ኃላፊነትን የምትወስድ አንተ በምንጣፍህ ንጉስ ነህ

ሳተናው!
በአደባባይ የተለማመድከው፣ በእልፍኝህም የደገምከው ኃላፊነትህ በመኝታ ቤትህ ጎልቶ ይታያል።ይኽም ማለት ባንተ እና በሚስትህ ለሚፈጸመው ተራክቦ ኃላፊው፣ መሪው፣ ተጠያቂው፣ ተሸላሚው፣ ተወቃሹም አንተ ነህ።

የትኛውም በቡድን፣ በጋራ የሚሠራ ድርጊት ሁለት ዋነኛ ተዋናዮች አሉት። እነርሱም በድረጊቱ የሚሳተፉ አባላትና ድርጊቱን በበላይነት የሚመራ፣ ተፈጻሚነቱንም የሚከታተል፣ ደረጃውንም የሚጠብቅ ከተሳታፊዎቹ በተሻለ ከስሜታዊ ይልቅ ምክንያታዊ የኾነ ግለሰብ።

አንድ ነገር አስተውል! አንተ ንጉስ ነህ። ንግስናህም በተለይ የራስህን ስሜት ከመግዛትና ከማስተዳደር ይጀምራል። በመኝታ ቤትህ ምንጣፍ ላይ በጭራሽ ችኩል፣ ጉጉ(የሚጓጓ) እና ስግብግብ አትኹን።ስሜትህን ተቆጣጠር፤ ድርጊቶችህ ኹሉ በእርጋታና በአስተውሎት ኾን ብለህም በእቅድ ይኹኑ።

ምንም አድርግ ምን ሳታስበው፣ ድንገት ተደስተህም ኾነ ተናደህ ከማድረግ ተቆጠብ። ይኽ ከፍተኛ ልዕልና፣ራስንም የመግዛት ልምምድ ነው። አንተ ራስህን እንዲህ የምትገዛ ወሲብንም እንደ እህል ውሃ ካላገኘህ የምትሞት ይመስል ጉጉ እስካልኾንክ ድረስ በራስህ ፍላጎቶች ላይ የነገስክ ንጉስ ነህ።

ሲቀጥል ሚስትህን የሚዋጋትን(የሚያሰኛትን) የወሲብ ፍላጎት ተረድተህና ገጥመህ እርፍ ታደርጋታለህና ንጉስ ነህ። ልብ አድርግ! የቀደመውን “ራስን መግዛት” ካላወቅክበት የኋለኛው (ሚስትህን ማስተዳደሩ)በጭራሽ አይቻልህም።

ነገር ግን ራስህን መግዛት ተለማመደህ ከመጣህና የእርሷን ስሜት አውቀህ መምራት ከጀመርክ፤ ልንገርህ አይደል እንዳንተ ጌታ፣ እንዳንተም ንጉስ የለም።

ፈጣሪ በአንተ እና በእርሷ መካከል ለሚፈጠረው ተራክቦ ስኬት አስፈላጊውን ኹሉ በእርሷ ውስጥ አድርጎ መሪውንና ቁልፉን ግን አንተ ጋር ያደረገው በምክንያት ነው።

ይኼውልህ ሳተናው!
ሴትን ልጅ እንደ አንድ ዘመንኛ ምርጥ መኪና() አስባት መኪናዋን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን ሾርም ትል ዘንድ የምትጠይቀውን ጉልበት አምራቾቹ ከውስጧ አስቀምጠዋል።

ነገር ግን መኪናዋ የምትነዳበትን መንገድ፣ ፍጥነትና ቆይታ የሚወስነው ሹፌሩ እርሷን የሚለኩስበትም ቁልፍ በእጁ ነው። እርሱ ራሱን የጠበቀ፣ የገዛ፣ የተረጋጋና የሚሠራውንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው። እርሷም ታምና ትታዘዘዋለች፤ እርሱ ሲያዛት እርሷም የታዘዘችውን ያክል ትመልስለታለች። ልብ አድርግ! የሰጠሃትን ያክል ብቻ መልሳ ትሰጥሃለች።

ይኽ ኃላፊነት የሚሰማው ሹፌር እርሷን የሚነዳበትን መንገድ፣ ፍጥነትና ቆይታዋን ወስኖ ይነዳታል። መንገድ አልኩ አጉል መንገድ ገብታ እንዳትጎዳበት ገደልና ድንጋይ እያየ እየመረጠ ይነዳታልና። ፍጥነት አልኩ እርሱ ሊቆጣጠራት ከሚችለው ፍጥነት በላይ በራ ትገለበጥና ራሷንም ኾነ እርሱን ተሳፋሪ ልጆቹንም(ቤተሰቡን) እንዳትጎዳ ይጠብቃታልና። ቆይታ አልኩ ምንም እንኳ በእርሱ እጅ ሾር ማለት ብትወድም ብዙ ከመነዳት ራሷን እንዳትጎዳ ቆይታዋን ወስኖ ያሳርፋታልና ነው።

ይኽ ኹሉ ሲኾን ታዲያ ለሚደርስበትም ኾነ ለሚያደርሰው ስኬትም ኾነ አደጋ ተጠያቂው እርሱ ቢኾን እንጂ መኪናዋ አትኾንም።

ሳተናው!
ባንተ እና በውዷ ሚስትህም እንዲሁ ነው። በምንጣፋችሁ ላይ በተራክቦኣችሁ ወቅት የምታሳይህ ጠባይ አንተ ለሰጠሃት ግብረ መልስ ነውና ኃላፊነቱን ውሰድ። ብዙውን ግዜ ክቡር በኾነው ትዳር ንጹሕ በኾነውም ምንጣፍ ሴቶች “ጨዋነት የተምላ” ተራክቦን (በጎን ሻጥ የምንላትን) እንጂ የተፈጥሮኣቸውን ጥያቄ መመለስ የሚችል ፍልሚያን ማጣጣም እንደሚፈልጉ አንረዳም ቢገባንም አንደፍርም።

እርሷ ደግሞ እዛ ድረስ በነፃነት ለመኾን ለድርጊቶቹ ኃላፊነት የሚወስድ፣ የሚሠራውን የሚያውቅ፣ የማያስፈቅድ ደፋር ወንድ ትፈልጋለች(አልያ ግን እምቢተኛ ነች)። ነገር ግን (ይኼን አስምርበት)በጭራሽ፣ በጭራሽ፣ በጭራሽ መንስዔ መኾንን እና ኃላፊነት መውስድን አትሻም። ይኼን ብታደርግማ ወንድሜ መንስዔ መኾኗ ከታዛዥነቷ፤ ኃላፊነት መውሰዷ ከትኅትናዋ ጋር ይጋጫሉ። ተራክቦን አንተ ስትቀሰቅስ፣ ስትጀምርና ስትመራ ብቻ ሚስትህ እንደሠራት እንደፈጠራትም ትኾናለች።

ስለዚህም ደግሜ ደጋግሜ ኃላፊነት እንድትወስድ እመክርሃለሁ። የኾነውና የሚኾነው ኹሉ አንተ ስላልክና ስላደረግከው ሲኾን የሚሳበበውም ባንተ ነው፣ ይኾናል፣ ይኹንም።

ሳተናው ንሳ! ኃላፊነት ውሰድ
ሚስትህ ለተራክቦኣችሁ የምትወስደው ኃላፊነት ኢምንት በኾነና ያንተ ደግሞ ባየለ ቁጥር ተፈጥሮዋን በሚገባ ማወቅ፣ ማድነቅ፣ መደሰት ከእርካታ ጥግም መድረስ ይቻላታል።

ሽሽሽ እነኾ ሚስጥር ሚስትህ ሁለት ማንነት አላት፦
አንዱ ማንም የሚያየው ተፈጥሮዋ ነው። እርሱም በተፈጥሮኣዊ ሴትነቷ፣ በባሕላዊ ጭምትነቷ፣ በሃይማኖታዊ ትኅትናዋ የታጠረው ጨዋና ጠንካራ ማንነቷ ነው። ለዚህም ራሷ ኃላፊነት ወስዳ ታሳድገዋለች ትጠብቀዋለች ትጠየቅበታለችም።

ሁለተኛው ግን ለማንም የማትነግረው ማግኘት፣ መኾንና ማጣጣም የምትሻው ኃላፊነት ግን የማትወስድበት የወሲብ ስሜቷ ነው። ለዚህ ደግሞ አንተ መምራትና መግራት ይጠበቅብሃል፤ ተቀባይ ናትና አንድም ኃላፊነቱን አትሻምና።

ባንተ መሪነት ፈጽማችሁት “እረሱ ነው….” ብላ ሸክሙን ላንተ ታደርጋለች። በእርግጥ ያደረገችውን ወዳው፣ ፈቅዳው በማድረጓ ደስተኛ ነች ነገር ግን አንተ ስላልካት አደረገችው እንጂ። አንተ ያልካትን ለማድረግ ቃልህንም ለመከተል ግ….ን የአባቷ ልጅ መኾን አለባት።

ሳምንት ጌታ ቢፈቅድና ብንኖር ላላገቡት ሴቶች እህቶቼ ሊመርጡት፣ ሊያስበልጡት፣ ሊያስቀድሙት የሚገባው ያባቱ ልጅ ማነው….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *