ኃላፊነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰበበኛነት

 

ኃላፊነቱን የማይወጣ ወንድ ሰበበኛ ነው። (በውስጥ መስመር መጥተህ “ሴትስ” አትበለኝ! እኔ እያወራሁ ያለሁት ላንተ ነው። ወሬውን ኹሉ ፆታ እየቀያየርኩ ሚዛን ሳደላድል አልገኝም) ኃላፊነትህን መወጣት ስትሰንፍ ሰበበኛነት ይሰለጥንብኃል።

ሰበበኛ ስትኾን ራስህን ላለመለወጥህ፣ ላለማደግህ፣ ቤትህን ማስተዳደር ላለመቻልህ ምክንያት ትደረድራለህ። ይኹን እንጂ ለራስህ ስንፍና፣ ለትዳርህ መናጋት፣ ለቤትህ መሰንጠቅ፣ ለልጆችህ ቅጥ ማጣት፣ ለትውልድ መረን መውጣት፣ ለኃይማኖትም ኾነ ለሀገር መሪ ማጣት ተጠያቂው አንተው ራስህ ነህ።(አንተ ውስጥ እኔም አለሁ)

በእርግጥ ዓለም አሳሳች የለባትም እያልኩህ አይደለም። አንተ ግን የመጣህበት ምክንያት የተፈጠርክበትም ዓላማ ቢገባህ ኖሮ እነርሱን እየተውክ ዳግምም ወደ ወጥመዳቸው እንዳትገባ እየተጠነቀቅህ፣ ካንተ መሰሎች ጋር እየተመጋገብህ ትጓዝ ነበር።

ወንድሜ ኑሮህን ከምታማርር፣ ሀገርህን ትውልድህንም ቆመህ ከምትወቅስ ይልቅ በችግርም ውስጥ ኾነህ ለተፈጠርክበት ዓላማ ኑር።

ሰበበኛነት ለጊዜው ራስህን ብትደልልበት እንጂ ለዘለቃው ከኅሊና ዳኝነት አይታደግህም።

በተሰጠህ ጸጋ በድለኃል? ፈጣሪህን አሳዝነሃል? ኃጢያትንም ሠርተሃል? እንግዲያውስ ንስሃ ግባ። “እገሌ ነው ያሳተኝ” “እገሌ ባይኖር አላደርገውም ነበር” አትበል። የሚያስብ አእምሮ፣ የሚያስተውልም ልብ ተሰጥቶሃል አመዛዝኖ ማድረግ በመዳፍህ ሥር ነበር።

የኾነውስ ኾነ ሰበብ አስባቡን ተወውና ንስሃ ግባ፤ ለድርጊትህ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነትን በመውሰድ ዐዲስ ጉዞ ጀምር። አንተ ንስሃ የገባህበትን ጉዳይ ሰዎች እያነሱ እንደመስቲካ ሲያላምጡት አትቆጭ ከሰይጣን ለከፉት ለእነርሱ ይብስባቸዋልና።

አንተ ግን በንስሃ የታደሰውን “አንተን” ይዘህ ለተፈጠርክበት ምክንያት ወደተፈጠርክበትም ዓላማ ተዘርጋ። ከትላንትናው ስህተትህም ተምረህ እለፍ።

ወንድሜ ለራስህ ሕይወት ኃላፊነቱን መውሰድ ተለማመድ። እናትህን፣ አባትህን፣ ወንድምህን፣ እህትህን የኃይማኖት መሪዎችን ቆመህ ስትከስ ብትኖር ሕይወትህ አትለወጥም።

እነዚህ ኹሉ አንተን ለማሳት መጥተው ይኾናል። መንገዳቸውን አለመከተል ግን ምርጫህ ነበር። ይኹን እንጂ በስንፍና፣ በሱስ ራስህን ዛሬ ላይ ብታገኘው ይኽ በራስህ ምርጫ ዛሬ ላይ የመጣ እንደኾነ አስተውል።

ወንድሜ ራስህን መቀየር ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከሰበበኛነት ውጣ፣ ጣትህንም ከሰው ላይ አንሳ፣ ራስህንም ወቅሰህ ለመለወጥ ቁረጥ፤ በውሳኔህም ጽና።

አንተን ለመለወጥ ካንተ ወዲያ ማንም አይመጣም። ስለራስህ፣ ስለአንደበትህም ኾነ ድርጊትህ ኃላፊነት ስትወስድ ሰበበኛነትህ ይቀራል ከተጠያቂነትም አትሸሽም።

ይኼን ማድረግ ይቻልህም ዘንድ ራስህን በእውቀት ገንባ። ኾድህን በእህል ኪስህን በገንዘብ ብቻ ከሚሞሉት ዓለማዊ እውቀቶች ይልቅ ራስህን የሚያሳውቁህን ከየት እንደመጣህ ወዴት እንደምትሄድ የሚያሳውቁህን ንባባት አዘውትር።

ያንጊዜ ራስህን ችለህ ታወራለህ። ለንግግርህም ኾነ ለድርጊትህ ኃላፊነት ትወስዳለህ፤ ለስንፍናህም ራስህን ትወቅሳለህ። ታርመህ ታድሰህም ዳግም ወደብርታት ትዘረጋለህ። በዚህም ሰበብ ካንተ ይርቃል የአባወራ ጉዞህም እንዲህ ይጀመራል።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *