አባወራነት

አኹን አኹን በጾታዊ የ”እኩልነት” አስተምህሮ እየመጡ ባሉ ችግሮች ላይ ላለፉት ስድስት ወራት በዚኽች ገጽ አንብበናል። በወንዶች ላይ ቀጥሎም የችግሩ ሰለባ በሚኾኑት ሴቶች፣ ልጆች፣ ትውልድ ብሎም በጠቅላላው ሀገር ላይ የሚያመጣውን ጉዳት በአባወራው ገጼ ላይ ነካክተናል። የተወሰኑትንም ረጅም ጽሑፍ ማንበብ ለሚሰለቹት በቁንጽል ተቀምጠዋል። እግዚአብሄር ቢፈቅድ ብንኖርም እንቀጥላለን ከዚህም በሰፋ መልኩ እንወያያለን።
አባወራነት
እኔ “አባወራ” የሚለውን ቃል የመረጥኩት ወንድ ልጅ ተፈጥሮውን የሚመስልበት ልከኛ ስም ኾኖ ስላገኘሁት ነው። ለእኔ ሹመትን፣ ጀግንነትን፣ ኃላፊነትን፣ መሪነትን፣ ወንድነትን……… ይገልጽኛል። እግዚአብሄር ሳያዛንፍ የፈጠረውን ፍጥረት ዓለም አዛንፋ መልሳ “በእኩልነት” ልፋፌ አስተካክላለሁ ትላለች።
ነገር ግን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ወንዶች ከየትኛውም የሰው ልጅ ከኖረበት ዘመን ይልቅ በራስ መተማመናቸው የወረደበት፣ ከእውቀት የራቁበት፣ ለንግግራቸውም ኾነ ለድርጊታቸው ኃላፊነት የማይወስዱበት፣ ዓላማ ቢስ ሕይወት የሚገፉበት፣ ራሳቸውን ሳይኾን ሴቶችን በመምሰል ሴቶችን(ሚስቶቻቸውን) ግራ ያጋቡበት፣ የወገንን፣ የሃገርን ፍቅርን ያጡበት፣ ከመሥራት መብላትን የመረጡበት፣ ክብራቸውን ያሽቀነጠሩበት፣ ከማወቅ ማውራትን ያስቀደሙበት፣በኃሳባቸው ከመጽናት እንደ እስስት የሚለዋወጡበት፣ ለሚስቶቻቸው ከባል ይልቅ ወንድም የኾኑበት፣ ከአእምሮአቸው ይልቅ ለጭንቅላታቸው(ለፀጉራቸው) የሚጨነቁበት፣ ከአፋቸው ለሚወጣው ሳይኾን ለአፋቸው ጠረን፣ለከንፈራቸው ልስላሴ የሚያስቡበት፣ ዓለምን ለመጥቀም(ለመንከባከብ) ሳይኾን ለመጠቀም ብቻ የሚሮጡበት፣ ማፍቀር ሲገባቸው አልተፈቀርንም ብለው የሚያጉረመርሙበት፣ የተሰጣቸውን የወደዱትን መጠየቂያ ድፍረት ጥለው ፍቅር ይዞኛል ብለው የሚያላዝኑብት፣ ቤተሰብ መምራት የተቸገሩበት፣ ተፈጥሮን ከመመርመር እና እውነትን ከመሻት ይልቅ ተራ እንሰሳዊ ስሜታቸውን በጭብጨባ የሚያጸድቁበት፣ የወሲብ ፍላጎታቸውን በአግባቡ ከማሳረፍ(ከመወጣት) ይልቅ ሴሰኛ የኾኑበት፣ የራሳቸውን የባህላቸውን፣ የአባቶቻቸውን መልክ ጥለው የሰው ጭምብል ያጠለቁበት፣ ከመሰካካት እና ከመገጣጠም መስተካከልን የመረጡበት፣ ለወንድ ልጆቻቸው አርአያ ለሴቶች ልጆቻቸው ፍቅር መኾንን የደበላለቁበት፣ ደርሰው ሆደ ባሻ፣ ቡቡ እና ሌሎችንም የማይኮነውን(መኾን የማይገባውን) ብዙ የኾኑበት በብዙ የከሰርንበትም ዘመን ኾኗል።

አሁንም ቢኾን የሰው ልጅ በወንድ እና በሴት ጾታ ቢፈጠርም ቅሉ የስጋው መልክ(ጠባይ፣ባሕርይ) አፈርን የነፍሱ(ጠባይ፣ባሕርይ) ሥላሴን መምሰሉ እርግጥ ነው። ይሁንና ምንም በሰውነታቸው(ሰው በመኾናቸው) አንድ ቢኾኑ የተፈጠሩበት ዓላማ ያሳኩ ዘንድ ከጅምሩ በጾታ ለይቷቸዋልና በአንድ ዓላማ ውስጥ ኾነው ሚናቸው ግን ለየቅል ነው።በተለይም ከትምህርት ኹሉ አስቀድማ ኃይማኖትን ለምታስተምር ሃገር ይኼ ግልጥ መኾን ነበረበት።

የአንተ እና የእኔ ጥያቄ እና ምርመራ ታዲያ ምን መኾን አለበት? ሰው ኾኜ ሳበቃ ወንድ አድርጎ ወደዚህ ምድር ያመጣኝ በእኔ ላይ ምን ዓይነት ዓላማ ቢኖረው ነው? እና ምንስ ዓይነት ሚና ተለይቶልኝ ነው? የሚሉት ናቸው።

ሰው የእግዚአብሄርን ፍጥረት ሲያጠና እስካሁን ድንቅ ፣ልዩ እና ለመረዳት የተወሳሰበ የኾነበት ራሱ የሰው ልጅ ነው። በሥላሴ አርአያ መፈጠሩ ራሱን ለመመርመር እጅግ ከብዶበታል። እውቀት ተከፍሎ ቢሰጠንም ባሕርያችንን ተረድተን በገባን መጠን መኖር ግን ዓላማችንን እንድናቅ መንገዳችንን እንዳንስት ያግዘናል።
የአባወራ ገጽ ዓላማም እንደ እንደሚናችን ተለይቶ የተሰጠንን ጾታ ኑሮአችንን ገንቢ እና ፈጣሪ ያስቀመጠውን ግብ የመታ እንዲኾን ሰውን ማገዝ ነው። በጾታ እኩልነት ሰበብ ዓለም የምትሸርበውን ሴራ ሰዎች በየዋህነት እንዳይጎነጩት እንዳይጨልጡትም ማሳሰብ ነው።
ይቆየን……

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *