አባወራነት ሲጠወልግ/ሲወድቅ እማወራነት ያብባል ክፍል 2

ሳተናው!
አኹን የምጽፍልህ ለመቀበል የሚከብድ ሐቅ፣ ለማመን የሚቸግር እውነት፣ ለመዋጥ የሚመርም መድኃኒት ነው። በርግጥ ብዙዎቹ የአባወራ ገጽ ጽሑፎች እንደዚህ ነበሩና ምቾትን ለለመዱ አንባቢዎች ፈተና ይኾናሉ።

አንተ እውነትን መርምረህ በተጠራህበት ልክ፣ ለተጠራህበት ዓላማ ለምትኖረው ወንድሜ ግን እነዚህ የኑሮህ ስንቅ ናቸውና ሳትሰለች አንብብ መርምር ተለማመዳቸውም።

የሰውን ዘር ለዘመናት በትዳር፣ በቤተሰብ፣ በማሕበረሰብ፣ በሕብረተሰብ እና በሀገር ገንብቶ ሲጓዝ የነበረው አባወራዊው ስርዓት አኹን የመጠውለግ/የመድረቅም አዝማሚያ ይታይበታል።

በዘመናችን አባትነት፣ ባልነት፣ ወንድነትና ራስነት (አባወራነት) ከየትኛውም የሰው ልጅ ከኖረባቸው ዘመናት ይልቅ በፈተና እየተናጠ ነው። ከዚህም የተነሳ ትዳር፣ ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ ሕብረተሰብ፣ ሀገር በፈተና እየተናጡ ነው፤ ሕልውናቸውም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ፈተናዎቹም፦ ስነምግባራዊ፣ ስነስርዓታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ መንፈሳዊ፣ ማሕበራዊ.. ናቸው)

በአካባቢያችን የምንሰማቸው፣ የምናያቸው እና የምናነባቸው ነገሮች አባወራው ትዳሩን እንዲመራ፣ ቤተሰቡንም እንዲያስተዳድር ከማገዝ ይልቅ ሚናውን የሚንቁ፣ ስሕተቱን እየፈለጉ የሚያጎሉና የሚከሱ፣ በድካሙም የሚሳለቁ ናቸው።

ብዙዎቹም በስልጣኔ እና በዘመናዊነት ስም ሚስቱን እንዲያስቀድም እርሷንም እንዲከተል ይኼም ሲኾን ትዳሩ እንደሚሰምር በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ያሳርፉበታል። ከእነዚህም ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት መገናኛ ብዙኃንና በእነርሱም ውስጥ የሚተላለፉት ኪነጥበባዊ ይዘት ያላቸው መርሃግብሮች ናቸው።

ከእነዚህ ተጽዕኖዎች ራሳቸውን ጠብቀው ከሚወራውና ከሚሰማው ርቀው የሚኖሩትን አምባገነን፣ ኋላቀር፣ ግትር እና የመሳሰሉትን አሸማቃቂ ቃላት እየለጠፉ እነርሱንም ኾነ ቤተሰቡን የማሳፈር ስርዓታቸውንም የማንቋሸሽ ነገር ይታያል።

ይኼንኑ ተከትሎም ወንዱ ፈጣሪው የሰጠውን ትውልድ የሚቀጠልበትን ትዳር፣ ሀገር የሚመሠረትበትን ቤተሰብ መምራት ቸል ይላል፤ ይፈራልም። እንዲኹም እነዚህን መሠረታዊ ተቋማት ቅርጽ የሚያሲዝበትን ስነስርዓትና ስነምግባር በመጠበቅ ራሱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን ማስጠበቅ ግድም ማለት ይተዋል።

ሳተናው!

ወንዱ(አባወራው) ተማርን ሰለጠንን እንዲኹም ዘመንን ከሚሉት አካላት ከሚደርስበት በዓይነት እና በመጠን የሚለያዩ ጫናቸው የተነሳ ፈጣሪ የጣለበትን ኃላፊነት ይተዋል። ሲቀጥልም የተሰጠውን ሚና እርሱንም የሚወጣበትን ጥበብና የተፈጠረለትንም ዓላማ ስለሚያጣው ልቡን ያሳርፍለት ዘንድ ለሌላ እርሱንም ኾነ ትዳሩን፣ ቤተሰቡን፣ ሀገሩን፣ ዘሩን(የሰውን ዘር) ለሚያጠፉ ድርጊቶች ወይም ቀውሶች ተላልፎ ይሰጣል።

እነዚህም፦ ሴሰኝነት፣ ሱሰኝነት፣ ፀበኝነት፣ ግዴለሽነት እንዲኹም ለድብርት፣ ለጭንቀትና መሰል በሽታዎች፣ ለሴቷ ፍላጎት ማጣት ስንፈተ ወሲብ፣ እና ለሌሎችም በአያት በአባቶቹ ዘንድ ለማይታወቁ የጤና እክሎች ይጋለጣል።

የእርሱ መጠውለግና በየመገናኛ ብዙኃኑና በየሙያ መስኩ በሚነሱ ርዕሰጉዳዮች ኹሉ ቅድሚያ እየተሰጠውና እየተበረታታ ያለው የሴቶች ወደ አመራርነት መምጣት ለእማወራዊው ስርዓት መሠረት እየጣለ ነው።

“እማወራዊ ስርዓት?” አዎ እማወራዊ ስርዓት ሴቶች የትዳሩ መሪ፣ የቤቱ አስተዳዳሪ፣ የቤተሰቡ ተጠሪ የሚኾኑበት ስርዓት። ልብ አድርግ! ይኽ ይበልጡን የሚመለከተው ወንድ ወዳና አግብታ እርሱንም ስትከተል የነበረች አንዲት ባሏ በሞት የተለያትን ሴት ሳይኾን በፈቃዳቸው ለኑሮኣቸው ወንድ አንፈልግም ብለው በፍቺም ኾነ ያለጋብቻ ልቅ ኾነው የሚኖሩትን ሴቶች ይኽንንም የሚደግፉላቸውን አልጫ ወንዶች እንጂ።

ይኽ ስርዓት ምን ያክል የሰው ልጅ መጥፊያው እንደኾነ ስታውቅ ብቻ ሁሉን አዋቂ የኾነው ፈጣሪ የትዳርን መሪ፣ የቤትን አስተዳዳሪ የሚስትን ራስ ወንድ ያደረገበት ምክንያት ይገባሃል።

እንዴት፣ ለምን፣ ምን ማለት ነው፣ ? … ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *