከሚፈልጉ ጉዳዮችም ራሷን አርቃ ተፈጥሮዋን የማየት፣ የማወቅ፣ የማበልጸግና የመንከባከብም ሥራ ላይ ብታተኩር፤ አንተም የተሰጠህን የመሪነት ሚና ከልዕልና ቦታህ ኾነህ ምክር ዝክር ሳታበዛ በጉዳዮቻችሁ ላይ ቆራጥ አቋምና ውሳኔ ብትይዝ ይሳካል።

ማስጠንቀቂያ!
“ሁለታችንም ግን መሪና ተመሪ ሳይኖርብን በእኩልነት ቤታችንን ብንመራስ?” ትለኝ እንደኾነ፦ በመካከላችሁ ሊፈጠርና ሊኖር የሚገባው ወሲባዊ ትንታግ(ወሲባዊ ፈቃድ) ታጡታላችሁ እልሃለሁ።

ይኽ የወሲብ ፈቃዳችሁ ትንታግ ደግሞ በጾታችሁ ልዩነት(በዋልታነታችሁ) ብቻ የሚመጣ ነው። የ”እኩልነት”ማ ፍሬ የኑሮ ረዳት፣ አብሮ አደር ጓደኛ ያደርጋችሁና ልጆች ማሳደግ፣ የኑሮን ቀዳዳ ለመሸፈን ደፋ ቀና ማለት፣ የቤት ውስጥ ሥራን መከወን የሕይወት ዘመን ግብ ያደርግባችኋል።

አኹን ላይ በየሚዲያው ስለ ወንድና ስለ ሴት እኩልነት ሲለፈፍ ትሰማለህ። ይኹን እንጂ እኛ ሰዎች እንደመኾናችንን የጾታችን ልዩነት ግን የማያወዳድረን፣ የማያበላልጠን በቦታችን ግን ልከኞች፣ አንዳችንም ያንዳችን ግጣሞች ነን።

ራሳችንን ስናውቅ ቦታችንን እናገኘዋለን። በቦታችንም ተገኝተን የተሰጠንን ሚና ስንወጣ ትዳራችን ይሰምራል ፍሬያማም እንኾናለን።

ለዘመናት ትዳርን መሪ የነበረው አባወራ አሁን አሁን በሚዲያው፣ በሕግ አካላትና በልሂቃኑ በሚደርስበት ነቀፋና መገፋት የተነሳ አንገቱን ደፍቶ የሚኖር ምስኪን፣ ሚናውንም ለመወጣት የሚፈራ አልጫ ኾኗል።

ከዚኽም የተነሳ የዛሬዋ ሴት(ሚስት) በሴታቆርቋዦቹ(Feminists) የውሸት ትርክት ተጠልፋ በዐለማዊው ትምሕርት፣ በኃብቱ፣ በሥልጣኑ እየበለጸገች ስትመጣ፤ እንዲሁም ከምትወደው ባሏ ይልቅ  በሚረቀቁት የቤተሰብ ሕግጋት ስትመካ ትዳሯን ታፈርሳለች። ከዚህም የተነሳ ቤተሰብ ይበተናል።

እነኾም ዛሬ ያለ አባት ልጆችን ማሳደግ “ጀግኒት” እያሰኘ፣ ያለ ባል ማርገዝ እንደ “መብት?” እየተቆጠረ፣ ያለወንድ መኖር ራስን በ”መቻል” እየተሞካሸ፣ ያለ ራስ(መሪ)መኖር ራስን “ማወቅ” እየተባለ ይወደሳል። ይኼም “አባወራ አያስፈልገንም እኛ ለእኛ በቂ ነን” የሚያስብል አንድምታ አለው።

ይኹንና ይኽ ሀገራችን ምናልባት ዛሬ አላስተዋልነው እንደኾነ እንጂ ለወደፊቱ ትልቅ አደጋን ጋርጦባታል። ይኸውም በትውልዱ ውስጥ በሴቶች(በእናቶች) ብቻ የሚያድጉ ልጆች እየበዙ መምጣት ሲኾን እርሱም ከፍተኛ የኾነ ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በግለሰብ፣ በማሕበረሰብም ኾነ በሀገር ደረጃ ማስከተሉ ነው። ዛሬም ቢኾን በጥቂቱም ለምሳሌ የሚኾኑ ሰዎችም ኾኑ ክስተቶች አይታጡም።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *