አባት የለሽ ዘመን-> ስሜታዊ ትውልድ-> ቆዳ ስስ መሪ-> አስታዋሽ ያጣች ሀገር

ሳተናው!

የአባት ሚና የተመናመነበት ጭርሱንም የጠፋበት ዘመን ላይ ትውልዱ ስሜታዊ ይኾናል። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች በቀላሉ ኾድ ይብሳቸዋል፣ በራስ መተማመናቸው ይሸረሸራል፣ ደስታንም ለማግኘት ሲሉ ካለቦታው ብዙ ብር አውጥተው ይፈልጉታል ግን አያገኙትም። ለአባታቸው፣ ለእጁ ሥራ፣ ላወረሳቸውም ቅርስ ክብር የላቸውምና እነሱም ኾኑ ሥራቸው መቅኖ ቢስ ይኾናሉ። …

አባት ተፈጥሮኣዊ ግዴታውን ከማይወጣበት ዘመን ላይ ስሜታዊ ከኾነው ትውልድ ውስጥ የተገኘው መሪ ቆዳው ስስ ይኾናል። የሕዝቡ ችግር ቶሎ ይሰማዋል፣ ሲያለቅሱ ያለቅሳል አፉም አንጀት ያርሳል፤ ግን በቅጽበት ይዘነጋዋል። ሀገራዊ ጋጣወጦችን ያልፋል ቅን ሂሶችን ድባቅ ይመታል። በእርሱ ዘመን ቋጥኝ ጥፋት ያጠፉት በምሕረት ሲታለፉ ባይተዋር የኾኑትም በደላቸውን ይቸከሙላቸዋል።

ለልጆቿ መካሪ፣ ተዉ ባይ አልያም ቀጪ አባት ያጣች ሀገር በራሷ ልጆች እንድትጠፋ የተተወች አስታዋሽም ያጣች ሀገር መኾኗ ነው።

ሳተናው!
አንተ ግን ለነገ ትውልድ ብሩህ ተስፋ ሰንቅ፤ ታላቅ ሀገራዊም ርዕይም ስቀል። ግድ የለህም እመነኝ ሀገራዊ ርዕይ እንዲኖርህ መራሔ መንግስት መኾን አይጠበቅብህም። ራስህን በማነጽ ጀምረህ ሚስትህንና ልጆችህን ተፈጥሮኣዊ በኾነው ቀመር መርተህ፣ አባቶችህ ባስቀመጡልህን መርህ ጊዜውን ዋጅተህ ልጆችህን ብትቀርጽ ትውልድን አነጽክ ሀገርህንም ገንባህ ማለት ነው።

አባት የለሽ ዘመን ግን ይኽ ነው፦

 • በቤቱ ውስጥ የሚለማመጥ እንጂ ተው ብሎ የሚገስጽ ቀጥቶም ስነስርዓት የሚያሲዝ አባት ብርቅ የኾነበት፤
 • የሥራ ትጋት፣ የማንነት እውቀት፣ የሰውነት ልክ፣ የሰብዓዊነት ዋጋ፣ የሀገር ፍቅር የጠፋበት
 • መካር ሽማግሌ አስተዋይ የኃይማኖት መሪ የማይገኝበት
 • የሰው ዋጋው የሚቀልበት፣ በነፃነት ስም የሴቶች ክብር የሚረክስበት፣ በእኩልነትም ስምም ተፈጥርኣዊ ግዴታችንን የምንስትበት
 • የስነምግባርና የሞራል ዝቅጠት የሚገንበት፣ ትውልድ ርዕይ አልባ መረን የሚኾንበት…. አባት የለሽ ዘመን ነው። ከዚህም ዘመን ስሜታዊ ትውልድ ይገኛል።

ስሜታዊ ትውልድ፦

 • ወደነፈሰበት የሚያዘነብል፣ ነፋስ ስሜቱን የሚከተል፣ እርሱንም መግዛት የማይችል፤
 • መጽሐፍትን መርምሮ እውነትን ከመለየት ቢመር ቢጣፍጥም እርሱን ከመቀበል ይልቅ በፌስቡክና መሰል የመንደር ልጥፍጣፊዎችና ወሬዎች “አውቃለሁ” የሚል
 • በሕይወት ልምድም ኾነ በንባብ እውቀት ከአባቱ ሳይሻል በተነሳው ርዕስ ኹሉ አባቱን(መምሕሩን) ዕውቀት “ከኔ ወዲያ ላሳር” ሲል ለመካሪም የማይመች
 • ሐዘኑም ከመድረሱ፣ ደስታውም ከመፈጸሙ፣ ንዴቱም ከመቀጣጠሉ በፊት ይኸው ስሜቱ የሚቆጣጠረው
 • ማጅራቱን መትተው እርቃኑን ያስቀሩትን አይቶ እንዳላየ አልፎ ከደረት ኪሱ ሶፍት የሰረቀውን እንዳይሞት እንዳይሽር አድርጎ የሚጥል
 • ፍቅር ሲይዘው ከፀሐይ በታች የመጀመሪያው ሰው እርሱ የሚመስለው፣ ብቻውን ተወልዶና አድጎ ሴት ሲያገኝ የተፈጠረበትን ዓላማ እስኪስት ድረስ “ካለ አንቺ መኖር አልችልም” ብሎ የሚያላዝን
 • የሚያገባትን ሴት ማሳረፍ የማይችል፤ በግራ መጋባቷ ላይ ጥርጣሬን የሚጨምር
 • አባቱን ንቆ በሰው አባት የሚቀና፤ ሀገሩን ሳያውቅ የሰው ሀገር የሚናፍቅ ስሜታዊ ትውልድ ነው ከእርሱ ደግሞ ቆዳ ስስ መሪ ይገኛል።

ቆዳ ስስ መሪ፦
መሪዎቻችንም ከኛው ከስሜታዊው ትውልድ ነውና የሚወጡት ቆዳ ስስ ቢኾኑ አይገርምም።

 • ሀገርን ይገነባል፣ ትውልድን ያንጻል ያሉትን ከማድረግ ይልቅ የሰው ፊት አይተው የሚሠሩ
 • ሰው ሊሰማ የሚወደውን አጣፍጠው፣ ከቁም ነገሩም ቧልት አብልጠው የሚናገሩ
 • “ዶሮን ሲደልሏት በመጫኚያ ጣሏት” እንዲሉ ሠርተው ሳይኾን ባንደበታቸው የሚያድሩ የሚያስተዳድሩም
 • ሕዝቡን የሚያስጨንቀውን አልፈው ተጨነቅኩ ብሎ አቤቱታ የሚያሰማው ላይ የሚዝቱ ቆዳ ስስ መሪዎች ናቸው።

አስታዋሽ ያጣች ሀገር፦
አባት ልጆቹን በኃላፊነት መክሮና ቀጥቶ ካላሳደገ፣ አባት ለልጆቹ ከኾድ በላይ ስብዕና፣ ከገንዘብ በላይ ወገን፣ ከጎጥና ዘር በላይ ደግሞ የሚሞትላት ሀገር እንዳለችው ካላስተማረ ሀገር አስታዋሽ ተረካቢም ታጣለች።

ትውልድ ከእውቀት የተነሳ ሳይኾን ከስሜት ከዘፈንና ከተረት ብቻ ተነስቶ ሀገሩን ከወደደ እርባና ቢስ ይኾናል። ሀገሬ ማን ነች? ሀገሬን ለምን እወዳታለሁ? ለሀገሬስ ለምን እሞታለሁ? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ በአግባቡ ሲያገኝ ከስሜታዊነት ወደምክንያታዊነት ይመጣል። ይኽን ማሳወቅ ደግሞ የአንተ የአባቱ ሥራ ነው። አልያ ግን እሞትላታለሁ ያለበት አንደበቱ ተገልብጦ ደግሞ “የወደድኳትን ያክል ጠላኋት” ብሎ ይሰደዳልና ነው።

ሳተናው!

ስለነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ፣ ስለሀገርህም ታስባለህ? ትቆረቆራለህም?እንግዲያውስ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች ቢኖሩ ቤትህን በስርዓትና በስነምግባር ከመምራት ጀምር።
ከስሜታዊነት የራቀ ምክንያታዊ የኾነ ከራሱ አልፎ አልፎ ስለወገን ስለሀገር መቆርቆር የሚችል ትውልድ መሥራት ከራስ ይጀምራል። ለዚህም መነሻ ይኾንህ ዘንድ አቋምህንም ትፈትሽበት ዘንድ ይኽችን መጽሐፍ አንብብ።

ጣትህን ሌላው ላይ ከመቀሰር ተፈጥሮህን በጠበቀ መልኩ ራስህን በአካል ብቃት፣ በአእምሮአዊ እውቀትና በመንፈሳዊ ልቀት ማሳደግ እንዴት እንደኾነና ጥቅሙን ታገኝበታለህ። ከዚህም የተነሳ ቤትህን፣ ትዳርህን፣ ሚስትህንና ልጆችህን በቀናው መስክ አሰማርተህ ለሀገርህ የሚበጁ ዜጎች የምታበረክትበትን ሐቅ ያወያይሃል።

ክብርና ምስጋና ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ሀገርን ከነሀብቱ፣ ኢትዮጲያዊነትን ከነክብሩ፣ስልጣኔን ከነጥበቡ፣ ባሕልን ከነወጉ፣ ኃይማኖትን ……. ላቆዩልን አባቶቻችን ይኹን።

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *