ትዳር ይቅርብህ፦ አታግባ ፪

ሚስቴ ብትፈታኝስ ብለህ ተሰቅቀህ ፈጣሪ የሰጠህን ግዴታ(የወሲብ፣ የማስተዳደርና፣ የሚያስፈልገውን የማቅረብ) ግዴታህን ከመወጣት ቸል ብትል፣ ብትተወውም ትዳር ለፈሪዎች አይደለምና ይቆይህ፦ አታግባ!

ሳተናው!

ከዚህ ቀደም ፍቺ የማን መገለጫ እንደኾነ ተጫውተናል፦ አንተ የትዳርህ መሪው፣ የሚስትህ ራስ፣ የቤትህም አስተዳዳሪ ኾነህ ሳለ በቤትህ ለሚኾነው የስርዓት መጥፋት የምግባርም መጓደል የሚጠይቀውን ዋጋ ሁሉ ከፍለህ ታቀናዋለህ እንጂ ልትሸሽ ትዳርህንም ልታፈርስ እንዳይገባህም ጭምር።

ማፍረስማ ሙያ ከኾነ ምን በሹመት፣ አልያም በበላይነት ማስተዳደር አስፈለገህ። ይኽን ስልህ ግን ፍቺን ፈርተህ ተሳቀህም እንድትኖር አይደለም፤ በጭራሽ!

በትዳርህ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ሲኖሩ ከእነዚህ ፈተናዎች አንዱ አልያም በሌሎች ፈተናዎች መንስዔነት ከሌሎች ጋር ተደርቦ የሚመጣው ትልቁ ፈተና የሚስትህ ፍቺን ፍለጋ፣ የ”እፈታሃለሁ” ፉከራ ነው።

የሴትን ልጅ ተፈጥሮ በጠቅላላው የሚስትህን ደግሞ በተለይ ስትረዳ የምታገኘው ነገር ሴት ልጅ ስሜታዊ እንደኾነች ነው። የያዘችው አቋም፣ የገባችበት ውል፣ የተቀበለችው ኪዳን “ጸንቶ”(ከጸናም) የሚኖረው በዚሁ በሚዋዥቀው ስሜቷ ላይ ነው። ለዚህም ነው አንተ የትዳሩ መሪ የእርሷም ራስ መደረግህ።

ሳተናው!
በዚህ የፈተና ወቅት አንተ “እንዲህ ስል፣ ብል፣ ብዬ፣ ባደርግ፣ ብኾን፣ ብወስን፣ ብመርጥ፣ ባይ፣ ብሰማ…. ሚስቴ ከምትፈታኝ” አልያም “እፈታሃለሁ ከምትለኝ” እያልክ በሰቀቀን፣ በስጋት የምትኖር ከኾነ ወይም የምትኖር ከመሰለህ፤ አሁንም ትዳር ላንተ አይኾንም ይቅርብህ አታግባ!

ኃላፊነትህን ላለመወጣት ወይም ደግሞ ከሴሰኛነትህ የተነሳ በትዳር ታጥረህ መቀመጥ ካልቻልክ እዚህ ቃልኪዳን ውስጥ አትግባ እንዳልኩህ ሁሉ አሁንም ፈጣሪክ ካንተ የሚጠብቀውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚስትህን ፊት የምታይ የምድራዊ መንግስትም ይኹንታን የምትጠብቅ ከኾነ ትዳር ይቅርብህ፦ አታግባ!

ሳተናው!
ትዳርን ያክል ታላቅና ሚስጥራዊ ተቋም እግዚአብሄር ሲሰጥህ ተራ የስጋ ፈቃድክን ብቻ የምትፈጽምበትም አይምሰልህ። ይልቁንስ የነገን ትውልድ የምትሠራበት ካባቶችህ በቅብብሎሽ የመጣን ሥርዓት የምታስቀጥልበትም፣ ፈጣሪ ለሰው ልጅ ያለውንም ዓላማ በታዛዥነት የምትፈጽምበት እንጂ።

ለትዳርህ የሚያስፈልገውን ወጥተህ ወርደህ የማምጣት፣ ቤተሰብህንም ከክፉ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለብህ ሁሉ ልጆችህን በሥነ-ስርዓትና በግብረገብ ማሳደግም ይጠበቅብሃል። በንጹሑ ምንጣፍህ ላይ የምትፈጽመው ወሲብማ ሚናው በውጪ ከምትደክመው፣ በቤትህ ከምታስጠብቀው ስርዓት ቢብስ እንጂ አያንስም።

እነዚህ ግዴታዎችህን የመፈጸም ኃላፊነት ሲኖርብህ ነገር ግን ከ”እኩልነት” ተነስተህ፣ ሚስትህንም ፈርተህ ኃላፊነትህን የምትሸሽ አልያም ፈጣሪ ባወቀ ያልሰጣትን ስልጣን ባንተም ኾነ በቤትህ ላይ የምትሰጣት ከኾነ አሁንም ትዳር ላንተ አይኾንምና አታግባ!

ሳተናው!
ትዳር ለፈሪ አይኾንም! እደግመዋለሁ ትዳር ለፈሪ አ…ይ…ኾ…ን…ም!
ቤትህን ምራ ስትባል የሚስትህን ይኹንታ፤ ወሲባዊ ፈቃዷን ከዳር አድርስላት ስትባል በጠረጴዛ ዙሪያ ስብሰባ የምትጠራ ከኾነ ግዴታህ ያልገባህ፣ ኃላፊነትህን የዘነጋህ፣ ጸጋህንም ያላወቅህ ምስኪን ነህና ትንሽ ቆይ አታግባ!

የሴትን ይኹንታ፦ ሴታውል ይፈልገዋል ምክንያቱም እርሱ ራስ ወዳድና ከወቅታዊ የወሲብ ፍላጎቱ ውጪ ምንም ርዕይ የለውምና ነው፤ ፦ ምስኪን ግን ከትቢያ አንስቶ ሰው ካደረገው ፈጣሪ የበለጠ “አስተዋይ” እና “ዲሞክራት”(አንዳንዶች ነን እንደሚሉት) የኾነ ይመስለዋል። ቁም ነገሩ ግን ሁለቱም የትዳር ዓላማውና ግዴታቸውም ያልገባቸው ሲኾኑ ትዳራቸው ከ”ፍቺ” ቢተርፍም መረን እና ስሜታዊ ትውልድም ያፈራሉ።

አንተ ሥነ-ስርዓት ይዘህ ሚስትህንና ልጆችህን እንዲሁ መምራት የማትችል አልያም ፈሪ ከኾንክ ትዳር ይቆይህ፦ አታግባም!
ከፈጣሪህ ቃል ይልቅ የሴት “ፍቅር” ፈሪ ካደረገህ፤ ትዳር ይቆይህ አታግባ!
ለሆድህ እና ለፍትወት ተሸንፈህ ከኃላፊነትህ ከራቅክ ትዳር ይቆይህ አታግባ!
ከፈጣሪ በላይ “ስልጡን” “ዲሞክራትም” ነኝ ካልክ “ትዳር ይቆይህ አታግባም!

አስተውል ግን!
……እስከዚያው ከማንም ተንጠላጠል አላልኩህም ..ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *