አባወራነት፦ራስን አውቆና ይዞ ለሌሎች መትረፍ

ሳተናው!
አንተ ወደ አባወራነት ስትመጣ ትልቁ ትኩረትህ መኾን ያለበት ራስህን(ፍጥረትህንም ኾነ ታሪክህን) ማወቅ ነው። ሲቀጥልም በዙሪያህ ያሉ ፍጥረታትን (ሰዎችንም ጨምሮ) እና በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ እንደየደረጃውና አስፈላጊነቱ ተፈጥሮኣዊ ባሕርያቸውንና ስጋዊ ጠባያቸውን መረዳት ግድ ይልሃል።

ራስህን ሳታውቅ ይኽም ማለት ከየት እንደመጣህ? ለምን እንደመጣህ? ማን  እንዳመጣህ? በምን እንደመጣህ? ከምን እንደመጣህ(እንደተሠራህ)? እና ወዴትስ እንደምትሄድ ሳትረዳ ሌላውን ፍጥረት አኗኗሩንም መመርመር አያተርፍህም።

ስለራስ ለማወቅ የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም ከየትኞቹም በላይ ግን ለእኔ በኃይማኖት ትምሕርት ውስጥ እንደተማርኩት ራስን ማወቂያ መንገድ አለ ብዬ አላስብም።

ይኽ በእንዲህ እንዳለ ግን ራስህን ካላወቅህ፣ ስለራስህ “ይኼነው” ብለህ የምትይዘው ነገር የለህም። ስለራስህ ደግሞ ይኼ ነው ብለህ የምትይዘው ነገር ከሌለህ ደግሞ ምንህ ለሌሎች ይተርፋል።

ራስህን ባለወቅክበት (ተፈጥሮኣዊ ማንነትህንና ታሪካዊ አመጣጥህን) ባልተረዳህበትም ሕይወት ኑሮህ የምስኪን አልያም የጋጠወጡን ዱርዬ፣ ድካምህም ከንቱ መኾኑ አይቀርም።

ሳተናው!
ለሰው ለመቆርቆር ብሎም ለመትረፍ መጀመሪያ ራስህን እወቅ፣ ያለህን ጠብቅ፣ በራስህ ተማመን፣ ባወቅከውና ባለህም አግባብ ኑር። ምስኪን ራሱን ሳይረዳ (ጠብቆም ኾነ ላልቶ በየተራ ይነበብ)፣ ያለውን ሳያውቅ ሰውን ሊረዳ(እንደቀደመው ይነበብ) ይወዳል።

ይኽም ብዙውን ጊዜ ከሰው እንዲጠብቅ ሲያደርገው ጠብቆ ባጣበት ጊዜ ኹሉም ብስጩ ይኾናል። እርሱ ለሰው ሲል የራሱን፣ ራሱንም ያጣል ያውም ላይመሰገን፤ ሊበሳጭም።

ሳተናው!
አንተ በአባወራነት ጉዞህ መጀመሪያ ራስህን መርምር በዚኽም ከዚህ በፊት ለጠቀስናቸው ጥያቄዎች መልስ አግኝ። አንተ ባወቅከው በያዝከውና በምትተማመንበትም ማንነት መኖር ስትችል ብቻ ያለ ጸጸት ለትዳርህ፣ ለትውልድ ብሎም ለሀገር መትረፍ ትችላለህ።

ስለራስህ ያለህ ግንዛቤ ግን የተዛባ ሲኾን በያዝከው ማንነት አትተማመንም። ከዚህም የተነሳ ምን ቢሞላልህ የበታችነት ስሜት የሚሰማህ ሰዎች ስላንተ ምን እንደሚሉ የሚያስጨንቅህ ትኾናለህ።

ስለ አንተም አንተ ራስህ ስትጠየቅ “እኔ እንዲህ ነኝ” ከማለት ይልቅ “ሰዎች እንዲህ ይሉኛል” በማለት የሰዎች ጭብጨባና ሙገሳ አንተን እንዲገልጽህ ትፈቅዳለህ። ይኽ ደግሞ በእጅ አዙር አንተን በምትሠራው ሥራ ጭብጨባና ሙገሳ እንድትጠብቅ የሰውም ፊት እንድታይ ስትገደድ፣ አልፎ ተርፎም የሰዎችን ይኹንታ የምትሻ ትኾናለህ።

አንተ ራስህን ስታውቅና ስትኾን፣ ስትኖረውም በራስ መተማመንህ ይጨምራል፤ ጭብጨባና ቲፎዞም አትፈልግም። አሥር ጊዜ “ልክ ነኝ?” “ልክ አይደለሁም?” የሚል ጥያቄም አታበዛም። ያመንክበትን ትሠራለህ፣ ለሥራህም ኃላፊነት ትወስዳለህ።

አንተ ራስህን ስታውቅና እርሱንም ገንዘብ ስታደርግ (ጥሪት ሲኾንህና እንደዚያም ስትቆጥረው)  ለተቸገሩት ከሚያስፈልጋቸው የምትችለውን ትሰጣለህ። ስትሰጣቸውም ስለሚያስፈልጋቸውና ከጉድለታቸውም አንጻር አንዲት ቀዳዳ እንዲሸፍንላቸው ነው። በዚኽም አንተ በይሉኝታ ሳይኾን በመስጠትህ ብቻ ስለምታገኘው ደስታ ስትል ትሰጣለህ።

ምስኪን እንደሚያደርገው (ብሰጥ ይሰጡኛል፣ ብወድ ይወዱኛል፣ ብውል ይውሉልኛል….ብለህ) ስትሰጥ ቀን ቆጥረህ፣ ቦታ ወስነህ፣ ስጦታህን አስልተህ ከሰዎች መልስ ጠብቀህ ግን አትስጥ።

ይኹንና በስጦታህ ልክ የኾነ ቦታና ቀን እንዲመለስልህ የምትፈልግ ኮነ አስቀድመህ በግልጽ ንገራቸው እንጂማ ከሰጠህ በኋላ ሰውን መታዘብ፣ በጸጸትም መቆጨት አንተን ብስጩና በሽተኛ ከማድረግ ውጪ ፋይዳ የለውም።

አንድም ደግሞ “ስጠን” ብለውህ ብትሰጣቸው እንኳ በጠየቁህ ልክና መጠን ስጣቸው እንጂ መመለስ ከሚችሉት በላይ ሰጥተህ እነርሱንም ለይሉኝታ ራስህንም ለስሞታ እንዳይዳርግህ ተጠንቀቅ።

ሳተናው!
ይኽ በአባወራነትህ ራስህን አውቀህ፣ ያወቅከውን ይዘህ፣ በራስህም ተማምነህ ኖረህበትም ለሌሎች መትረፍ ለምትወዳት ሴት ለሚስትህም ቢኾን ይሠራል፤ በመጠኑ ቢለይም።

እንዴት?….. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *