“ነኝ”ን ተውና ኾነህ ተገኝ!

ሳተናው!
ዛሬ ዛሬ የምታየው ወንድ በአብዛኛው ስሜታዊ ነው። አብዛኞቻችን ያልኾንነውን እንዲህ “ነን”፣ “እንዲህ ነኝ” ብለን እናወራለን። እንዲህ የምንለው አንድም ከመኾን ማውራት ስለሚቀለን፣ አንድም ደግሞ በሰዎች ዘንድ (በተለይም በሴቶች ዘንድ) ተወዳጅነትን ለማትረፍ ነው።

? “አንባቢ ነን” ስንል መጽሓፍ እንይዛለን፣ ትንታኔ ማብራሪያም እንደሚያነብ ሰው እንሰጣለን፤ አንድ መጽሓፍ አንብበን የጨረስንበት ቀን ግን ትዝ አይለንም።

? “እስፖርተኛ ነን” እንላለን ስንሠራ አንታይም፣ ሰውነታችንም የስፖርተኛ አይደለም ነገር ግን ሰለእስፖርት ጥቅምና ስለእኛም እስፖርተኛነት ስናወራ እናስቀናለን።

? ብዙ ገንዘብ አልያም ትርፍ ሊያስገኝልን የሚችል ሕልም ርዕይ እንዳለን እናወራለን ይኹን እንጂ በብዙ ሰበቦች እና ምክንያቶች ተተብትበናል። ሕልማችንንም እውን ለማድረግ አንዲትም እርምጃ ያላነሳን ነን። የማንኖረው ርዕይ ያለን ሌሎችን ስለርዕይ የምናስተምር አቃቂርም የምናወጣላቸው ነን።

? “በፍቅር አምናለሁ” ብለን ፉከራ ብቻ፤ ኾነን መገኘት ግን የማንችል፤ ያለመቻላችንም ስንፍና የሚያሳብቅብን ራስወዳዶች ነን።

? “ስርዓት አለን” ብለን በሥነ-ስርዓት የማንኖር፣ በስርዓት ኑሩ ስንባል “ተጨቆንን” የምንል፤ እንዲህ ላለመኖርም “ፍቅርን” እና “እኩልነትን” ደጋግመን የምናነሳ።

? “በእኩልነት እናምናለን” ብለን ከፈጣሪ በላይ “ዲሞክራት” የኾንን፤ ልዩነቶቻችንን በአንድነት እና እኩልነት ስም የምንጨፈልቅ፤ እኩልነትና አንድነት የተምታታብን(በተለይ የጾታ)፤

? “ብዙ አውቃለሁ” ባዮች የራሳችንን ተፈጥሮ እንኳ በውል አውቀን ያልተገኘን ድኩማን፤

? “እውነትን እንሻለን” ብለን እርሷን ከማየትና ከመስማት የምንርቅ፣ ከእርሷም ይልቅ ቧልትና ስላቅ የማረኩን፣ እውነት ግን የምንታንገሸግሸን፤

? “መሪ መኾን የምንፈልግ” በማንንም ግን መመራት የማንሻ(በፈጣሪም ጭምር)፤ ይኹን እንጂ ያልገራነው ፈቃዳችን እንደፈለገ የሚነዳን፤

? “እውነተኛ ቃል አለን” የምንል በዚያ ቃል እንኳ ያልተገኘን፤ ምግባራችን ከቃላችን ያልተስማማልን፤

?? “የሀገር የወገን ፍቅር አለኝ” የምንል በተገኘው አጋጣሚ ግን “ተረኛ ነኝ” ብለን ሀገር የምንዘርፍ፣ ወገን የምስናስለቅስ፤

? “መንፈሳዊ ነን” ባዮች በስጋዊ(እንሰሳዊ) ጠባያችን ግን አይደለም ከቤት ከዱር እንሰሳት ያልተሻልን፤

በንግግራችን ሁሉ “ነን” የምንል፤ ነገር ግን ከኾንነው ይልቅ ያልኾንነው ሚዛን የደፋብን ነን።

ሳተናው!
አንተ ግን “ነኝ” ማለትን ከማብዛት ይልቅ ኾነህ ተገኝ። የወንድነት ልኩ፣ የጀግንነት ጥጉ፣ የአባወራነትም መለያው ወሬ ማጣፈጡ ሳይኾን ኾኖ መገኘቱ ነውና። አለበለዚያ ግን በሰበብ አስባቡ አቋምህን የምትቀያይር ሰዎች (በተለይም ሴቶች) መስማት የሚወዱትን ተናግረህ የማትኖረው፣ ያልኖርከውንም የምትናገረው ከኾነ እነርሱን ከመደለልና ከመተኛት ውጪ ቁም ነገር የሌለህ ሴታውል፤ አልያም ደግሞ ካለእነርሱ “አልኖርም” ባይ ምስኪን ትኾናለህ።

ሳተናው!
“እንዲህ ነኝ”፣ “እንዲያ ነኝ” ማለቱን ተውና መኾንን ተለማመድ። “ነኝ” ማለት በጣም ቀላል ሲኾን ኾኖ መገኘት ግን ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ይጠይቃልና።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *