ትዳር ይቅርብህ፦ አታግባ!

ሳተናው!
ለትዳርህ ፈተና ፍቺን እንደመፍትሄ የምታስቀምጥ ከኾነ ይቅርብህ አታግባ!

ፍቺ ስንፍና ነው! ለትዳር የምትኾንህን ሴት በአግባቡ ያለመምረጥ አልያም የመረጥካትን መክረህና ገስጸህ መምራት ያለመቻል ስንፍና እና ደካማነት ነው።

ሳተናው! ደግሜ እነግርሃለሁ
ፍቺ ቃላባይነት ነው! በእግዚኣብሄር ፊት፣ በሰው ምስክር ፊት፣ በሰማይና በምድር ፊት እጠብቀዋለሁ ያልከውን ቃል ማጠፍ ነው።

ሳተናው!
ፍቺ የዝንጉ ማንነት ነው! ትዳርን፣ በእርሱም ያለን ዓላማ፣ ጸጋውንና ክብሩን ያልገባው አልያም የዘነጋ፤ ቸኩሎ፦ሰዎች አግብተው ሲወልዱ አይቶ፤ አርፍዶ፦ ጊዜዬ አመለጠኝ ብሎ የገባበት የእርሱ ነው።

ሳተናው! ግድ የለህም ልጨምርልህ፦
ፍቺ የፈሪ መለያ ምልክቱ ነው! ትዳርን ያክል ታላቅ ተቋም ባርኮና ቀድሶ፤ ከሰጠው ከፈጣሪው ይልቅ የዓለምን ማስፈራሪያ ሰምቶ ኃላፊነቱን ከመለማመድ፣ ጸጋውን ከመጠቀም በሚናው ከማትረፍ ይልቅ ሽሽትን የሚመርጥ የፈሪ ነው፤ ከተጠያቂነት ግን አይድንም።

ሳተናው!
ፍቺን እንደ አማራጭ ይዘህ ትዳር ውስጥ ለመግባት የምታስብ ከኾነ፤ በትዳር ውስጥም ለሚገጥሙህ ፈተናዎች መጀመሪያ የሚመጣልህ መፍትሔ ፍቺ ከኾነ ትዳር ይቅርብህ፤ አንተ ዝግጁ አይደለህምና፤ አታግባም!

በእርግጥ ዘመንኛዋ ዓለም ሚስትህን የመምራት፣ የመምከርና የመገሰጽ ስልጣንህን ኋላቀርነት፣ አለመሰልጠን እና አምባገነንነት ብላ ትገፍሃለች። አንተም ይህን ይዘህ የተጣመመውን ከማቅናት የተሳተውን ከማረም እና በእርሱም ያለን መስዋዕትነት ከመቀበል ይልቅ ዘለህ ፍቺ ላይ ፊጥ የምትል ከኾነ ትዳር ይቅርብህ፦ አታግባም

ትዳር ለእንዳንተ ዓይነት በትንሽ በትልቁ ለሚበረግጉ፣ ሚስቱም ኾነች ኑሮው ጓ ባሉ ቁጥር እፈታሻለሁ፣ እፈታታለሁ እያሉ የፈሪ ቀረርቶ ያልጫም ሽለላ ለሚያሰሙ ለሚርበደበዱትም አይደለም።

ትዳርን በኃላፊነት እንድትመራው ስትታዘዝ፣ የቤትህም ራስነት ሲነገርህ ይኽንኑ የምትወጣበት ሚና ጸንቶልህ፣ ጸጋውም ተሰጥቶህ እጂ በባዶ አይደለም። ይኽን ኃላፊነትህን ሳትረዳ፣ ሚናህን ሳትለይ፣ ጸጋህንም ሳታውቀው ግልብ በኾነ ስጋዊ ስሜት እንዳው በ”እወድሻለሁ ካላንቺ አልኖርም” እንጉርጉሮ ተወስውሰህ ልታገባ ከኾነ ባታስበው ይሻልሃል፤ ይቅርብህ።

ምክንያቱም ትዳር ያየኸውን የሕንድ አልያም የሆሊውድ ፊልም ወይም ደግሞ ስትሰማ የኖርካቸውን “የፍቅር ዘፈኖች” እውን የምታደርግበት መድረክ ሳይኾን እግዚአብሄር ለሰው ልጅ ያለውን ዓላማ ተረድተህ እርሱንም ዳር የምታደርስት፤ በፈተና የሚጠነክር በጽናትም እስከ ሞት የሚቆይ ተቋም እንጂ።

ሳተናው!
በትዳርህ ውስጥ ሁሌ ደስታ የለም። ሁሌ ደስታ ስለማይኖርም ደስታን እንደ አንድ ግብ ይዘህ ትዳር ውስጥ አትገባም። ይልቁንስ ልጆችን ወልዶ፣ ቤተሰብን መሥርቶ፣ ሥነ-ስርዓትና ሥነ-ምግባር ያለው ጤናማ ትውልድ ለሀገርና ለዓለም ማትረፍ እንጂ። ወደዚህ ዓለም የሚመጡት ልጆችህ ያንተ የስንፍና ውሳኔህ ሰለባ መኾን የለባቸውም፤ አይገባቸውምም።

ሚስትህ በተፈጥሮዋ ቆዳዋ ስስ፣ ስሜቷም ቅርብ ነው። እርሷ ስትከፋ፣ “ደስታም” ስታጣ ለምን እዚህ ውስጥ ገባሁ ማለቷ አይደንቅም፤ ፍቺንም ተደጋግሞ ከአፏ ቢሰማ አያስገርምም፤ ያንተ ከእርሷ ብሶ ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ ለፍቺ መንደርደር እንጂ። ስለዚህም ረጋ በል ለፍቺ ለምትቸኩለው ለእንዳንተ ዓይነቱ አይደለምና ትዳርን አቆየው፦ አታግባ።

ቃልኪዳንህን መጠበቅ፣ በፈተና ውስጥ ጸንተህ ለማለፍ፣ በኃላፊነት ለምትመራው ለእግዚአብሄር ተቋም መስዋዕትነት መክፈል የማትችል መስሎ ከተሰማ ትዳር ይቆይ፤ አታግባ።

ቅዱሱን ኪዳን አታርክስ፣ ባንተ ሊመሰገን የሚገባውን ሰጪ አታስመርር፣ ቤተሰብህን አትበትን፣ ትውልድንም አትግደል፣ ሀገርንም አትበድል።…….

ነገር ግን ፍቺን አትፍራ! ምን?………ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *