ትዳር ይቅርብህ፦ አታግባም! ፫

ሳተናው!

በቀደሙት ሁለት ጦማሮች የጀመርኩትን “አታግባ” ምክሬን ዛሬ ልቋጨው።

ትዳርህ ውስጥ ከሚገጥሙ ፈተናዎች የተነሳ ፍቺን እንደ አማራጭ አስበህ አትግባ ማለቴን ታስታውሳለህ። አዎን! አንተ ትዳርን ስታፈርስ ፈራሹ በተለይ ቤተሰብህ ቢኾንም ትውልድና ሀገርም ግን ተመሳሳይ ዕጣ ይገጥማቸዋል።

እንዲሁም ደግሞ በቀጠለው ጦማር ምንም እንኳ “ትዳሬን አላፈርስም” ብትልም “እፈታሃለሁ” ብላ በምትፎክር ሚስትህ ፊት ግን ፍቺን ፈርተህ ፈጣሪ የጣለብህን ኃላፊነት፣ የሰጠህንም ሚና ጸጋህንም ጭምር ከመለማመድ ወደኋላ እንዳትል አስጠንቅቄሃለሁ።

ቤተሰብ ትንሿ ሀገር ናት፤ ልጆችህ ደግሞ የትውልዱ አካል፤ ስለዚህም አንተ ወደ ትዳር ስትገባ የምታያቸውንና የምትጨበጣቸውን ቤተሰብና ልጆች ብቻ አስበህ ሳይኾን የትውልድን ነገር፣ የሀገርንም ዕጣ ፈንታ እና በጠቅላላውም ስለሰው ዘር አስበህ ግባ።

አንተ በግልህ የምትወስናት ይህቺ የትዳር ውሳኔ የሰው ልጅ(ትውልዱ) ከራሱ ፣ ከተፈጥሮ እና ከፈጣሪም ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ያላት ተጽዕኖ ከፍተኛ ነውና።

ወንድምዓለም!

አሁን እንግዲህ ከማግባትህ በፊት ዐራት ነገሮችን በደንብ እንድታስብባቸው ልጠቁምህ፦

፩ኛ ትዳርን አንድ ጊዜ ልትፈጽመው እንዳለህ እንጂ በየሕይወት መንገድህ ላይ እንደምትፈታው እና እንደምታስረው የወገብህ ቀበቶ አልያም የጫማህም ክር አለመኾኑን

፪ኛ ለማግባት ከመወሰንህ በፊት በትዳር ውስጥ የራስክን፣ የሴቶችን እናም የፈጣሪን ፈቃድ፣ ሚና እና ጠባይም እንድትረዳ፤ ምክንያቱም በምትመሠርተው ትዳር ውስጥ አንደኛ ደረጃ ባለድርሻ ናቸውና።

፫ኛ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ የተረዳኸውን እውነት ለመኖር ቁርጥ ፈቃድ፣ ውሳኔ እና ልምምድም ይኑርህ።

፬ኛ የሴት ምርጫህ ከሰሜታዊነት ወጥቶ በተራ ቁጥር ፪ ላይ በምታገኘው ተፈጥሮኣዊ እውቀትና ሐቅ ላይ የተመሠረተ ይኹን።

እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ዐራት ነጥቦች አውቀህ ለመኖር ምን ያክል እንደምትፈተን መረዳት አያዳግትህም። እኔም “ይበልህ ተፈተን ተጨነቅ ካለማወቅ የተነሳ፣ አልያም ትዳርን አቅልለኸው ገብተህ ከምታየው ፍዳ የተነሳ ይኼ ኢምንት ነው” እልሃለሁ።

ሳተናው!

ብልጭልጯንና አፈ-ቅቤዋን ዓለም ተከትለህ ከምክንያታዊነት እርቀህ በስሜት አትንጎድ። ዓለም በ”እኩልነት”፣ በ”ነጻነት” ፣ በ”ፍቅር” እና በ”ጥበብ” ሰበብ አድርጋ የሰው ወንዱን ስነልቦና ማኮላሸት ከጀመረች ቆይታለች፤ ተሳክቶላታልም።

በዚህም ላባቶቹ፣ ላያቶቹ ክብር የሌለው እንኳን የድካማቸውን ፍሬ ሊጠብቅ፣ ባስረከቡትም ሊዘክራቸው ይቅርና መፈጠራቸውን የሚክድ ሆድ አደር፣ መረን፣ ምግባር የለሽ የኾነ መልኩን አሳምሮ ወሬን የሚያጣፍጥ፣ ፈሪንም ትውልድ አፍርታለች።

ስለዚህም በዚህ በሦስተኛው ጦማሬም አሳስብሃለሁ።

?እባክህ ግዴታህን ዘንግተህ በትንሽ በትልቁም ገንፍለህ ኃላፊነትህን መወጣት የማትችል በዚህም ትዳርህን የምታፈርስ ከኾነ ትዳሩ ይቆይህ አታግባ!

?እባክህን! “ሚስት የምትኾነኝ ሴት ኃይለኛ እና የውሳኔ ሰው ከኾነች እኔ እሺ ብዬ፣ አጎንብሼ፣ ታዝዤ፣ ስለልጆቼ እና ስለትዳሬ ስል እኖራለሁ” የምትልም ከኾነ ትዳሩ ይቆይህ አታግባ!

ሳተናው!

ትዳር ዓላማው ገብቷቸው በዚህም ኃላፊነታቸውን አውቀው፣ ሚናቸውን ለይተው፣ በጸጋቸውም ተጠቅመው ለሚጠቅሙበት ደፋርና ጠንካሮች እንጂ ለሰነፍና ፈሪዎች አይደለም!……. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *