አባወራነትህን ምን ያጠወልገዋል

ሳተናው!
አንተ ጀግና የአባወራነትህን ሚና እንዲህ እንደቀላል ሚስት በማግባትና ልጅ በመውለድ ብቻ ወስነኸው አትቅር።

ልጅ መውለድ በእርግጥ ቀላል ነው። ነገር ግን ነገ ሀገርህን የሚረከቡ ርዕይ ያላቸው፣ በስነስርዓትና በስነምግባር የተቀረጹ ልጆችን ማፍራት ግን ቁርጥ ውሳኔንና ጽናት ይፈልጋልና አቋምህ ጽኑ ይኹን።

ወንድሜ ሚስት ማግባት ቀላል ነው ። ነገር ግን የውስጥ መሻቷ እና የአንደበቷ ጥያቄ የሰማይና የምድር የሚራራቁባትን ሚስትህን ማወቅ፣ መረዳት እና መፈጸም ጥበብ ይፈልጋል። የሚደንቀው ግን ይኽን ጥበብ ፈጣሪህ ላንተ ቢሰጥህም ዐለም ግን በውሸት በርዛዋለችና ምን ብትመርም እውነትን ፈልጋት።

ወንድሜ በቁሙ ሱሪን መታጠቅ ቀላል ነው። ነገር ግን ቆራጥነት፣ ጀግንነት፣ ርዕትነት፣ ግልጽነት በሚፈለጉበት ቦታ ሱሪ መታጠቅ(መጀገን) ተፈጥሮህ ነው እወቅበት።

ወንድሜ ተሹሞ መሪ መኾን ቀላል ነው። ነገር ግን በተፈጥሮ አቻህ ከኾነችው፣ በፍቅር ሠንሠለት ከተሳሰረችው ሴት ላይ መሾም እርሷንም መምራት ግን ትልቅ ጥበብ፣ ብልሃትና በራስመተማመንን የሚሻ ነው።

አባወራነትህ ዘወትር ልታሳደግው፣ ልታሰለጥነው እና ስለእርሱም ልታጠና(ልታነብ) የሚገባህ ሚና ነው እንጂ በአንድ ቀን ድግስ ባል ኾኛለህ፣ አልያም በአንድ ቀን ወሊድ አባት ኾኛለሁ ብለህ ብታርፍ ትዳርህ/ቤትህ አይንህ እያየ ይፈርሳል።

አባወራነትህን ከሚያጠወልጉትና ፣ ከሚያቀጭጩና ፍሬም እንዳያፈራ(እንዳተፋራ) አንቀው ከሚያስቀሩት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ምቾት ነው።

አብዛኞቻችን ምንም እንኳ ማደግና መለወጥ ብንፈልግም አኹን ከለመድነው ምቾት ግን መውጣት ወይም መራቅ በፍጹም አንፈልግም። ራሳችንን ብንለውጥ ከዚህ የተሻለ ይመጣልን ሳይኾን የባሰው ይኾናል ብለን እንፈራለን። ስለዚህም ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ተመሳሳይ ሥራን እየሠራን የተለየ ውጤት የምንፈልግ ኑሮኣችን፣ እንዲሻሻል የምንፈልግ፣ ትዳራችን እንዲሻሻል የምንፈልግ ነን።

ቁምነገሩ ግን ተመሳሳይ ሥራን ደግመው ደጋግመው እየሠሩ ለውጥን ኃሳብ ላይ አንጠልጥሎ የተለየ ውጤት መጠበቅ በሕይወታችን እንድንሰላች፣ ተስፋም እንድንቆርጥ ማድረጉ ነው።

ምቾት
ሳተናው! ምቾት ትልቁ የእድገትህ ማነቆ ነው። “እኔ መች ተመቸኝና?” ካልከኝ ደግሞ “አኹን ካለህበት እንዳትወጣ ማን ከለከለህ?” እልሃለሁ። አየህ ይኼኛው ኑሮ “አልተመቸኝም” ትላለህ እንጂ በዚህ ኑሮ ከለመድካቸው ነገሮች በመውጣትህ ይቀሩብኛል ብለህ የምትሰጋቸው ነገሮች አሉ።

፩ኛ ከእንቅልፍህ ቀንሰህ ጠዋት ለምስጋና፣ ለእስፖርታዊ እንቅስቃሴ አልያም ለንባብ መነሳት አትፈልግም። ታዲያ ይኼ ምቾት አይደለምን?

፪ኛ “ሚስቴ ታኮርፈኛለች፣ ትከፋለች፣ ቅር ትሰኛለች” ስትል ልክ ያልኾነውን ነገር/ድርጊት አይኾነም ማለት በእርሱም መጽናት አትችልም ታዲያ ይኼ ምቾት አይደለምን?

፫ኛ ልጆችህን ለመከታተል የቤትህን ስነስርዓት የሚኖሩበትንም ስነምግባር ለማስተማር አንዴ ጊዜ የለኝም፣ አንዴ ሆዴ ቡቡ ነው ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲያድጉ ይጠሉኛል “ውሻና ልጅ ቂም አይረሱም” እያልክ ትጠቅሳለህ። ይኼስ ካለኽበት ምቾት ላለመውጣት የምትደረድረው ምክንያት አይደለምን?

ፍርሃት!

ዛሬ ባለህ ትንሽና እርባና ቢስ ምቾት ጎልቶ የሚያስቀርህ ትልቁ በሽታ ፍርሃት ነው። አዎ! በአባወራነትህ የተጣለብህን ኃላፊነት ለመወጣት የተሰጠህን ሚና መጫወት ግድ ይልሃል። አንድ ኳስ ተጫዋች ዋንጫም ፈልጎ እግሩ እንዳይጎዳም ፈርቶ ይኾናል እንዴ? አንተ የተሻለ ሕይወት፣ ትዳር፣ መገንባት ከእርሱም ውስጥ ኃላፊነት የሚሰማቸው ልጆች ማፍራት ከሻህ ይኽን ለማድረግ ስትነሳ የሚመጡትን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ዝግጁ መኾን አለብህ።

ሳተናው! መውደቅን፣ መጋጨትን አትፍራ ከሚስትህም ጋር ቢኾን። ነገር ግን እንደ አብሿም በረባው ባረባው ተደባደብ አላልኩህም። ላመንክበት ዓላማ ጽና ጸብን ፣ ጭቅጭቅን፣ ግጭትን ሸሽተህ ከዓላማህ ዝንፍ አትበል ይኼም ይጽናብህ ማለቴ እንጂ አልያ ከማንም ቀድማ የምትንቅህ ሚስትህ ናት።

አንተ አቋሜ ይኼ ነው፣ አጥሬ እዚህ ጋር ነው ስትል እርሷ በትንሽ ትልቁ አጥርህን፣ ድንበርህን ትፈትናለች፣ ትነቀንቃለች በቀላሉ ከጣለችውም እመነኝ እንዳንተ የምትንቀው የላትም።

አባወራነትህ እንዳይጠወልግ
እንግዲህ ልብ አድርግ! ከእርሷ ጋር መጋጨትን ፈርተህ(ፍርሃት)፣ ጭቅጭቅ የሌለበት ኑሮ ተመኝተህ(ምቾት) ስትኖር አባወራነትህ ይጠወልጋል፤ ይቀጭጫልም። ይኽ የጠወለገ እና የቀጨጨ ሚናህም ፍሬ ማፍራት(ልጆች) ይሳነዋል።

አስተውል! ሠርተህ ወጥተህ ወርደህ ሚስትህና ልጆችህ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት ተገቢ ቢኾንም የሚናህ ዝርዝር ግን ከዚህ በላይ ነው።

ወዳጄ ይህች አገር በስነስርዓትና በስነምግባር የሰለጠነ ትውልድ ይገባታል። ይኽን ልትሰጣት የምትችል ካልመሰለህ አታግባ ከዚያ በፊት ራስህን አሰልጥን።

ትውልድን(ልጆችን) መስጠት የፈጣሪ ሥራ ቢኾንም የተሰጠንን መሥራት፣ ማሰልጠንና ለቁም ነገር ማብቃት ግን የእኔና የአንተ ሥራ ነው። ለዚህ ደግሞ ርዕይ፣ ዓላማ፣ አቋም፣ ጽናት፣ ትጋት፣ ትዕግስት ያስፈልጉናል። እነዚህንም ስንለማመድ የሚመጡት ፈተናዎች እኛን የሚሠሩን የሚያሳድጉን እንጂ የሚያፈርሱን አይደሉም።

ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *