አባወራውና የስልጣኑ ነገር

አንድ አባት ቤቱን፣ ቤተሰቡን፣ ሚስቱን ልጆን በስነስርዓትና በስነምግባር መምራት አለበት። ምሪቱም ስልጣኑን፣ ሥራውን፣ መምራቱን ወዶት፦ወዶት ስል አንድም እነርሱንም የሚያገለግልበት መሣሪያ ነውና ይወዳቸዋልና ይወደዋል። አንድም ደግሞ ከፈጣሪው የተሰጠው ሊሠራው የተገባ አምላካዊ ትዕዛዝ ነውና ደስ ብሎት ይፈጽመዋልና ነው።

ይኹንና ዛሬ ዛሬ ወንዶቹ ቤተሰባቸውን/ቤታቸውን ደፍረውና ነጥረው ወጥተው መምራት አይደለም ሲያስቡት ገና ይጠየፉታል፤ ምክንያቱም እነርሱ “ስልጣኔ” የዘለቃቸው “ስልጡን” “ፍቅር” የገባቸው “ደግ” እና “ርህሩህ”(የሚራሩ) አባት፣ ባል ነን ብለው ስለሚያስቡ።

ይኸው ታዲያ ቤት “በጋራ ይመራል፣ ለሁለት ይዘወራል እንጂ ማነው ለአባወራው ብቻ የሰጠው” እየተባለ ትዳራችንን ለፈተና፣ ልጆቻችንን ለጎዳና፣ ሀገራችንን ለልመና፣ ትውልዱንም መረንና ቦዘን እየዳረገ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ታዲያ ለቤታቸው ኃላፊነት ቢሰማቸውም ከሚስታቸው ጋር ሙግቱን ፈርተው እርሷ በወሰነች ኹሉ የሚስማሙ ለቤታቸው ሕግና ስርዓት መቅረጽ ስነምግባርንም ማስተማር የማይችሉ ደካማና ወኔ ቢስ አባቶችን(ወንዶችን) አስገኘ።

የዛሬ የማሕበረሰባችን ቀውስ፣ የልጆቻችን ከትምሕርት ቤት ጠፍቶ በየጫት ቤቱ መገኘት፣ ወሮበላ መኾን፣ የሴቶች ልጆቻችን ቶሎ መጎርመስ(የወር አበባን በ9 እና በ10 እድሜ ላይ ማየት)፣ ለአዛውንቶች፣ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለሀገርም ኾነ ለመሪዎቿ ክብርን አለመስጠት የዚህ ውጤት ናቸው። ኃላፊነታቸውን፣ ግዴታቸውን ያልተወጡ፣ በስልጣናቸው ቤታቸውን ያላገለገሉ፣ ስጦታቸውን/ጸጋቸውን በጣሉ/በዘነጉ ወንዶች(አባቶች) የተፈጠረ።

ሳተናው ወንድሜ!

አንተ ግን የነገይቱን ኢትዮጲያ ለሚቀጥለው ትውልድ መገንባት ትሻለህን? እንግዲያውስ ተምታቶባት ከምታምታታብህ ዓለም ተጠበቅ፣ መስማት ያለብህን እውነት ሳይኾን መስማት የምትፈልገውን ደስ ስለሚል ውሸት ከሚነግሩህ መገናኛ ብዙኃን ራቅ፣ ጥራዝ ነጠቅ እየኾነ የመጣውንም የማሕበራዊ ድረ -ገጽንም ወሬ መርምር።
በተለይም ስለ ትዳር፣ ስለ ወላጆች፣ ስለ ልጆችና ቤተሰብ ከመሥራቹ ከፈጣሪ የተሰጠህን ትዕዛዝ “በስልጣኔ፣በእኩልነት ስም” ከዓለም ርኩሰት ጋር አታሞዳሙድ/አተደራድር።

አንተ አባወራ፦ አባት የቤትህም መሪ ነህ። ስለዚህም ደግሞ መሠረታዊው ከልጆችህ ጋር ልትመሠርተው የሚገባው ግንኙነት የመሪነት ስልጣንህን እንዲያውቁ እንዲያከብሩም ማድረግ ነው። አንተን የሚያዩህን፣ የሚዳስሱህን፣ የሚስሙህን፣ የሚያሸቱህን፣ ፍቅርህን፣ ስጦታህን የሚያጣጥሙት አጠገባቸው ያለኸውን አንተን አባታቸውን ያላከበሩና ያልፈሩ ልጆችህ ያላዩትን የሰማዩ አባታቸውን እንዴት ያከብሩታል ይፈሩታልስ?

አስተውል! ትዳርህ አምላካዊውን ዓላማ የምትፈጽምበት ባንተ ሳይኾን በእርሱ ታቅዶበት የተሰጠህ የሥራ ቦታ ነው(የምን ሥራ? እግዚአብሄር ዓላማውን ይፈጽም ዘንድ የመሠረተው ተቋም ውስጥ የምትሠራው የፍቅር ሥራ ነው)። ይኽንን ፍቅር፣ ስነስርዓት፣ ፈሪሃ እግዚአብሄር ለቤትህ የምታስተምርበትን ቢሮ ደግሞ ብታስደፍርና ግዴታህን ባትወጣ ተጠያቂነቱ ከራስህ አይወርድም።

ልጆች ሲወለዱ እናትና አባታቸውን ማክበር አውቀው አይወለዱም እኛ እናስተምራቸዋለን እንጂ። አክብሮቱንም እንዲፈጽሙት ግድ እንላቸዋለን። ይኼንን ወላጆቻቸውን የማክበር አምላካዊ ትዕዛዝ የማስጠበቅ መፈጸማቸውንም የማረጋገጥ ግዴታ ደግሞ ያንተ ነው።

ይኽንን ለመፈጸም ግን አንተ መጀመሪያ ስርዓት ሳይኖርህ ስነምግባርንም ሳታውቅ አይኾንም። ልጆችህን በዱላ ብዛት የምታሰቃያቸው ዱለኛ አልያም እርግፍ አድርገህ የተውካቸው ግድ የለሽ ልፍስፍስም እንድትኾን አይደለም።ይልቅስ በተሰጠህ ስልጣን ቤተሰብህን የምታገለግልበት ጠንካራ አባት አባወራም እንድትኾን ያሻል። የተሰጠህ ስልጣን ጥቅም የአባትነትህም ትርጉሙ ይኼው ነው።

አባወራነት ቤትህን የምታገለግልበት መሳሪያ እንጂ ሽልማትህ አይደለም(መቼ ለሠራኸው ትሸለማለህ?)። አንተ በፍጹም ልብህ እና ፈቃድህ ለፈጣሪህ ተገዝተህ ሚስትህንና ልጆችህን ልታኖር፣ ልትመራ እና ልታስተዳድር ይገባሃል። ይኽንን ግዴታ ትፈጽምበት፣ ታገለግልበትም ዘንድ ይኽ ስልጣን ተሰጠህ።

ልብ አድርግ! የአባትነት ስልጣንህ ማገልገያ መሣሪያህ ነው። የሰጠህም ፈጣሪ እንጂ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወይም ሌላ አይደለም። የሰጠህ እርሱ የምታኖራቸውም በእርሱ ፈቃድ ለእርሱ ወደ እርሱ እንድታደርሳቸው ነው። ስልጣኑን ያልሰጡህ አካላት እንዴት እንደምትጠቀምበት ሊወስኑ አይችሉም።

“ስልጣን ማገልገያ መሣሪያ ነው” ሲባል ሰምተሃል መቼም፤ ከአባወራነትህ አንጻር እንዴት እንደኾነ እንየው…. ይቆየን

Author: Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

Henok Hailegabriel

A Husband & a Father who believes in men dominance, anti feminist and helps other men to boost their masculinity, dominate life & save their marriages.

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *