ትምሕርት ከጥበብ

ትምሕርት=Education
ጥበብ= intelligence ነው  ሳይኾን በዚኽ ዐውደ ንባብ እንደዚህ ለማለት ነው።

ሳተናው!

ካለፈው ሳምንት ጽሑፍ እንደመነሻ ፦ የሚስትህ የትምሕርት ደረጃ በተለምዶው አጠራር በዲፕሎማ፣ በዲግሪ፣ በማስትሬትም ኾነ በዶክትሬት መስፈርት መገኘቱ ምድራዊ ኑሮኣችሁን ብታቀሉበት ያንተንም የቤት አስተዳደር ብታግዝበት እንጂ አባወራነትህን የሚተካ(የሚሽር) መኾን የለበትም።

ይኽ ከላይ ያስቀመጥኩት አንቀጽ ካለፈው ሳምንት ልጥፍ የተወሰደ ነው። ከእርሱ በመነሳትም ዛሬ መደበኛው የትምሕርት ስርዓት ተፈጥሮኣዊው ሚናችንን እንወጣበት ዘንድ ከታደልነው ጥበብ(ጸጋ) ጋር ያላቸውን ዝምድና እንይ። መደበኛው የትምሕርት ስርዓት ተፈጥሮኣዊውን ሚናችንን እርሱንም ማስኬጃ የተሰጠንን ጥበብ ለማበልጸግ ያግዘናልና።

በትዳር ወስጥ ወንዱም ኾነ ሴቷ ለአንድ ዐላማ ቢሠሩም ቅሉ ሊወጡት ያላቸው ሚና ግን ለየቅል ነው። ዐላማችንን የምንወጣበት ሚና ሲለይልን ሚናችንን የምናውቅበትንም ጥበብ(ጸጋ)  ታድለን(አድሎን) ነው።

ይኽች ጥበብ ተፈጥሮኣዊና በውስጣችን ያለች ብትኾንም በትምሕርትና በስልጠና ልትዳብር ልትጎለብትም ትችላለች። በተቃራኒውም ደግሞ ልትደበዝዝ፣ ልትረሳና ልትከስምም ትችላለች።
ይኽችን ውስጣዊ ጥበብ ብናዳምጣት የችሎታችንን መጠን፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ገንዘብ ልናደርጋቸው በምንፈልጋቸው ክሕሎቶቻችንም ያሉብንን ውሱንነት ትጠቁመናለች፣ ትመራናለች።

የአባወራ ገጽ መፈክር “ተፈጥሮኣዊ እውነት ለስኬታማ ትዳር” መኾኑን አስተውል። ይኼንንም በዚኹ ገጻችን ላይ አስረግጠን ለማስረዳት ስንል ፈጣሪ የሰጠንን ሀብት፣ ጸጋ፣ ጥበብ በየክፍላቸው እንደየቦታቸው እና እንደየጊዜያቸው እያየን መጥተናል።

የዛሬ ችግሮቻችን(በተለይ የትዳሩ) ቀድሞውኑ በተፈጥሮ የተሰጠንን ጸጋ ካለማወቅ፣ ካለመረዳት፣ አውቀን ከመናቅም የመጡ ናቸው። ለቤት ከመሠረት ጀምረው ወደ ውሃልክ እንዲሄዱ፤ እኛም መሠረታዊ ከኾነው ከተፈጥሮኣችን ጸጋ ጥበብ ተነስተን፣ ወደ ውሃ ልኩ ሚና፣ ወደ ድምድማቱ ዓላማ እንዘረጋለን።

መደበኛው ትምሕርት ቤት ገብተን የምንቀስመው ውስጣችን የተቀመጠውን ተፈጥሮኣዊ ጥበብ እንዲያድግ፣ እንዲወጣና እንዲፈጸም አብዝተንም እንድናተርፍበት የሚያግዘን መኾን አለበት።

ይኹንና ብዙዎች ካለማወቅ አንድ ሰው ከትምሕርት ቤት ገብቶ ብዙ ዐይነት ትምሕርት ስለቀሰመ ጠቢብ ነው ብለው ያስባሉ። ኾኖም ግን ይኽ በተማረበት ትምሕርት የደረሰበትን ደረጃ ቢያሳይ እንጂ ጠቢብ ስለመኾኑ ዋስትና አይኾንም። ሰዎች በሕይወታቸው ጠቢብ ኾነው በትምሕርት ቤት የሚሰጠውን መደበኛ ትምሕርት ግን ያልተከታተሉ ሊኾኑ ይችላሉ (እንደ ቀደሙት እናትና አባቶቻችን)። በተቃራኒው ደግሞ በመደበኛው ትምሕርት እስከ ዶክትሬቱ ደርሰው ተፈጥሮኣዊውን ጸጋ ንቀው አማናዊው(እውነተኛው) ጥበብ የራቃቸው ኑሮን በስሌት ብቻ ለመኖር የሚሞክሩ ይኾናሉ(ራሳችንን ማየት እንችላለን)።

ትዳር ተቋም ነው፤ እርሱንም አቅዶ፣ ተጣማሪዎቹን በቁጥር እና በጾታ ወስኖ ለአንድ ዓላማ አጽንቶ፣ ሚናን ለይቶ፣ ሚናችንን በጥበብ ሞልቶ የሰጠንን ፈጣሪ ስናስብ መሥራቹ እርሱ ነው እንላለን። 

አንድም ከነበሩበት የብቸኝነት ሕይወት ወጥተው፣ በአንድ ጣሪያ ሥር አርፈው፣ ከአንድ ማዕድ ቆርሰው፣ አንዲት ንጹሕ ምንጣፍ ላይ ፈቃዳቸውን ፈጽመው ዐዲሱን ሕይወት ሲጀምሩ ስናይ መሠረቱ ቢባል ከቀደመው ቢስማማ እንጂ አይጣላም።

“ፈጣሪያችን በትዳር ውስጥ ለዓላማ አንድ አደረገን” ብንል ይኽን ዓላማ ዳር እንድናደርስበት የሰጠን ሚና ግን ለየቅል ነው። ይኽንኑ ሚና የምንመግብበት ጥበብ(ጸጋ) ደግሞ ይለያያል። 

እኔ ወንድ ነኝ። በትዳሬ ውስጥ የአባወራውን ሚና ስይዝ ይኼን ሚና ተጠቅሜ የጋራ ዓላማችንን ለማሳካት ይረዳኝ ዘንድ የተሰጠኝ የታጠቅኩት ጥበብ አለ፤ ለሚስቴም እንዲሁ ነው።

ይኼ ጥበብ ተፈጥሮኣዊና ውስጣዊ ነው። ይኽም ማለት እኔ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ መምህር፣ ወታደር፣ ዶክተር፣ ሚንስትር ብኾን እንኳ በውጫዊ ትምሕርት ባሳድገው አልያም ባደበዝዘው እንጂ ይኽን ጥበብ አልፈጠርኩትምና አላጠፋውምም ሊዛነፍብኝም አይገባም።

ለሚስቴም እንዲሁ የተሰጣት ጥበብ/ጸጋ ተፈጥሮኣዊ ውስጣዊም ነው። የቤት እመቤት፣ መምሕር፣ ነጋዴ ባለማስትሬትም ኾነ ባለዶክትሬት ሌላም ብትኾን የደረሰችበትን የትምህርት ደረጃዋን ቢያሳይ እንጂ ተፈጥሮኣዊ ጸጋዋን/ጥበቧን ሊያዛንፈው አይገባም። 

ይኽም ማለት የታደልነው ጥበብ ተፈጥሮኣዊ(ውስጣዊ) ነው ስል በገባንበት ትዳር ውስጥ ለያዝነው ዓላማ መሳካት የበኩላችንን ድርሻ የምንወጣበትን ሚና የሚነልጽ፣ የሚያሳውቅ እናም የሚያስታጥቅ ነው።

ምንም ዓይነት የመደበኛ ትምሕርት ብንማር ቢቻል ይኽን ተፈጥሮኣዊ ጥበብ የሚያበለጽግልን ቢኾን እንጂ ሊያኮስስ፣ ሊያጠለሽ እና ሊያናንቅብን አይገባም አልያ ግን ተጽዕኖ እንዲደረግበት መፍቀድ የለብንም።

፨ ያንተም ኾነ የሚስትህ ዘመናዊ ትምሕርት መማርም ኾነ አለመማር የእርሷን ትሕትናና ታዛዥነት ከማየት፣ ከማመስገን የሚጋርድህ አልያም እንድትንቃት የሚጋብዝህ መኾን የለበትም።

፨ ያንተም ኾነ የሚስትህ ዘመናዊ ትምሕርት መማርም ኾነ አለመማር አንተን ከአባወራነትህ ሚና የሚለይህ፣ እርሷንም “ምሪኝ፣ እታዘዝሻለሁ” እያሰኘ የሚያስከትልህ ሊኾን አይገባም።

፨ ያንተም ኾነ የሚስትህ ዘመናዊ ትምሕርት መማርም ኾነ አለመማር እርሷን ባንተ ላይ ራስ፣ አዛዥ የሚያደርጋት አልያም ትንቅህ ዘንድ ምክንያት የሚኾናት መኾን የለበትም።

፨ ያንተም ኾነ የሚስትህ ዘመናዊ ትምሕርት መማርም ኾነ አለመማር ያንተን ራስነት፣ አዛዥነት እንዳታመሰግን፣ እንዳትቀበልም የሚጋርዳት መኾን የለበትም።

፨ ያንተም ኾነ የሚስትህ ዘመናዊ ትምሕርት መማርም ኾነ አለመማር ላንተ በትሕትናና በታዛዥነት እንዳትሰጥህ የሚከለክላት መኾን የለበትም።

ይኽ ሳይኾን ቀርቶ አንተ የተሰጠህን ስልጣን አለኣግባብ ተጠቅመህ ብታስጨንቃት ጥፋተኛ ሲያደርግህ፤ በሌላ በኩል ስልጣንህን በፈቃደኝነት አሳልፈህ ብትሰጥ ደግሞ እማወራ ኾና ከድጡ ወደማጡ መኼዳችሁ እማይቀር ነው። 

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *